MAP

የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚዬም (SECAM) 20ኛ ጠቅላላ ጉባኤ 2ኛ ቀን ውሎ የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚዬም (SECAM) 20ኛ ጠቅላላ ጉባኤ 2ኛ ቀን ውሎ  

የሴካም የ2ኛ ቀን ውሎ የአፍሪካ ቤተክርስቲያን የረዥም ጊዜ ራዕይ እና ከአንድ በላይ ማግባት በሚሉ ጭብጦች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገለጸ

“ኢየሱስ ክርስቶስ የተስፋ፣ የእርቅ እና የሰላም ምንጭ” በሚል መሪ ቃል በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚዬም (SECAM) 20ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከአፍሪካ የተውጣጡ ብጹአን ጳጳሳት የተገኙ ሲሆን፥ የዚህ ጉባኤ የሁለተኛ ቀን ውይይቶች ያተኮሩት በጉባዔው ማዕከላዊ ጭብጥ ላይ በማሰላሰል እንዲሁም የአህጉሪቱ የረዥም ጊዜ ራዕይ ላይ በመወያየት እንደነበረ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዕለቱን ስብሰባ እና አጀንዳ የመሩት የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚዬም (ሴካም) ሁለተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት እና በናይጄሪያ የዮላ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ እስጢፋኖስ ዳሚ ማምዛ፣ በካሜሩን የባሜንዳ ሊቀ ጳጳስ አንድሪው ኒኪያ፣ እንዲሁም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢዶፋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት የመካከለኛው አፍሪካ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤዎች ማህበር ቋሚ ኮሚቴ አባል እና የክልል ተወካይ ብጹዕ አቡነ ጆሴ ሞኮ ሲሆን፥ ብጹዕ አቡነ ሞኮ ምልአተ ጉባኤውን ያማከለ ንግግር ማድረጋቸው ተነግሯል።

ያለፈውን መገንባት
ታዛቢዎች እና አንዳንድ ብጹአን ጳጳሳት ሴካም ለአፍሪካ ቤተክርስቲያን ያስቀመጠውን የ 25 ዓመታት ራዕይ ተነሳሽነትን እንደ ወሳኝ እና አበረታች እርምጃ የገለጹት ሲሆን፥ ምናልባትም ይህ ተነሳሽነቱ የአፍሪካ ቤተክርስቲያን እራሷን “የእግዚአብሔር ቤተሰብ” አድርጋ ከመግለጿ ጋር ሊነፃፀር ይችላል ብለዋል።

ይህ ራዕይ መነሻውን ያደረገው በ 1986 ዓ.ም. በሮም በተካሄደው የአፍሪካ ሲኖዶስ ላይ እንደሆነ እና ይህ ራዕይ በአፍሪካ ማህበረሰብ ውስጥ የተንሰራፋውን የመተሳሰብ፣ የአንድነት፣ የኡቡንቱ እና የጠንካራ ግንኙነቶች እሴቶች ላይ አጽንኦት እንደሚሰጥ የተነገረ ሲሆን፥ በወቅቱም ብጹአን ጳጳሳቱ ‘በአፍሪካ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን እንደ አምላክ ቤተሰብ’ የሚለውን ሞዴል ሀሳብ አቅርበው እንደነበር እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ‘ኤክሌሺያ ኢን አፍሪካ’ በተሰኘው የድህረ ሲኖዶሳዊው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ይህንን የአፍሪካዊያን ብጹአን ጳጳሳት ራዕይ እንዳጸደቁት ተገልጿል።

አዲስ ጉዞ ተጀምሯል
ብጹአን ጳጳሳቱ አርብ ዕለት ባደረጉት ውይይት እንደ ጎረጎሳዊያኑ ከ 2025 እስከ 2050 ባሉት የ 25 ዓመታት ጉዞ ላይ ሰፊ ምክክር ያደረጉ ሲሆን፥ በአፍሪካ የምትገኘው ቤተክርስቲያን “ዛሬ ላይ የት ነን?”፣ “በሚቀጥሉት ሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ የት መሆን እንፈልጋለን?” እንዲሁም “ወደ መዳረሻችን እንዴት ነው የምንደርሰው?” የሚሉትን ሶስት ቁልፍ ጥያቄዎችን ራሷን እንደምትጠይቅ ጠቁመው፥ ለእነዚህም ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሴካም ከሁሉም የአፍሪካ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤዎች እና ከተመረጡ የነገረ መለኮት ምሁራን ጋር ሰፊ ምክክር ማድረጉ ተገልጿል።

በዚህም መሰረት የተገኙት ውጤቶች ‘ለሚቀጥሉት 25 ዓመታት በአፍሪካ ውስጥ ያለው የቤተክርስቲያን-የእግዚአብሔር ቤተሰብ ራዕይ’ በሚለው ሰነድ ውስጥ ተሰንዶ መቀመጡን አብራርተዋል።

ጉባኤው በቤተክርስቲያን ውስጥ “በድፍረት፣ በእምነት፣ በኅብረት እና በአንድነት ለመራመድ” ካለው ፍላጎት የተነሳ ይህንን ስትራቴጂካዊ ፍኖተ ካርታ በአስቸኳይ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑ ተነግሯል።

ከአንድ በላይ ማግባትን በተመለከተ የአፍሪካ ሲኖዶስ ሰነድ ምን ይላል
ከዚህም በተጨማሪ የጉባኤው ተሳታፊ ብጹአን ጳጳሳት አርብ ዕለት ከሰዓት በኋላ ባካሄዱት ውይይት በአፍሪካ ክርስቲያናዊ ጋብቻ ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት ስለሆነው ከአንድ ሚስት በላይ የማግባት ባህላዊ ልማድን በማንሳት ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳስ ንኪያ እና ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ እንደተናገሩት ብጹአን ጳጳሳት ከአንድ በላይ ሚስት ላላቸው ማኅበራት ፈቃድ ሰጥተዋል ወይም የቤተ ክርስቲያንን የጋብቻ ሥርዓተ ሚስጥር በተመለከተ አስተምህሮ ለመለወጥ አስበዋል ብለው የሚገልጹ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ትክክል እንዳልሆኑ አብራርተዋል።

ከዚህም ባለፈ ብጹአን ጳጳሳቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋብቻ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የዕድሜ ልክ፣ ብቸኛ እና ታማኝ ጥምረት መሆኑን እንደምታስተምር አረጋግጠዋል።

በቅርቡ በተካሄደው ሲኖዶስ ላይ ትኩረት ተደርጎ በዋናነት ውይይት የተደረገበት ጉዳይ እምነቱን የሚፈልጉ ክርስቲያኖችም ሆኑ ያልተጠመቁ እንዲሁም ቀደም ብለው ከአንድ በላይ ሚስት ያላቸው ወንዶች ማህበራት ውስጥ ለሚገኙት ሰዎች የሃዋሪያዊ እንክብካቤ መስጠት እና ትብብር ማድረግ አስፈላጊነት ላይ እንደነበር አስታውሰዋል።

ብጹአን ጳጳሳቱ ባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ባሉ ማህበራት ውስጥ ያሉ ግለሰቦች በቀላሉ ለመውጣት እንዳይችሉ አስቸጋሪ እንደሚያደርጉ፥ በተለይም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሴቶች እና ሕፃናት እንደሚጎዱ ገልጸው፥ ‘የቤተክርስቲያኒቷ ሲኖዶሳዊ አካሄድ ማንንም ሰው ወደ ኋላ የማይተው፣ ሁሉንም የሚያካትት እንጂ የሚያገል አይደለም’ ሲሉ አሳስበዋል።

ከአንድ በላይ ሚስት ባላቸው ማህበራት ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የሚደረግ ሃዋሪያዊ እንክብካቤ
ጉባኤው ጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም. የተካሄደውን ሲኖዶስ ተከትሎ በተከታታይ ባደረገው ውይይት ከአንድ በላይ ሚስት ባላቸው ማህበራት ውስጥ ላሉት ሰዎች የሚደረግ ሃዋሪያዊ ጥበቃ በተመለከተ ዝርዝር ሰነድ መዘጋጀቱን ያመላከተ ሲሆን፥ ሰነዱ በአፍሪካ የነገረ መለኮት ምሁራን እና በአንዳንድ ብጹአን ጳጳሳት በትብብር የተገመገመ እንደሆነ እንዲሁም ከቅድስት መንበር የእምነት አስተምህሮ ጽህፈት ቤት ጠቃሚ አስተያየቶችን እና ምክረ ሃሳቦች ማግኘቱን ብጹዕ ካርዲናል አምቦንጎ ገልጸዋል።

ከሐምሌ 23-28 ቀን 2017 ዓ. ም. ድረስ በተካሄደው በ20ኛው የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት (SECAM) ምልአተ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን በመወከል ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የጅማ ቦንጋ ሀገረስብከት ጳጳስ እንዲሁም ክቡር አባ ከተማ አስፋው የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጸኃፊ ተገኝተዋል።

04 Aug 2025, 14:47