የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ጥምረት አዲስ ፕሬዝዳንት መምረጡ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የፖርቱጋል ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ዳይሬክተር የነበሩት ዶክተር ኢዛቤል ካፔሎ ጊል የካቶሊክ የምርምር ዩኒቨርስቲዎች ስትራቴጂካዊ ጥምረት (SACRU) ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸው የተነገረ ሲሆን፥ ይህ ስትራቴጂካል ጥምረት በካቶሊክ ማኅበራዊ አስተምህሮ የተደገፈ ጥናት እና ምርምር የሚያደርጉ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ትስስር እንደሆነ ተገልጿል።
የካቶሊክ የምርምር ዩኒቨርስቲዎች ስትራቴጂካዊ ጥምረት (SACRU) የሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ኢስያ እና የአውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲዎችን የሚያካትት ሲሆን፥ ዶክተር ጊል በተቋሙ ውስጥ ሆነው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጥምረቱን “ልዩ ምርምሮችን ከካቶሊክ እሴቶች እና ተልዕኮዎች ጋር አጣምሮ የያዘ ልዩ የእውቀት ትስስር” ሲሉ ገልጸውታል።
ምርምር በጥምረቱ ውስጥ ያሉት ዘጠኙ ዩኒቨርሲቲዎች ለማስተማር እና የጋራ ጥቅምን ለማስከበር ለሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ ኃይል መሆኑን የገለጹት ፕረዚዳንቷ፥ በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ የካቶሊክ ዩኒቨርስቲዎች የቤተክርስቲያኗን ተልእኮ ለማራመድ፣ ብሎም ውይይትን፣ አካታችነትን እና አንድነትን ለማጎልበት ወሳኝ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የባህል ጥናት ሙሉ ፕሮፌሰር እና በአሁኑ ወቅት የፖርቱጋል ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ (UCP) ዳይሬክተር የሆኑት አዲሷ ፕሬዝዳንት፥ ከሊዝበን ዩኒቨርሲቲ በዘመናዊ ቋንቋዎች እና ስነ-ጽሑፍ ዲግሪ፣ በመቀጠልም በጀርመን ቋንቋ እና ባህል ከፖርቱጋል ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲ ዲግሪ ያገኙ ሲሆን፥ ጀርመን፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አየርላንድ፣ ኢጣሊያ፣ ብራዚል እና አሜሪካን ጨምሮ በበርካታ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ተባባሪ ፕሮፌሰር ሆነው አገልግለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በለንደን ዩኒቨርሲቲ የከፍተኛ ጥናቶች ትምህርት ቤት የክብር ባልደረባ እና በፖርቱጋል ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ ሳይንስ ፋኩልቲ ዲን በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፥ የሊዝበን ኮንሰርቲየም፣ የኮሙኒኬሽን እና የባህል የምርምር ማዕከል መስራች እንደሆኑ ተገልጿል።
የካቶሊክ የምርምር ዩኒቨርስቲዎች ስትራቴጂካዊ ጥምረት በካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ፌደሬሽን ውስጥ በርካታ ተወካዮች ያሉት እና በዓለም አቀፍ የካቶሊክ አካዳሚክ ማህበረሰብ ውስጥ ትልቅ ሚና የሚጫወት ተቋም እንደሆነም ጭምር ተነግሯል።
የሳክሮ ኩሬ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ዳይሬተር የሆኑት ኤሌና ቤካሊ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን (IFCU) ምክትል ፕሬዚዳንት እና የአውሮፓ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ፌዴሬሽን (FUCE) ፕሬዝዳንት ሲሆኑ፥ ሌላኛው ተወካይ የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን የካቶሊክ ዩኒቨርስቲዎች ድርጅትን ለሦስት ዓመታት የመሩት እና የሪዮ ዴ ጄኔሮ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ዳይሬክተር የሆኑት አባ አንደርሰን አንቶኒዮ መሆናቸው ተገልጿል።
የካቶሊክ የምርምር ዩኒቨርስቲዎች ስትራቴጂካዊ ጥምረት ዘጠኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከ250,000 በላይ ተማሪዎችን፣ እንዲሁም 20,000 ምሁራን እና ተመራማሪዎችን የያዘ ሲሆን፥ ይህ ትስስር ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እንዲሁም ‘በአንድ የጤና ማዕቀፍ ውስጥ በምርምር እና በፖሊሲ አወጣጥ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር’ ከዓለም ምግብ እና ግብርና ተቋም ጋር በትብብር እደሚሰራ ተነግሯል።
ድርጅቱ በካቶሊክ የትምህርት ተቋማት መካከል የላቀ ግንኙነት እንዲፈጠር ከቅድስት መንበር የባህል እና ትምህርት ጽህፈት ቤት ጋር የሚሰራ ሲሆን፥ በሚቀጥለው ዓመት ከጥቅምት 17 እስከ 23 ድረስ የካቶሊክ የምርምር ዩኒቨርስቲዎች ስትራቴጂካዊ ጥምረት እና የቅድስት መንበር ጽህፈት ቤት ከዓለም የትምህርት ኢዮቤልዩ ጋር በመተባበር "የሳይንሳዊ ምርምር ነፃነት" ላይ ያተኮረ መርሃ ግብር እንደሚያዘጋጁ ተነግሯል።
መርሃ ግብሩ የሚካሄደው በሮም በሚገኘው የአውስትራሊያ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ቅርንጫፍ ውስጥ ሲሆን፥ በዚህም ዝግጅት ተመራማሪዎች የአካዳሚክ ነፃነት ማዕቀፎችን፣ የገንዘብ አወቃቀሮችን እና የሥነ ምግባር ጉዳዮችን በሚመሩበት ወቅት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች እና እድሎች እንደሚዳስሱበት ተገልጿል።