MAP

ፓትርያርክ ፒዛባላ ሃምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ከኢየሩሳሌም ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ሳልሳዊ ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ፓትርያርክ ፒዛባላ ሃምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ከኢየሩሳሌም ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ሳልሳዊ ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ  

ፓትርያርክ ፒዛባላ፡ 'በቅድስት ሀገር ውስጥ እንኳን ቢሆን ልባችን ሊለወጥ ይችላል’ አሉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ነሀሴ 16 የፆም ጸሎት ቀን እንዲሆን ካቀረቡት ጥሪ ቀደም ብሎ የኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ሰዎች ለመታመን እና መልካም ለማድረግ፣ የጋራ ጉዳዮችን ማግኘት በማይቻልበት በቅድስት ምድር እንኳን ጸሎት ያለውን ሃይል በማጉላት ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የሰዎች ልብ ሊለወጥ እንደሚችል ላላቸው የማያቋርጥ ትኩረት እና ተስፋ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የፆም ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡበት ነሐሴ 16 ዋዜማው የእመቤታችን የንግሥተ ሰማያት በዓል ሲሆን፥ ረቡዕ ዕለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በተለይም በቅድስት ሀገር እና በዩክሬን ላይ በማተኮር በትጥቅ ግጭቶች ምክንያት ለሚሰቃዩት ሰዎች “ሰላም እና ፍትህ” እንዲመጣ እግዚያብሄርን አጥብቀው እንዲለምኑ በዓለም ዙሪያ ያሉ ምእመናንን ጋብዘዋል።

ጸልዩ፣ ፁሙ እንዲሁም ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ
ፓትርያርክ ፒዛባላ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ብዙ ጊዜ ለሚያነሱት የሰላም ጭብጥ ያላቸውን ምስጋና አቅርበው፥ ይህ በጣም ርህራሄ የተሞላበት ሃሳብ ስለሆነ በእኛ ዘንድ ጥልቅ የሆነ ስሜት ተሰምቶናል ብለዋል።

“የፆም ጸሎት ቀናትን ለማሳለፍ እራሳችንን ስናዘጋጅ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም” ያሉት ፓትሪያርኩ፥ ቀደም ባሉት ጊዜያት በተመሳሳይ ሁኔታ መፈጸማቸውን አስታውሰው፥ በዚህ ጊዜ ማድረግ የምንችለው ብቸኛው ነገር ይህ እንደሆነ፥ ትኩረታችንን ወደ እግዚአብሔር ለማድረግ መጸለይ እና መጾም እንደሚገባ ካሳሰቡ በኋላ፥ “የሰዎች ልብ እንዲለወጥ አሁን ማድረግ የምንችለው ብቸኛው ነገር ይህ ነው” ብለዋል።

ጸሎት አስማታዊ ቀመር አይደለም
ፓትሪያርክ ፒዛባላ ጸሎት ችግሮችን የሚፈታ አስማታዊ ቀመር ተደርጎ መታመን እንደሌለበት አስጠንቅቀው፥ በዚህ መልኩ የሚደረግ ጸሎት መጨረሻው ወደ ተስፋ መቁረጥ እንደሚወስድ ያሳሰቡ ሲሆን፥ ከዚህ ይልቅ ጸሎት ልብን ለመለወጥ የሚረዳ መሳሪያ እንደሆነ፣ እንዲሁም በጦርነትና በሰላም እጦት የሚከሰተውን ጥላቻና ሌላውን የማግለል ዝንባሌ ወቅት ጸሎት ልብን ለመክፈት እንደሚያገለግል ገልጸዋል።

“ይልቁንስ ልባችን ሁል ጊዜ ለማመን፣ መልካም ማድረግን ለመሻት እና መልካም ነገርን ለመገንባት ክፍት መሆን አለበት” ያሉት ፓትሪያርኩ፥ በተለይም በቅድስት ሀገር በአሁኑ ጊዜ ሌላውን ሰው ለማወቅ በማይቻልበት ወቅት ይህ የጸሎት ጥንካሬ ነው ብለዋል።

የሰው ልብ ሊለወጥ ይችላል
ፓትርያርኩ በማከልም ፆም ጸሎት ማድረግ በሞትና በዓመፅ በተሞላ እና ሰላም የሚለው ቃል የጋራ መሠረታዊ ትርጉም በሌለው ቦታ ለሚኖሩ ሰዎች ብርታት እንደሚሰጣቸው ጠቁመው፥ ጸሎት በፖለቲካዊም ሆነ በሃይማኖታዊ ትላልቅ ተቋማት ውስጥ ምንም መሠረት እንዳላገኘ፥ ነገር ግን ይሄንን የቁልቁለት ጉዞ በማይቀበሉ በርካታ ሰዎች፣ እንቅስቃሴዎች፣ ቡድኖች፣ ማህበራት እና ግለሰቦች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ጸሎት ምንም እንኳን የተለያዩ ሁኔታዎች ቢኖሩም እና በቅድስት ምድር እንኳን ቢሆን አሁንም የሰው ልብ ሊለውጥ ይችላል ብለው ከሚያምኑ ከሁሉም የእምነት ተከታዮች ጋር ይህንን ትስስር ለመፍጠር እንደሚረዳ አስረድተዋል።

የጸሎት ጥንካሬ
በጋዛ በሚገኘው የቅድስት ቤተሰብ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ በደረሰው የቦምብ ጥቃት በኋላ ፓትሪያርክ ፒዛባላ ጋዛ የሚገኙ የክርስቲያን ማኅበረሰብን ጎብኝተው በሚመለሱበት ወቅት ከኢየሩሳሌም ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ 3ኛ ጋር ሆነው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት “የዓርብ የጸሎት ቀን ክርስቶስ ከጋዛ እንደማይለይ ያረጋግጥልናል” በማለት ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።

“ህብረተሰቡን ለመገንዘብ እንደቻልኩት ጥንካሬያቸው የሚመነጨው በትክክል ከጸሎት ነው ማለት እችላለሁ” ያሉት ፓትሪያርኩ፥ እነዛን አስከፊ ሁኔታዎች ለመቋቋም ጥንካሬ የሆናቸው ጸሎት እንደሆነ ጠቅሰው፥ በዚህ በተጀመረው ሥራ ላይ ምን እንደሚከሰት፣ እኛ ላይ፣ ጎረቤቶቻችን ላይ እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው ላይ ነገ ምን እንደሚፈጠር እና ምን ሊደርስ እንደሚችል በማናውቅበት ዋዜማ ላይ ነን ብለዋል።

ነገር ግን ችግሮችን ለመቋቋም፣ ሁሉንም ሰው ምግብ በማቅረብ እና መድሃኒት በማከፋፈል ለማገዝ ጥንካሬአቸውን ያገኙት ከጸሎት እና ጸሎት ብቻ ሊሰጠን ከሚችለው አንድነት መሆኑን አብራርተዋል።

በዕለተ አርብ የቅድስት ሀገር አማኞች ሰላም እንዲሰፍን እና የማያቋርጥ ስጋት እንዲያበቃ ለራሳቸው እና ለጎረቤቶቻቸው እንደሚጸልዩ ያስታወሱት ፓትርያርክ ፒዛባላ፥ በአሁኑ ወቅት ከክልሉ የሚገኘው መረጃ ግራ የሚያጋባ መሆኑን በመጥቀስ፥ ከእስራኤል መንግስት አከባቢውን ለቀው እንዲወጡ በቀጥታ የተላለፈ ትእዛዝ አለመኖሩን፥ ነገር ግን ጦርነቱ ወደ አካባቢያቸው እየተቃረበ መምጣቱን እና ቤተክርስቲያኗ አከባቢ የነበሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጸው፥ በአሁኑ ወቅት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለመረዳት እየተጠባበቁ እንደሆነ አብራርተዋል።

22 Aug 2025, 15:40