በኩዌት የምትገኘው የአረቢያ እመቤታችን ቤተክርስቲያን ወደ ‘ንዑስ ባሲሊካነት’ ከፍ ማለቱ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የሰሜን አረቢያ ሃዋሪያዊ አስተዳዳሪ የሆኑት ብፁእ አቡነ አልዶ ቤራርዲ ከቫቲካን ዜና ጋር በስልክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ በኩዌት አሕመዲ የሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ቤተ ክርስቲያን ወደ ‘ንዑስ ባሲሊካ’ ማዕረግ ከፍ ማለት በመቻሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ይህ ክብር በአሁኑ ጊዜ በባህረ ሰላጤው ዳርቻ ላይ ለምትገኘው እና በሀገሪቱ ውስጥ የመጀመሪያ ለሆነው ቤተክርስቲያን በይፋ እውቅና በመስጠት ያለውን ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ሃዋሪያዊ ሥራ አስፈላጊነትን እንደሚያጎላ ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት በሐዋርያዊ አስተዳደሩ ሥር የሚተዳደረው ይህ ቤተክርስቲያን የቆየ ደብር መሆኑን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ቤራርዲ፥ በኩዌት የነዳጅ ኩባንያ በነዳጅ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመሥራት ለሚመጡ ሰዎች በቀርሜላውያን ተነሳሽነት እ.አ.አ. በ 1948 ዓ.ም. እንደተገነባ እና ከሁለት ዓመት በፊት 75ኛ ዓመቱን እንዳከበሩ ገልጸዋል።
ለታላቅ መንፈሳዊ እና ሃዋሪያዊ ሥራ ጠቀሜታ ያለው ቤተክርስቲያን
ብጹዕነታቸው በዚህ ስፍራ ሁሉም ስደተኞች እና ወደ ሀገሪቱ ለመኖር ብሎም ለሥራ ለሚመጡ ሰዎች ሁሉ በእመቤታችን ጥበቃ ሥር ሆነው እምነታቸውን በነፃነት ሊለማመዱ ስለቻሉ እና ወደፊትም ስለሚያስችል ቤተክርስቲያኗ ትልቅ መንፈሳዊ ትርጉም እንዳላት አስረድተዋል።
እ.አ.አ. በ 1949 ዓ.ም. የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛን ቡራኬ በሮም ያገኘው እና በ2011 ዓ.ም. ብፁዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ካኒዛሬስ ሎቬራ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ስም የዘውድ አክሊል የደፉላት የአረቢያ እመቤታችን ሐውልት መገኛም ጭምር እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ ታላቅ አምልኮ ያለበት ቤተ መቅደስ መሆኑን ጠቁመው ይህም በመሆኑ ጥልቅ ታሪካዊ ሥረ መሠረቱን አጉልቶ ያሳያል ብለዋል።
በአብዛኛው ሙስሊም በሚበዛበት አካባቢ እንደዚህ አይነት ውክልናዎች በተከለከሉበት አካባቢ፣ የእመቤታችን ድንግል ማሪያም ሀውልት መኖሩ ትልቅ ተቀባይነት እንዳለው የገለጹት ብጹዕነታቸው፣ “ይህ ትልቅ ትርጉም ያለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ” ብለዋል።
የባህረ ሰላጤው የመጀመሪያው “ንዑስ ባሲሊካ”
የአረቢያ እመቤታችን በባህረ ሰላጤው አካባቢ የመጀመሪያዋ ንዑስ ባሲሊካ እንደሆነች የገለጹት ብጹዕ አቡነ አልዶ ቤራርዲ፥ ይህንን እውቅና ለማግኘት አስተዋፅኦ ላደረጉት ሁሉ፥ ከአካባቢው ባለስልጣናት ጀምሮ እስከ ከብዙ ዓመታት በፊት በህንፃው ግንባታ እና በማህበረሰቡ ውስጥ ለተሳተፉ፣ ይህንን ሥርዓተ አምልኮ በመጠበቅ እዚህ አከባቢ ለረጅም ጊዜ ሲያገለግሉ ለነበሩት ገዳማዊያት እና ገዳማዊያን፣ ለኩዌት እና የሰሜን አረቢያ ሐዋሪያዊ አስተዳደሮች፣ እንዲሁም ከሁሉም በላይ ለቅድስት መንበር ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል።
ይህች ቤተ ክርስቲያን ለአካባቢው ‘አበባ’ ናት ያሉት ብጹዕነታቸው፥ በኢራቅ እና በኩዌት መካከል በተካሄደው ጦርነትም ቢሆን የእመቤታችን ምስለ ሃውልት ለዚያች ትንሽዬ ቤተ ክርስቲያን እና በዚያን ጊዜ መሸሽ ላልቻሉት ሁሉ ጠባቂ ሆኖ እንደቆየ አስታውሰው፥ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የባህረ ሰላጤው ማለትም የሰሜን እና የደቡብ ሃዋሪያዊ አስተዳደሮች ጠባቂ እንደሆነች አስረድተዋል።
የሁለት ሚሊዮን ካቶሊኮች “ወጣት እና ሕያው” እምነት
ብጹዕ አቡነ አልዶ ቤራርዲ በገለጻቸው፥ የሰሜን አረቢያ ሐዋርያዊ አስተዳደር ባህሬን፣ ኳታር፣ ኩዌት እና ሳውዲ አረቢያን እንደሚያካትት አብራርተው፥ ከዚህም ባለፈ ከመላው ዓለም በተለይም ከፊሊፒንስ እና ህንድ የተውጣጡ ማህበረሰቦችን እንደሚያጠቃልል፥ ብሎም ከበርካታ የአፍሪካ እና የአውሮፓ ሃገራት ለሥራ የመጡ ስደተኞችን እንደሚጨምር ገልጸዋል።
ብጹዕነታቸው በማከልም፥ ‘የሁሉም የአምልኮ ሥርዓት ተከታይ ክርስቲያኖች በዚህ ስፍራ ስለሚገኙ እኛ የዓለም አቀፉ ቤተ ክርስቲያን መገለጫ ነን ማለት እንችላለን’ ያሉ ሲሆን፥ ሁሉም ማህበረሰቦች ከቋንቋቸው እና ከሥርዓተ አምልኮአቸው ጋር በጣም የተቆራኙ እንደሆኑ ጠቅሰው፥ የደቡብ ሃዋሪያዊ አስተዳደርን ሳይጨምር በሰሜናዊ ሃዋሪያዊ አስተዳደር ውስጥ ብቻ ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ የውጭ አገር ዜጎች የሆኑ ሁለት ሚሊዮን ካቶሊኮች እንዳሉ ገልጸዋል።
ነገር ግን በርካታ የሀገር ውስጥ ሰዎችም እንዳሉ እና ሌላው ቀርቶ በትውልድ የኩዌት ዜግነት የወሰዱ እንዳሉ አስታውሰው፥ በአጭሩ እዚህ ያለው ማህበረሰብ ህያው፣ ወጣት እና ታማኝ ማህበረሰብ እንደሆነ አብራርተዋል።
የወጣቶች ኢዮቤልዩ አከባበር
በሐምሌ ወር መጨረሻ እና በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓልን ለማክበር ከባህረ ሰላጤው ክልል ብዙ ወጣቶች እንደመጡ ያስታወሱት ብጹዕነታቸው፥ ለወጣቶቹ በአንድነት የተሰበሰበውን የመላው ቤተክርስትያንን ሥርዓተ አምልኮ ለመለማመድ ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ምንም እንኳን በቤተክርስቲያናቸው ውስጥ የአምልኮ ነፃነት ቢኖርም፣ ኩዌት ውስጥ እምነትን በአደባባይ ለመግለጽ የተወሰኑ ገደቦችን ማክበር ስላለባቸው፥ ወጣቶቹ ዘወትር ሊገኙ በማይችሉ የጸጋ እና የመካፈል ጊዜ እንዳሳለፉ ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት፣ ከዓለም ዙሪያ ካሉ ወጣቶች ጋር አብሮ መሆንና መጓዝ ለእነሱ በጣም አስፈላጊ እንደነበር አስታውሰው፥ በእምነታቸው እንዲጠነክሩ፣ በሰማዕታት ቦታ ጸሎታቸውን እንዲያሰሙ፣ በታሪካዊው ቅዱስ ክሪሶ-ጎኖ ባሲሊካ በተከናወነው የቅዱስ ቁርባን በዓል ላይ ለመሳተፍ እና በቶር ቬርጋታ እስፕላንዴ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር ሆነው የጸሎት እና ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ ለመሳተፍ እንደቻሉ ገልጸዋል።
ብጹዕነታቸው ወጣቶቹ ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ እ.አ.አ. በ 2027 ዓ.ም. በደቡብ ኮሪያ ለሚካሄደው የዓለም ወጣቶች ቀን በመዘጋጀት ላይ እንደሆኑም ጭምር አክለው ገልጸዋል።
ለማሪያም መሰጠት እና ትምህርተ ክርስቲያን ለልጆች
በተፈቀደላቸው ድንበሮች ውስጥ፥ በተለይም ችግር ላጋጠማቸው ሰራተኞች አነስተኛ የእርዳታ እና የድጋፍ ስራዎችን በማደራጀት እንደሚሳተፉ ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ቤራርዲ፥ እንደ ‘ካሪዝማቲክስ’ ያሉ ጠንካራ ተሳትፎ ያላቸው የንቅናቄ ቡድኖች፣ የማሪያን ማህበረሰቦች እና የሃይማኖታዊ ሥርዓቶች አባላት በአከባቢው እንዳሉ ጠቅሰው፥ ሁሉም ነገር የሚያጠነጥነው በሦስቱ መሰረታዊ ምሰሶዎች በሆኑት ሥርዓተ ቅዳሴ፣ የቅዱስ ቁርባን አምልኮ እና ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መሰጠት ላይ እንደሆኑ እና እነዚህም ከልጆች የትምህርተ ክርስቲያን ክፍለ ጊዜ እና የምዕመናን አገልጋዮች ምስረታ ጊዜያት ጋር እንደሚያያዙ አብራርተዋል።
ማዕረጉን የሚያሰጥ አዋጅ
ከሐዋርያዊ አስተዳደሩ የተሰጠው ማስታወሻ እንደሚገልጸው፥ በብጹዕ አቡነ ቤራርዲ የቀረበውን መደበኛ ጥያቄ ተከትሎ የመጣው ሥያሜን ከፍ የማድረግ አዋጅ ቁጥር 18/25 በኩዌት እና በመላው አረቢያ ባሕረ ገብ መሬት በሚገኙ የካቶሊክ ምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ የመሪነት ሚና በመገንዘብ እንደሆነ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ ይህ ውጤት በአህመዲ የአረቢያ እመቤታችን ቤተክርስቲያን የካህናት ሃዋሪያዊ ሥራ እና የቁምስናው የምዕመናን ምክር ቤት ፍሬ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ የካፑቺን ካህን የሆኑት አባ ሮስዊን ሬዴንቶ እና ቡድናቸው ለውጤቱ ወሳኝ የሆነውን አስፈላጊውን ሰነዶችን በማዘጋጀት መርዳታቸውን አስረድተዋል።
መግለጫው በማከልም የንዑስ ባሲሊካው ማዕረግ በቅዱስ አባታችን ፍቃድ በሥርዓተ አምልኮ እና በሃዋሪያዊ ሥራ ሕይወት ውስጥ ባላቸው ታሪካዊ፣ መንፈሳዊና ሥነ ሕንፃዊ እሴቶቻቸው ላይ ልዩ ጠቀሜታ ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት እንደሚሰጥ መግለጫው አክሎ ገልጿል።
ንዑስ ባሲሊካው ከሮማ መንበር እና ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር ልዩ ትስስር የሚኖረው ሲሆን፥ ከተሰጣቸው መብቶች መካከል የቁልፎቹን ምልክት በተለያዩ ዕቃዎቹ እና በሰንደቅ ዓላማዎቹ ላይ የማሳየት እንዲሁም ‘ኦምብሬሊኖ’ የተሰኘውን በአንድ ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን ከፀሐይ ለመከላከል ያገለግል የነበረውን ቀይ እና ወርቅማ ቀለም ያለው ጃንጥላ እንዲሁም ‘ቲንቲናቡለም’ የተሰኘውን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን መምጣት የሚያመላክት ዘንግ ላይ የተገጠመ ደወል የመያዝ መብት ይገኙበታል ተብሏል።
ብጹዕ አቡነ ቤራርዲ በመጨረሻም ‘በቅድስት መንበር እውቅና ማግኘታቸው ለሃዋሪያዊ አስተዳደሩ ታላቅ ክብር ብቻ ሳይሆን በአረብ ባሕረ ገብ መሬት ላሉ ሕዝቦች ሕያው እምነት ጥልቅ ማረጋገጫ’ እንደሆነ ጠቅሰው፥ የንዑስ ባሲሊካው አዋጅ የሚከበርበት ቀን በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ገልጸዋል።