የኢንዶኔዢያ ብጹዓ ጳጳሳት የእምነት ነፃነትን ለማስጠበቅ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የኢንዶኔዢያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በጃካርታ የሚገኘው ማዕከላዊ መንግሥት በሁሉም ዓይነት አለመቻቻሎች ላይ ቆራጥ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀው፥ በተለይ በሁከት ሲታጀብ ጥፋትን እንደሚያስከትል አስረድተዋል።
ፊደስ የተሰኘ የቫቲካን ዜና ወኪል እንደዘገበው፥ ካቶሊካዊ ጳጳሳት በማሳሰቢያቸው፥ “ማንም ሰው አሰቃቂ ድርጊቶችን ቢፈጽም በተለይም በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች የሚከናወኑ የጸሎት እና የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶችን ዒላማ ካደረገ ሳይቀጣ መቅረት እንደሌለበት አሳስበዋል።
ጳጳሳቱ በጉባኤያቸው በኩል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ በቅርቡ በአምልኮ ቦታዎች እና በቤተ ክርስቲያን ተቋማት ላይ ከተፈጸሙ ጥቃቶችን ጋር የተያያዘ ሲሆን፥ በፊርማ የቀረበው አቤቱታው በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ብቻ ሳይሆን በኢንዶኔዥያ የሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ምክር ቤት (MATAKIN)፣ በቡዳ እና በፕሮቴስታንት እምነቶች መካከል ያለውን አንድነት የሚያንፀባርቅ እንደሆነ ታውቋል።
የጋራ መግለጫው የሃይማኖት እና የአምልኮ ነፃነት ኢንዶኔዥያ ውስጥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1945 ዓ. ም. በተደነገገው ሕገ መንግሥት አንቀፅ 28 እና 29 የተረጋገጠ መሆኑን አስታውሶ፥ በአምልኮ ቦታዎች እና ተቋማት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የማይደገሙ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በሕግ አስከባሪ አካላት እና በአከባቢ ባለስልጣናት በኩል መንግሥት ግዴታ እንዳለበት አረጋግጧል።
የቅርብ ጊዜ ክስተቶች በበርካታ የክርስቲያን ማኅበረሰብ የአምልኮ ቦታዎች ላይ የደረሰውን ውድመት እና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ንብረት በሆነው ትምህርት ቤት የተካሄደውን ወረራ የሚያካትቱ እንደ ነበር ታውቋል። አቤቱታው ሕግ አስከባሪ እና የፍትህ አካላት እያንዳንዱን የሁከት፣ የእምቢተኝነት፣ የእንቅፋት ተግባራትን እና እንዲሁም የጸሎት ቦታዎችን ማውደም እንዲከላከሉ እና በጥልቀት እንዲመረመሩ ጠይቋል።
ለአቤቱታ አቅራቢዎቹ የሃይማኖት ነፃነትን ማስጠበቅ የሁሉንም ማለትም የመንግሥት ተቋማት፣ የሃይማኖት አንድነት መድረክ (FKUB) እና የጠቅላላ ኅብረተሰብ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ታውቋል።አቤቱታ አቅራቢዎቹ፥ የአምልኮ ቦታዎች ሁል ጊዜ “የሰላም፣ የጸጥታ እና የክብር ቦታዎች ሆነው እንዲቀጥሉ አጥብቀው በማሳሰብ የሃይማኖት መሪዎች ምእመናኖቻቸው በከፋፋይ ንግግሮች እንዳይቆጡ፥ ይልቁንም እምነታቸውን በሰላም፣ በስምምነት እና በመቻቻል እንዲኖሩት አሳስበዋል።
መግለጫው በማጠቃለያው፥ “እያንዳንዱ የጥቃት፣ የማዕቀብ ወይም የጸሎት ሥነ-ሥር ዓት መስተጓጎል በመቻቻል እና በሰላም አብሮ የመኖር ግንባታ ላይ ከባድ ጉዳት ነው” ሲል ገልጾ፥ ማንኛውም የማስፈራራት፣ የኃይል እርምጃ ወይም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችን መገደብ ሕግን የሚጻረር እና የአንድ አገር ዜጎች በጋራ የመኖር መሠረታዊ እሴቶችን የሚጎዳ ነው” ሲል አስገንዝቧል።