MAP

የሄይቲያዊያን በፖርት-አው-ፕሪንስ በተከሰተው የቡድን ጥቃት ምክንያት ኬንስኮፍ አከባቢ ከሚገኘው የመኖሪያ መንደራቸው ሲሸሹ የሄይቲያዊያን በፖርት-አው-ፕሪንስ በተከሰተው የቡድን ጥቃት ምክንያት ኬንስኮፍ አከባቢ ከሚገኘው የመኖሪያ መንደራቸው ሲሸሹ  

የሄይቲ ብፁአን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ላቀረቡት የሰላም ጥሪ ምስጋናቸውን አቀረቡ

የሄይቲ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብፁአን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት እና የፖርት ኦ-ፕሪንስ ሊቀ ጳጳስ ማክስ ሌሮይ ሜሲዶር የሄይቲ ብፁአን ጳጳሳት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እሁድ ዕለት ለሄይቲ ሰላም ላቀረቡት ጥሪ ያላቸውን ምስጋና ገልጸው፥ በሀገሪቱ እየተፈጸመ ያለው ወንጀል “ወሰን የለውም” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጥሪ በሄይቲ ባለስልጣናት እና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ እንደሚሰማ ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ለቫቲካን ዜና የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ ሜሲዶር፥ እሁድ ዕለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሄይቲ ሰላም ይሰፍን ዘንድ ላቀረቡት ጥሪ የሃገሪቱ ብፁአን ጳጳሳት ያላቸውን ምስጋና ገልጸዋል።

በቃለ ምልልሱ ወቅት በሃገሪቱ ላይ እየተካሄደ ስላለው ሁኔታ ያብራሩት ሊቀ ጳጳሱ፥ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁኔታውን አስመልክቶ በርካታ ስብሰባዎችን ማካሄዱን አስታውሰው፥ ሆኖም ግን የውይይቱ ውጤቶችን በፍጥነት እውን ለማድረግ እንዳልተቻለ እና የዓለም አቀፉ የጸጥታ ደጋፊ ሃይል በግጭቱ ውስጥ በጣም የተገደበ ተፅዕኖ እንዳለው፣ እንዲሁም ከፍተኛ የሰራተኛ እና ሎጅስቲክ ሀብት እጥረት እንዳለበት አብራርተዋል።

ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ምስጋና
የሄይቲ ብፁአን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት እና የፖርት ኦ-ፕሪንስ ሊቀ ጳጳስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ባቀረቡት የመልአከ እግዚያብሄር ጸሎት ወቅት ስለ ሄይቲ ለተናገሩት ቃላት፣ በተለይም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ‘በሄይቲ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቅረፍ ከዚህ የበለጠ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባው እና ተጨባጭ ተግባራትን እንዲያከናውን የሄይቲን ህዝብ ወክለው ላሰሙት የሰላም ጥሪ የሄይቲ ብፁአን ጳጳሳት ቅዱስ አባታችንን ማመስገናቸውን አስረድተዋል።

ብፁእነታቸው አክለውም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በችግር ውስጥ ላሉ ሕዝቦች፣ ለፍትሕ መጓደል፣ ለጦርነትና ለአመጽ ሰለባ ለሆኑ ሕዝቦች ያላቸውን አሳቢነት በመግለጽ፥ ቅዱስ አባታችን በሄይቲ የምትገኘው ቤተክርስትያን ሁከቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ያላትን ጥሪ ማስተጋባታቸውን ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ወቅት ትኩረታቸውን በሄይቲ እየተካሄደ ባለው ቀውስ ላይ በማድረግ፣ በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ባለው ስቃይ ምክንያት ህዝቡ ‘ተስፋ የመቁረጥ ስሜት’ ውስጥ መግባቱን ጠቅሰው የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን መግለፃቸውን እና በሃገሪቱ የተንሰራፋውን ‘ሁሉንም ዓይነት ጥቃት፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በግዳጅ መፈናቀል እና አፈናን ማውገዛቸውን አስታውሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ‘የሄይቲ ህዝብ በሰላም እንዲኖር የሚያስችለውን ማህበራዊ እና ተቋማዊ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተጨባጭ ድጋፍ እንዲያደርግ በማሳሰብ፥ ‘ሁሉም ኃላፊነት የሚሰማቸው አካላት ታጋቾቹን በአስቸኳይ እንዲፈቱ ልባዊ ጥሪዬን አቀርባለሁ’ ብለዋል።

‘ወንጀል ድንበር የለውም’
ሊቀ ጳጳስ ሜሲዶር ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፣ “በሄይቲ የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ወንጀል ወሰን እንደሌለው እንደምትገነዘብ” አስረድተው፥ ለዚህም በኬንስ-ኮፍ ከተማ በሚገኘው የቅድስት ሄለን የህጻናት ማሳደጊያ አንድ የሦስት ዓመት ህፃን ልጅን ጨምሮ በስምንት ሰዎች ላይ የተፈፀመው የአፈና ተግባር አንዱ ማሳያ እንደሆነ አስታውሰው፥ ይህ የአረመኔነት ተግባር የህይወት እና ሰብአዊ ክብሩን እያጣ ላለው መንግስት እና ማህበረሰብ ውድቀትን ከሚያሳዩ በርካታ ምልክቶች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

“ይህ የአረመኔነት ድርጊት የህይወት ስሜትን እና ሰብአዊ ክብርን እያጣ ላለው መንግስት እና ማህበረሰብ ውድቀት ከሚያሳዩ በርካታ ምልክቶች አንዱ ነው”

በዋናነት እኛ ሄይቲያዊያን መደራጀት አለብን
“የቅዱስ አባታችን ጩኸት በመጀመሪያ እና ከሁሉም በላይ በሄይቲያዊያን ልብ ውስጥ መሰማት አለበት” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ “በሰላማዊ እና በፍትህ ላይ የተመሰረተ ውይይትን በማበረታታት ሀገራችንን በጋራ ፕሮጀክት ዙሪያ ማደራጀት በዋናነት የኛ ፋንታ ነው” ካሉ በኋላ፥ ሰላማዊ ውይይት እና ብሔራዊ ጉባኤ እንዲደረግ በቅድሚያ የጦር መሳሪያዎቹ ዝም ማለት እንዳለባቸው እና የወንጀል ተግባራት በይፋ መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

“ሰላማዊ ውይይት እና ብሔራዊ ጉባኤ እንዲደረግ በቅድሚያ የጦር መሳሪያዎች ዝም ማለት አለባቸው፣ የወንጀል ተግባራት በይፋ መቆም አለባቸው”

ሄይቲያዊያን ልማትን ከሚያደናቅፉ ተግባራት ነፃ መሆን አለባቸው
የሄይቲ ብፁአን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ቅዱስ አባታችን ላቀረቡት የሰላም ጥሪ በድጋሚ ምስጋናቸውን በማቅረብ፥ የሄይቲ ህዝብ ልማታቸውን ከሚያደናቅፉ ተግባራት እንዲቆጠቡ፥ በተለይም ከታጣቂ ቡድኖች ጥቃት፣ ከሀገር ወዳድነት ግንዛቤ ማነስ፣ ለስልጣን እና ለገንዘብ ከሚደረገው ከንቱ ትግል እግዚአብሔር እንዲጠብቃቸው ከቅዱስ አባታችን ጋር በጋራ እንጸልያለን ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ ሜሲዶር በመጨረሻም ‘ይህ የተስፋ ኢዮቤልዩ በሄይቲ የሚገኙትን የእግዚአብሔርን ልጆች እምነት እንዲያጠናክር፣ በእግዚአብሔር ላይ ያለው ተስፋ ፈጽሞ ስለማያሳፍር ይህ ኢዮቤልዩ ለሄይቲያዊያን የጸጋ እና የበረከት ጊዜ እንዲያደርግ’ ጸሎት በማድረግ አጠቃለዋል።

12 Aug 2025, 14:02