የሄይቲ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በአገሪቱ ያለው ደም መፋሰስ እና ስጋት እንዲቆም ተማጸነች
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“በአገሪቱ ውስጥ በሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ የነበሩ አንድ የአየርላንድ ሚስዮናዊ እና አንድ የአካል ጉዳተኛ አዳጊ ሕጻንን ጨምሮ በዘጠኝ ግለሰቦች ላይ የተፈጸመው የአፈና ተግባር አዲስ አረመኔያዊ ድርጊት፣ አሳፋሪ ተግባር እና መላውን የሄይቲ ማኅበረሰብ እያዳረሰ የሚገኝ የሞራል ውድቀት ነው” ሲል መግለጫው ገልጿል።
የፖርት ኦ-ፕሪንስ ሀገረ ስብከት ይህን ተግባር ያወገዘው በዋና ከተማዋ ደቡብ ምሥራቅ በሚገኝ የቅድስት ሄለን የሕፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ሐምሌ 27/2017 ዓ. ም. በሰጠው መግለጫ ነው። ቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመናኑ በጸሎት በርትተው ተጨባጭ ሰብዓዊ ዕርዳታን በማቅረብ የተቋማቱን ሥርዓት፣ ደህንነት እና ፍትህ እንዲያረጋግጡ ጥሪዋን አቅርባለች።
ብጥብጥ እና በኅብረተሰቡ ላይ የሚፈጸም ጥቃት
የተፈጸመው አፈና በማኅበረሰቡ መልካም ገጽታዎች ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው” ያለው የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት መግለጫ፥ ከራስ ወዳድነት ነፃ ሆኖ ሌሎችን መንከባከብ፥ ንፁሃን ልጆችን መጠበቅ እና በእምነት የታገዙ በጎ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ አሳስቧል። ሁከቱ በቀጥታ የሚጎዳው በዋና ከተማዪቱ ውስጥ በምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ብቻ ሳይሆን የዜጎችን አብሮ የመኖር ባሕል እና የሰብዓዊ ክብር መሠረትን የሚጎዳ መሆኑን መግለጫው አስታውቋል።
መግለጫው በማከልም፥ እንደነዚህ ያሉት ወንጀሎች መንግሥት እና ኅብረተሰቡ ለሕይወት ያላቸውን ተቆርቋሪነት ማጣታቸውን የሚያሳይ እንደሆነ አጽንዖት በመስጠት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጾ፥ “የማይታሰብ ነገር መደበኛ እየሆነ በመጣበት፣ የተቸገሩትን ለመንከባከብ ለትምህርት እና ለመጠለያነት የተቋቋሙ ቦታዎች ዒላማ እየሆኑ በመጡበት ወቅት የእየተባባሰ የመጣው ደም መፋሰስ እና ስጋት የማስጠንቀቂያ ድምጽ ነው” ሲል ገልጿል።
የኃላፊነት ተማጽኖ
ቤተ ክርስቲያኒቱ የሁኔታውን አሳሳቢነት በመገንዘብ፥ ለመላው ማኅበረሰብ ባቀረበችው ጥሪ፥ “ምእመናን እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በሙሉ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ፣ በጸሎት እንዲተባበሩ እና ሰብዓዊ ክብርን የሚያጎድፍ ተግባርን ውድቅ በማድረግ እርምጃን እንዲወስዱ ግብዣዋን አቅርባ፥ ሲቪሉ ማኅበረሰብ፣ ወታደራዊ እና የፖሊስ ኃይሎች ሃላፊነት እንዲወስዱ፥ የሕዝቡን ደህንነት እንዲያረጋግጡ እና የታሰሩት ግለሰቦች በአስቸኳይ እንዲፈቱ አሳስባለች። የቤተ ክርስቲያኒቱ መግለጫ በተጨማሪም፥ “የሄይቲ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በደም መፋሰስ እና በፍርሃት ሊገነባ እንደማይችል በማስረዳት፥ በኅብረት ሆነን በቃ የሚባልበት እና እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ አሁን ነው” ሲል በግልጽ ተናግሯል።
ግዴለሽነት እና ሰብዓዊ ቀውስ
ቤተ ክርስቲያኒቱ በመግለጫው ማጠቃለያ፥ በግዴለሽነት እና በውስጥ አለመግባባቶች ውስጥ መውደቅ እንደማይገባ በማስጠንቀቅ፥ ግድየለሽነት ለተጎጂዎች ያለውን ተቆርቋሪነት በማስወገድ በሀገሪቱ ላይ በሚደርስ ጥፋት ተባባሪ የሚያደርግ መሆኑን አስረድታለች።
በሄይቲ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ቢሮ ባወጣው ዘገባ፥ በሚያዝያ እና ሰኔ ወር መካከል ቢያንስ 185 አፈናዎች መመዝገባቸውን ገልጾ፥ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ሁከት በሺህዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የሞት አደጋን፣ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ መፈናቀልን እንዳስከተለ፣ በረጅም ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ በምትገኘው ሄይቲ ያለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው” ሲል ገልጿል።