አባ ሮማኔሊ የጋዛ ክርስቲያኖች ስቃይ እየደረሰባቸው ከሚገኙ ፍልስጤማዊያን ጎን እንደሚቆሙ ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በጋዛ ሰርጥ የምትገኘው የቅድስት ቤተስብ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ካህን የሆኑት አባ ሮማኔሊ እና ሌሎች ገዳማዊያት እና ገዳማዊያን ‘በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙትን አረጋውያንን እና ህሙማንን’ ማገልገላቸውን እንደሚቀጥሉ ለቫቲካን ዜና የገለጹ ሲሆን፥ አባ ገብርኤል ሮማኔሊ ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩት “እኛ በጌታ እጅ ላይ ነን፥ በመሆኑም በዓለም ዙሪያ ባሉ በርካታ መልካም ሰዎች እርዳታ ይህ ጦርነት እንደሚቆም እናምናለን” ብለዋል።
አባ ሮማኔሊ በጋዛ ብቸኛው የካቶሊክ ደብር ውስጥ የተሰበሰቡት በሙሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመልካም ሥራ በኩል ሊያገለግሉት እዚያ እንደሚገኙ ገልጸው፥ ‘ሁላችንም በድሆች፣ በሕሙማን እና ስቃይ ውስጥ በሚገኙት አማካይነት ጌታችንን እናገለግላለን’ ብለዋል።
ትውልደ አርጀንቲናዊው ካህን አባ ሮማኔሊ እና በግቢው ውስጥ አብረዋቸው ያሉት ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ጌታ የጠየቃቸው ይህንኑ በመሆኑ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ከሚገኙት ጎን ለመቆም እና “ሁሉንም ሰው ለማገልገል” መምረጣቸውን የገለጹ ሲሆን፥ በደብሩ ውስጥ ከአባ ሮማኔሊ በተጨማሪ የ ‘ኢንስቲትውት ኦፍ ኢንካርኔት ዎርድ’ ካህናት እና እህቶች እንዲሁም የበጎ አድራጎት ሚስዮናውያን አባላት እንዳሉ ተገልጿል።
“ሁላችንም አንድ አይነት ስሜት እንጋራለን” ያሉት አባ ሮማኔሊ፥ ‘የአረጋውያንን፣ የተጨነቁትን፣ የተሸበሩትን፣ ያዘኑትን እና የአካል ጉዳተኞችን ፍላጎት ስንመለከት ጌታ ማገልገላችንን እንድንቀጥል እየጠራን እንደሆነ እንረዳለን’ ያሉ ሲሆን፥ ይህ ካልሆነ በስተቀር እነዚህ ሰዎች ሊተርፉ እንደማይችሉ አስረድተዋል።
ጦርነቱ እንዲቆም እና ሰላም እንዲሰፍን ጸልዩ
የቁምስናው ካህን እና የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች ማክሰኞ ዕለት በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ እና በኢየሩሳሌም የግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ሣልሳዊ በጋራ ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ የተቀላቀሉ ሲሆን፥ አባ ሮማኔሊ እንዳሉት እሳቸው እና ሁሉም በጋዛ ደብር ውስጥ የሚገኙ ሰዎች “ስለ ሰላም፣ ነፃነትን ለተነጠቁት ሁሉ፣ ለታጋቾች፣ በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ ህሙማን እና በጋዛ ሰርጥ ውስጥ በየትኛውም ቦታ ህክምና እና የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ ማግኘት ላልቻሉ የቆሰሉ ሰዎች መጸለያቸውን አጠናክረው እንደቀጠሉ ገልጸዋል።
ውድመት፣ ሞት እና የአካል ጉዳት
በተለይ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በጋዛ ከተማ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን፥ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ወታደራዊ ዘመቻዎች እና የቦምብ ጥቃቶች ተባብሰው መቀጠላቸው ከአከባቢው የሚወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ።
አባ ሮማኔሊ እነዚህ ዘመቻዎች ተጨማሪ ሞት፣ ውድመት እና ቁስለኛ ማስከተላቸውን ገልጸው፥ እነዚህ ሁሉ ክስተቶች ሁሉም ሰው መጪው ጊዜ ምን እንደሚፈጠር ማወቅ እንዳይችል ያደረገ አጠቃላይ ሁኔታ እንደሆነ፥ ብሎም ጦርነቱ እንደሚቀጥል እና ቀጣዩ ደረጃ በቀጥታ በጋዛ ከተማ ላይ ጦርነት ሊሆን እንደሚችል አሳስበዋል።
ይህም በመሆኑ ሁሉም ሰው ግጭቱ እንዲቆም እና ሰላም እንዲሰፍን ጸሎት ማድረግ እንደሚገባ የጋበዙት አባ ሮማኔሊ፥ በአከባቢው ህዝቡን በታላቅ አክብሮት እና ትህትና ማገልገላቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸው፥ ውሳኔው ቀላል ባይሆንም ነገር ግን በጌታ እጅ ላይ እንደሆኑ እና በዓለም ላይ ባሉ በርካታ መልካም ሰዎች እርዳታ ይህ ሁሉ አንድ ቀን እንደሚቆም ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ አጠቃለዋል።