MAP

የጉድ ሼፐርድ ገዳማዊያት ማህበር አባል የሆኑት እህት አንቶኔት አሳፍ በሊባኖስ ሩይሳት በሚገኘው የቅዱስ አንቶኒ ማህበረሰብ ጤና ጣቢያ ውስጥ ታካሚ ህፃን ይዘው የጉድ ሼፐርድ ገዳማዊያት ማህበር አባል የሆኑት እህት አንቶኔት አሳፍ በሊባኖስ ሩይሳት በሚገኘው የቅዱስ አንቶኒ ማህበረሰብ ጤና ጣቢያ ውስጥ ታካሚ ህፃን ይዘው   (Raghida Skaff - CNEWA)

የአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ ቢቋረጥም የቤተ ክርስቲያን ቡድኖች በመካከለኛው ምስራቅ ማገልገላቸውን ቀጥለዋል

ምንም እንኳን ዩናይትድ ስቴትስ ለውጭ ሃገራት የምታደርገው የዕርዳታ ገንዘብ በእጅጉ ቢቀንስም፣ የካቶሊክ የረድኤት ድርጅቶች በመካከለኛው ምሥራቅ ለተቸገሩ ማህበረሰቦች ሰብዓዊ ዕርዳታ እያቀረቡ እንደሆነ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከቤይሩት በስተሰሜን 6 ማይል ርቀት ላይ በሚገኘው የቅዱስ አንቶኒ ማህበረሰብ ጤና ጣቢያ መግቢያ ላይ “ዩኤስኤአይዲ - ከአሜሪካ ህዝብ - ዓለም አቀፍ የህክምና ጓድ” የሚል ጽሁፍ ቢኖርም፥ በቅነሳው ምክንያት ከአሁን በኋላ ተግባራዊ የማይሆን ጽሁፍ እንደሆነ ይታወቃል።

ጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም. የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ሁሉንም የመንግስት የውጭ ዕርዳታዎች ለሶስት ወራት ያክል እንዲታገድ የስራ አስፈፃሚ ትዕዛዝ መስጠቱ የሚታወስ ሲሆን፥ ትዕዛዙ “የውጭ ዕርዳታ ኢንዱስትሪ እና ቢሮክራሲ ከአሜሪካውያን ፍላጎት ጋር የማይጣጣሙ እና በብዙ ሁኔታዎች ከአሜሪካ እሴቶች ጋር የሚቃረኑ ናቸው” ከሚል መግለጫ ጋር ተያይዞ መውጣቱ ይታወሳ።

በሺዎች ለሚቆጠሩ የሰብአዊ ፕሮጄክቶች አስፈላጊ የሆነው የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ በድንገተኛ ሁኔታ መቋረጥ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ኤጀንሲዎችን እና ተጠቃሚዎቻቸውን ያስደነገጠ ሲሆን፥ በ 2016 ዓ.ም. የአሜሪካ የውጭ ዕርዳታ በዓለም ዙሪያ በአጠቃላይ 56 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ተገልጿል።

ይህ የአሜሪካ መንግስት ድንገተኛ ውሳኔ የቅዱስ አንቶኒ ማህበረሰብ ጤና ጣቢያን በፍጥነት የደረሰ ሲሆን፥ በመልካም እረኞች ገዳማዊያት ማህበር እህቶች የሚተዳደረው ማዕከሉ ከ 2000 ዓ.ም. ጀምሮ የአሜሪካ መንግስት ለጤና ጣቢያው የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ሲመራው ከነበረው ዓለም አቀፍ የህክምና ኮርፖሬሽን የሥራ ማቆም ትእዛዝ መቀበሉ ተገልጿል።

ይሄንን ድንገተኛ ውሳኔ አስመልክተው የህክምና ማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ጆኤሌ ካሊፍ እንደተናገሩት፥ “በአንድ እሁድ ምሽት ከሰኞ ጀምሮ ለምክር አገልግሎቱ፣ ለደም ምርመራ፣ ለመድሀኒቶች እና ለህክምና ቁሳቁሶች የሚሆነውን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያቆሙ የሚገልጽ መልዕክት ልከውልናል” ሲሉ ተናግረዋል።

መጀመሪያ ላይ፣ ዓለም አቀፉ ሜዲካል ኮርፖሬሽኑ የጤና ጣቢያውን ዓመታዊ በጀት አንድ ሶስተኛውን የሚሸፍነውን የገንዘብ ድጋፍ ማቆሙን ያስታወሱት ዳይሬክተሯ፥ “ከሁለት ሳምንታት በኋላ ቡድኑ ከእኛ ጋር የነበረው ውል መቋረጡን በትህትና ገልፀውልናል” ሲሉ ተናግረዋል።

“ዓለም አቀፉ ሜዲካል ኮርፖሬሽን ይሸፍነው የነበረውን ወጪ ታካሚዎቻችንን ማስከፈል ስንጀምር አንዳንዶቹ መምጣት አቆሙ” ሲሉ በየወሩ ከ 2,000 ሰዎች በላይ ለሚሆኑ ሰዎች አገልግሎት ለሚሰጠው ጤና ጣቢያው ይህ ውሳኔ የሚያስከትለውን መዘዝ ያስረዱት ዶክተር ካሊፍ፥ ታካሚዎቻቸው ወደ እነሱ የሚመጡት በግል ሆስፒታሎች ውስጥ የጤና አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል የገንዘብ አቅም ስለሌላቸው እንደሆነ አክለው ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የተወሰነው ውሳኔ እንዴት የጤና እንክብካቤ ወጪዎቻቸውን እንደማይሸፍኑ ለታካሚዎቻቸው ማስረዳት ከባድ እንደ ነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሯ፥ ሆኖም ግን ጌታ ከእነሱ ጋር እንደሆነ እና በዚህ የገንዘብ ድጋፍ ችግር ምክንያት ማዕከላቸውን እንደማይዘጉ አስታውቀዋል።

በሊባኖስ ለማህበረሰባቸው ዓለም አቀፍ ድጋፎችን የሚያስተባብሩት ሌላኛዋ የጉድ ሼፐርድ እህት አንቶኔት አሳፍ በበኩላቸው ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጀምሮ የገንዘብ አቅርቦት ተደራሽነት “በጣም ከባድ” እንደነበር አስታውሰው፥ እነዚህ ቅነሳዎች ቀድሞውኑ የነበሩትን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን የበለጠ ፈታኝ እንዳደረጉት ገልጸዋል።

በመጋቢት ወር አጋማሽ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ 83 በመቶው የዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ. ውሎች መሰረዛቸውን እና የተቀሩት ደግሞ በየካቲት ወር ወደ ስቴት ዲፓርትመንት መቀላቀላቸውን አስታውቀው የነበረ ሲሆን፥ ሆኖም ከአንድ ወር በኋላ እንኳን የተቋረጡ የገንዘብ ድጋፎች የመጨረሻ ዝርዝር ይፋ አልተደረጉም ነበር።

ሆኖም ግን ‘ጄኔቫ ሶሉሽንስ’ የተሰኘው የዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶችን ሥራ የሚዘግበው የድህረ ገጽ የዜና ማሰራጫ ጣቢያ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም. እንደዘገበው 77 በመቶው የዩኤስኤአይዲ እርዳታ ወይም የ36 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ መቋረጡን ዘግቧል።

በዚህ ዝርዝር ውስጥ የዓለም ጤና ድርጅት፣ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም፣ ሜርሲ ኮርፕስ እና ዩኒሴፍ ከዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የሚያገኙትን የገንዘብ ድጋፍ ከአንድ ሶስተኛ እስከ 98 በመቶ ያጣሉ ተብሏል።

ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ አስተዳደሩ ጥቂት ቅነሳዎችን በማጤን ሚያዝያ 1 ላይ የዓለም የምግብ ፕሮግራም በሊባኖስ፣ በሶሪያ፣ በኢራቅ፣ በዮርዳኖስ፣ በኢኳዶር እና በሶማሊያ ላሉት ፕሮጀክቶቹ የተወሰኑ የገንዘብ ድጋፎችን ማድረጉ ይታወሳል።

ከእነዚህም ተቋማት በተጨማሪ የክርስቲያን ድርጅቶች ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖው ማሳደሩ የተነገረ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሰብአዊ እና የልማት ድርጅት ካሪታስ ከዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ከሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ 25 በመቶውን፣ እንዲሁም ወርልድ ቪዥን 16 በመቶ እንዲያጣ ታቅዶ እንደ ነበር ተገልጿል።

በቤይሩት በሚገኘው የቅዱስ ዮሴፍ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ፣ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች እና የዓለም አቀፍ ሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ካሪም ኤል-ሙፍቲ እነዚህ የልማት ዕርዳታዎች እና ዓለም አቀፍ ትብብር ላይ የሚደረጉ የበጀት ቅነሳዎች የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ልማትን እንደሚጎዳ ጠቅሰው፥ በተለይም ስደተኞችን እና ሌሎች ተጋላጭ ቡድኖችን የሚደግፉ ፕሮግራሞችን በእጅጉ እንደሚጎዳ አሳስበዋል።

ይህ የአሜሪካ ፖሊሲ ለውጥ በአሜሪካ እርዳታ በኩል በዓለም አቀፍ እና በመካከለኛው ምስራቅ በሚሰሩት ሥራዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር የገለጹት ፕሮፌሰሩ፥ ከእነዚህም ውስጥ በጦርነት የፈራረሰችው እና በውጪ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ የሆነችው ሊባኖስ አንዷ እንደሆነች እና ሃገሪቷ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ትግል ላይ እንደሆነች ጠቅሰው፥ በዩናይትድ ስቴትስ የሚደገፉት ፕሮግራሞች በጤና አጠባበቅ፣ በትምህርት እና በመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ረገድ በጣም ጠቃሚ እንደነበሩ አስረድተዋል።

እ.አ.አ. በ 2024 ዓ.ም. ሃገሪቷ በደቡብ እና ቤቃ ሸለቆ ውስጥ ብቻ ተወስኖ ከነበረው ጦርነት፣ ኃይለኛው የሊባኖስ የፖለቲካ ፓርቲ እና የሺዓ ሚሊሻ የሆነው ሂዝቦላ ከእስራኤል ጋር ወደ ሚያካሂደው ሁሉን አቀፍ ጦርነት እንደገባች የሚታወቅ ሲሆን፥ በዚያው ዓመት ሊባኖስ 63 በመቶው ለኢኮኖሚ ልማት እና የተቀረው የገንዘብ እጥረት ላለበት ወታደራዊ ኃይል ድጋፍ የሚውል ወደ 390 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የአሜሪካ ዕርዳታ መቀበሏ ተገልጿል።

ዩናይትድ ስቴትስ ከዚህም በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታት በአገሪቱ ውስጥ ላሉት አጠቃላይ ፕሮጀክቶች 20 በመቶውን የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

በሊባኖስ፣ ሶሪያ እና ግብፅ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት የበጎ አድራጎት ማህበር (CNEWA) የክልል ዳይሬክተር የሆኑት ሚሼል ኮንስታንቲን እንደተናገሩት፥ በሊባኖስ ውስጥ በተቋማቸው ከሚደገፉት 100 ፕሮጀክቶች ውስጥ እስካሁን ድረስ የቅዱስ አንቶኒ ማህበረሰብ ጤና ጣቢያ እና ሌላ የሕክምና ማእከል በቀጥታ በቅነሳዎቹ መጎዳታቸውን ገልጸው፥ ሆኖም ከጥር ወር ጀምሮ ሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶች “በገንዘብ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት” ወደ ቢሮአቸው እንደመጡ አስታውሰዋል።

አቶ ሚሼል አክለውም የዚህ ዓመት በጀታቸው አስቀድሞ ስለተጠናቀቀ ድርጅቶቹን ጉልህ በሆነ መልኩ ሊረዷቸው እንደማይችሉ ጠቅሰው፥ አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያን ተቋማት አማራጭ የገንዘብ ድጋፍ ሊያገኙ እንደሚችሉ ቢሰማቸውም በእርግጠኝነት ቅነሳው በሁሉም የሀገሪቱ ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ ከሚሰጡት አገልግሎቶች ደረጃ እና ጥራት አንፃር ተጎጂ መሆናቸውን አመላክተዋል።

በሊባኖስ የአሜሪካ መንግስት የትምህርት፣ የጤና አጠባበቅ እና የሥነ-ምግብ መርሃ ግብሮችን እንደሚደግፍ በማናማ፣ ባህሬን በሚገኘው ዓለም አቀፍ የስትራቴጂክ ጥናት ተቋም የምርምር አስተባባሪ የሆኑት ሌይት አላጅ-ሎኒ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በሊባኖስ የሚገኙ የፍልስጤም እና የሶሪያ ስደተኞች እንዲሁም ከሃገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሊባኖሳውያንን የሚረዱ ፕሮግራሞች እንደሚጎዱ ገልጸው፥ የገንዘብ ቅነሳው የሰብአዊ ተሃድሶውን እና በዓለም ባንክ 11 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን የተገመተው የሊባኖስን መልሶ ግንባታን እንደሚያዳክም አብራርተዋል።

ኢራቅ እና ዮርዳኖስ የረዥም ጊዜ የአሜሪካ መንግስት እርዳታ ተቀባዮች እንደሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፥ እ.አ.አ. በ 2024 ኢራቅ 333 ሚሊዮን ዶላር፣ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር “በጣም ተወዳጅ ሃገራዊ የንግድ ልውውጥ” የሚያደርገው የዮርዳኖሱ የሃሽማይቶች ግዛት ደግሞ የ1.75 ቢሊዮን ዶላር የአሜሪካን እርዳታ ማግኘቱን ገልጸዋል።

የገንዘብ ቅነሳው በእያንዳንዱ ሀገር ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በእጅጉ ሊለያይ እንደሚችል የገለጹት አቶ ሌይት፥ ነገር ግን የዮርዳኖስ ጉዳይ ጎልቶ እንደሚታይ ጠቅሰው፥ አሜሪካ ለዮርዳኖስ ከምታደርገው የውጭ ዕርዳታ ግማሹ ወደ ዮርዳኖስ ብሔራዊ በጀት እንደሚሄድ እና ግማሹ ደግሞ በዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ በኩል ወደ ልማት ሴክተሩ የሚተላለፍ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህ ምክንያት ብሄራዊ የበጀት ጉድለት እንደሚጨምር እንዲሁም የጤና አገልግሎት፣ የትምህርት እና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ‘ዘ ናሽናል’ የተባለው በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የሚታተመው የመንግስት ጋዜጣ እንደዘገበው በዮርዳኖስ 35,000 ሰዎች በገንዘብ ቅነሳው ምክንያት በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ስራቸውን እንዳጡ በመጥቀስ፥ ይህም በ2024 መጨረሻ ላይ ያለውን 21.4 በመቶ የሥራ አጥነት መጠን መጨመሩን አብራርቷል።

አቶ ሌይት ከዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ለኢራቅ ከተሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ግማሽ ያህሉ ወደ ወታደራዊ በጀት የተመራ ሲሆን፥ የድጋፉ መቆም “ኢራቅ ከ ISIS እራሷን የመከላከል አቅም ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችል ገልጸው፥ ምናልባትም አገሪቷ ፊቷን ወደ ኢራን ልታዞር እንደምትችል ጠቁመዋል።

በኢራቅ የልማት ዘርፍ ሥር የሚገኙ የተጎዱት ፕሮጀክቶች በዋናነት ከዴሞክራሲያዊ ፕሮግራሞች እና ስደተኞች ጋር የተሳሰሩ ሲሆን፥ ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮምሽን ሚያዚያ 2015 ዓ.ም. በተገኘው የቅርብ ጊዜ አኃዛዊ መረጃ መሠረት ኢራቅ 280,000 ስደተኞች እና 1.2 ሚሊዮን ተፈናቃዮች እንደነበሯት ገልፆ ነበር።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የካቶሊክ የእርዳታ አገልግሎት እና የኢየሱሳዊያን የስደተኞች አገልግሎት የመሳሰሉ ቁልፍ የእርዳታ ድርጅቶች በአሜሪካ መንግስት ውሳኔ ተጎጂ መሆናቸው የተናገሩ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት የምግብ እርዳታ፣ የትምህርት እና የአደጋ ጊዜ ምላሽ አቅማቸው እንደሚቀንስ አስረድተዋል።

በዮርዳኖስ እና ኢራቅ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት የበጎ አድራጎት ማህበር (CNEWA) ክልላዊ ዳይሬክተር የሆኑት ራኤድ ባሁ ‘ክፍተቱን ለመሙላት’ የገንዘብ አቅም ስለማይኖር በቢሮአቸው ላይ ‘በተለይ በጤና እንክብካቤ ዘርፍ’ ብዙ ተጨማሪ የፋይናንስ ጫና እንደሚኖር ገልጸው፥ ተቋማቸው በፈረንሳይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተነሳሽነት የሆነው እና የገንዘብ ድጋፉ ቢቋረጥም ፕሮጄክቶቹ ያልተቋረጡበት ‘ሎውቭር ዲ ኦሪየንትን’ ጨምሮ ከትንሽ የካቶሊክ ድርጅቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በሊባኖስ፣ ሶሪያ እና ዮርዳኖስ የሎውቭር ዲኦሪየንት የሀገር ውስጥ ዳይሬክተር የሆኑት ቪንሰንት ጌሎት የኤጀንሲው አጋሮች የሆኑት ሃይማኖታዊ ጉባኤዎች፣ ሀገረ ስብከቶች እና የሀገር ውስጥ ማህበራት የግል ወይም እምነት ላይ የተመሰረቱ ስለሆኑ በትልልቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ትልቅ የገንዘብ ድጋፍ ሰጪ አካላት እንደማይረዱ አስረድተዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ የካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ የክልል አስተባባሪ ካራም አቢ ያዝቤክ በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ 40 በመቶው በጀታቸው የሚመጣው ከዩናይትድ ስቴትስ መንግስት እንደሆነ ገልጸው፥ ሌላኛው ትልቁ ለጋሽ በአሜሪካ መንግስት የውጪ እርዳታ ቅነሳ ምክንያት 62 በመቶ የሚሆነውን የገንዘብ ድጋፍ ያጣው የካቶሊክ የእርዳታ አገልግሎት እንደሆነ ገልጸዋል።

አንዳንድ ማህበረሰቦች የአገልግሎታቸው ጥገኛ ስለሆኑ ካሪታስ ይህ ጉዳይ እንደሚያሳስበው የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ሚያዝያ ወር ላይ አዳዲስ የገንዘብ ምንጮችን በመለየት እና እንቅስቃሴዎችን ለመቀነስ እንዲሁም በዮርዳኖስ የሚገኘውን ቢሮ ለመት በሂደት ላይ እንደነበሩ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ካሪታስ ኢራቅ ከዓመታዊ በጀቱ 20 በመቶውን ወይም ወደ 700,000 ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ ማጣቱን፥ በዚህም ምክንያት 25 ሰራተኞችን ማሰናበቱን የካሪታስ ኢራቅ ዋና ዳይሬክተር ናቢል ኒሳን ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ የገንዘብ ቅነሳው በሃገራቱ ውስጥ ባለው ከፍተኛ ሥራ አጥነት እና አስቸጋሪ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ምክንያት በኢራቅ እና በዮርዳኖስ ውስጥ በሚገኙ አናሳ የክርስቲያን ማህበረሰቦች ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አሳስበው፥ ይሄም በመሆኑ ለስደት እያጋለጣቸው እንደሆነ ጠቁመዋል።

“ፕሮጀክቶችን መተግበር ቤተ ክርስቲያን በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላትን ህልውና ያጠናክራል” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ ከዚህም ባለፈ ክርስትና ኢራቅ ውስጥ እንዳለ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ብሎም እሴቶቻቸውን እንደሚያሳዩበት ገልጸዋል።

አቶ ናቢል በቤተክርስትያናት የሚተዳደሩ እና በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙት ድርጅቶች ከአዲሱ የገንዘብ ድጋፍ አውድ ጋር በመላመድ ላይ እንደሆኑ እና ተጨማሪ እርዳታ ለማግኘት ፊታቸውን ወደ አውሮፓ ማዞራቸውን ገልጸው፥ ሆኖም ግን የአውሮፓ አጋሮች ድጋፍ ማድረግ ቢጀምሩ እንኳን፥ ‘የአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ ከፍተኛ’ ስለነበር ክፍተቶች ይኖራሉ’ ብለዋል።

15 Aug 2025, 12:58