አባ ሮማኔሊ በጋዛ የሚገኘው የካቶሊክ ደብር እስራኤል ባስተላለፈችው ለቆ የመውጣት ትእዛዝ ሥር እንዳልገባ አሳወቁ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
“በቤተክርስቲያናችን እና በአቅራቢያው ምንም አይነት የመልቀቂያ ትእዛዝ አልተላለፈም” ያሉት አባ ገብርኤል፥ አካባቢው በአሮጌው የጋዛ ከተማ በትልቁ የዘይቱን ሰፈር ውስጥ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በጋዛ የሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የቅድስት ቤተሰብ አጥቢያ ካህን የሆኑት አባ ገብርኤል ሮማኔሊ ማክሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2017 ዓ.ም. ለቫቲካን መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ አካባቢው አደገኛ እና ሌት ተቀን ለቤተክርስቲያኑ በቅርብ ርቀት፣ አንዳንዴም ከሩቅ አከባቢ የቦምብ ፍንዳታ እንደሚሰማ ጠቅሰው፥ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የቦንብ ፍንጣሪዎች ሳይቀሩ አከባቢያቸው ላይ እንደሚወድቁ አስረድተዋል።
እንደ አለመታደል ሆኖ ጦርነቱ በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠሉን የገለጹት ካህኑ፥ በየቀኑ የሚሞቱ፣ የሚቆስሉ እና የውድመቱ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው፥ በዚህም ምክንያት አጠቃላይ የሲቪሉ የጋዛ ህዝብ ፍላጎት በየዕለቱ ከፍ እንደሚል በመጠቆም፥ “ሆኖም ግን እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነን” ካሉ በኋላ “ስለ ሰላም መጸለያችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” በማለት ደምድመዋል።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ በርካታ ሰዎች በጋዛ በምትገኘው ብቸኛዋ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተጠልለው እንደሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን፥ ሃምሌ 10 በቤተክርስቲያኑ አቅራቢያ በደረሰው የታንክ ጥቃት ሶስት ሰዎች መሞታቸው እና በርካቶች ደግሞ መቁሰላቸውን እንዲሁም አባ ሮማኔሊ እግራቸው በአደጋው መቁሰሉ ይታወሳል።
ይህ ጥቃት በደረሰበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ‘አስከፊው ጦርነት’ በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ ካቀረቡ በኋላ፥ ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንደሚፈታ ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ ለተጎጂዎች መጸለያቸው ይታወሳል።