በእግዚአብሔር አብ አምናለሁ
የእምነት ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የእምነት ምልክቶች ወይም “የእምነት መግለጫዎች” ወይም “የሃይማኖት ጸሎቶች” የሚባሉት ስብስብ ቀመሮች ሲሆኑ እነርሱም ቤተክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ በአንድነት የገለጸቻቸውና ለምእመናን ሁሉ በሚገባ መደበኛ ቋንቋ የራስዋን እምነት ያስተላለፈችባቸው ናቸው፡፡
ከሁሉም ጥንታዊ የሆኑ የእምነት ምልክቶች (መግለጫዎች) የትኞቹ ናቸው?
ከሁሉም ጥንታዊ የሆኑ የእምነት ምልክቶች የጥምቀት ጸሎቶች ናቸው፡፡ ጥምቀት የሚሰጠው “በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም” (ማቴ. 28፣19) ስለሆነ በጥምቀት ጊዜ የተገለጹ የእምነት እውነቶች በቅድስት ሥላሴ ሶስቱ አካላት ስም የተነገሩ ናቸው፡፡
ከሁሉ የሚበልጡ የእምነት ምልክቶች የትኞቹ ናቸው?
ከሁሉ የሚበልጡ የእምነት ምልክቶች የሐዋርያት ጸሎቶች ናቸው፡፡ እነርሱም በኒቂያ (እ.ኤ.አ. 325 ዓ.ም.) እና በቁስጥንጥንያ (እ.ኤ.አ. 381 ዓ.ም.) በተካሄዱት የመጀመሪያዎቹ ሁለት የክርስቲያኖች አንድነት ጉባኤዎች የመነጩ የሮማ ቤተክርስቲያንና የኒቂያና የቁስጥንጥንያ ጸሎተ ሃይማኖት ጥንታዊ የጥምቀት ምልክት ናቸው፡፡ እነርሱም እስከ ዛሬም ድረስ ለምሥራቅና ለምዕራብ ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የጋራ ምልክቶች ናቸው፡፡ “ሁሉን በሚችል፣ ሰማይና ምድርን በፈጠረ በእግዚአብሐር አብ አምናለሁ፡፡”
የእምነት መግለጫ “በእግዚአብሔር አምናለሁ” በሚሉ ቃላት የሚጀምረው ለምንድ ነው?
የእምነት መግለጫ በእነዚህ ቃላት የሚጀምርበት ምክንያት “በእግዚአብሔር አምናለሁ” የሚለው ማረጋገጫ ስለ ሰው እና ስለ ዓለም፣ በእግዚአብሐር ስለሚያምነው ሰው ሕይወት በሙሉ ላሉ ሌሎች እውነቶች ሁሉ ምንጭ የሆነ እጅግ አስፈላጊ ነገር ስለሆነ ነው፡፡
ሰው እግዚአብሔር አንድ ነው የሚለውን እምነቱን መግለጽ ያለበት ለምንድነው?
ሰው በአንድ እግዚአብሐር ማመኑን የሚገልጽበት ምክንያት እግዙአብሐር ራሱ አንድ ብቻ መሆኑን ለእስራኤል ሕዝብ ሲናገር “እስራኤል ሆይ፣ ስማ፣ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአበሐር ነው” (ዘጸ. 6፡4) እና “ሌላ አምላክ የለም” (ኢሳ. 45፡22) በማለት ራሱን ስለገለጸ ነው፡፡ እግዚአብሔር “አንድ ጌታ” (ማር. 12፡29) መሆኑን ኢየሱስ ራሱ አረጋግጦአል፡፡ ኢየሱስና መንፈስ ቅዱስም አምላክና ጌታ ናቸው ብሎ ማመን አንድ እግዚአብሔርን መለያየት አይሆንም፡፡
እግዚአብሔር ራሱን የገለጸው በምን ስም ነው?
እግዚአብሔር ሕያው አምላክ ለመሆኑ ራሱን ለሙሴ ሲገልጽ፣ “የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ” (ዘጸ. 3፡6) ሲል ተናገረ፡፡ እግዚአብሔር ምስጢራዊ ስሙን ደግሞ ለሙሴ ሲናገር “እኔ ነኝ (ያሕዌ ነኝ) አለ፡፡ ያኔ በብሉይ ኪዳን ዘመን ይህ በቃላት ሊገለጽ የማይችል የእግዚአብሔር ስም ጌታ በሚለው መለኮታዊ ስያሜ ተተካ፡፡ ስለዚህ፣ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጌታ እየተባለ የሚጠራው ኢየሱስ እንደ እውነተኛ አምላክ ተቆጠረ።
“ያለና የሚኖር” እግዚአብሐር ብቻ ነው?
ፍጥረታት ህልውናቸውን ያገኙት ከእግዚአብሐር ሲሆን፣ በራሱ ምሉዕና ፍጹም የሆነው እግዚአበሐር ብቻ ነው፡፡ እግዚአበሐር “ያለና የሚኖር” መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ነው፡፡ ኢየስስ ደግሞ “እኔ ነኝ” (ዮሐ. 8፡28) የሚል መለኮታዊ ስም እንዳለው ገለጸ፡፡
የእግዚአብሔር ስም መገለጥ ያስፈለገው ለምንድነው?
ስሙን በመግለጽ፣ እግዚአብሐር በቃላት ሊገለጽ በማይችለው በርሱ የሕልውና ምስጢር ውስጥ ያለውን ሀብት ያሳውቃል፡፡ እርሱ ብቻ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይኖራል፡፡ ከዓለምና ከታሪክ በላይ ልቆ የሚገኘው እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሰማይና ምድርን የፈጠረ እርሱ ነው፡፡ እርሱ ሊያድናቸው ሁልጊዜ ከሕዝቡ አጠገብ የሚገኝ ታማኝ አምላክ ነው፡፡ እርሱ ፍጹም ጻድቅ፣ “ምህረቱ የበዛ” (ኤፌ.2፡4) ዘወትር ለይቅርታ ዝግጁ የሆነ ነው፡፡ መንፈሳዊ፣ ከሁሉ የላቀ፣ ሁሉን ቻይ፣ ዘለዓለማዊ ግላዊ እና ፍጹም አምላክ ነው፡፡ እርሱ እውነትና ፍቅር ነው፡፡
“እግዚአብሔር ቅድስት ሥላስ የሆነ ወደር የማይገኝለት ፍጹም ሕልው ነው” (ቅዱስ ቱሪቢዬስ ዘሞንተኔግሮ)።
እግዚአብሔር እውነት የሆነው እንዴት ነው?
እግዚአብሔር ራሱ እውነት ስለሆነ ሊያታልልም ሊታለልም አይትልም፡፡ እርሱ “ብርሃን ነው፣
በእርሱ ውስጥ ጨለማ የለም” (1ኛ ዮሐ.1፡5)፡፡ የጥበብ ምሳሌ የሆነው የእግዚአበሐር ዘለዓለማዊ ልጅ “እውነትን ይመሰክር ዘንድ” ወደ ዓለም ተላከ (ዮሐ. 18፡37)፡፡
እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን እንዴት ይገልጻል?
ወላጆች ለልጆቻቸው ወይም ባሎች እና ሚስቶች ለትዳር ጓደኞቻቸው ካላቸው ፍቅር የበለጠ ፍቅር እንዳለው እግዚአብሐር ስለራሱ ለእስራአል ሕዝብ ገለጸ፡፡ እግዚአብሔር በራሱ “ፍቅር ነው” (1ኛ ዮሐ. 4፡8.16)፡፡ እርሱ ራሱን ሙሉ በሙሉና በልግስና አሳልፎ ይሰጣል፡፡ “ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሣ ዓለም በእርሱ ይድን ዘንድ አንድያ ልጁን ሰጠ” (ዮሐ. 3፡16-17)፡፡ ልጁንና መንፈስ ቅዱስን በመላክ እግዚአብሔር ራሱ ዘላለማዊ የፍቅር ለውጥ መሆኑን አሳየ፡፡
በአንድ አምላክ ማመን ማለት ምን ማለት ነው?
በአንድና በአንድ እግዚአብሔር ብቻ ማመን የእርሱን ታላቅነትና ግርማ ሞገስ ማወቅን፣ በመከራ ጊዜ እንኳ ሳይቀር በምስጋናና ዘወትር በእርሱ በመታመን መኖርን፣ በእርሱ አምሳል የተፈጠሩ ሰዎችን ሁሉ አንድነትና እውነተኛ ክብር ማወቅን፣ በእርሱ የተፈጠሩትን ነገሮች በሙሉ በአግባቡ መጠቀምን ያካትታል፡፡
የክርስቲያናዊ እምነትና ሕይወት ማእከላዊ ምስጢር ምንድነው?
የክርስቲያናዊ እምነትና ሕይወት ማዕከላዊ ምስጢር የቅድስት ሥላስ ምስጢር ነው፡፡ ክርስቲያኖች የተጠመቁት በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡
NJͭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዩሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ካጸደቁት፣ በአጭሩ ከተጻፈው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ከዋናው ከላቲን ቅጂ ከተተረጎመው መጽሐፍ ከአንቀጽ 185-226 ላይ የተወሰደ።