MAP

ስሪላንካውያን እ.አ.አ. በ 2019 ዓ.ም. የትንሳኤ እሁድ ዕለት በተፈጸመው ጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሰዎች መታሰቢያ ላይ ሻማ ሲያበሩ ስሪላንካውያን እ.አ.አ. በ 2019 ዓ.ም. የትንሳኤ እሁድ ዕለት በተፈጸመው ጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሰዎች መታሰቢያ ላይ ሻማ ሲያበሩ   (ANSA)

የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣው ሃይማኖታዊ ጥቃት ሁሉንም እምነቶች እንደሚያሰጋ አስጠንቅቋል

እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ቤተክርስቲያናትን የሚረዳው ‘ኤይድ ቱ ዘ ቸርች ኢንኒድ’ (ACN) የተሰኘው የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሃይማኖት ነፃነት ጥሰቶች እየጨመሩ በመምጣታቸው “በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች” የአደጋው ሰለባ እንደሚሆኑ በማስጠንቀቅ፥ በአንድ የእምነት ማህበረሰብ ላይ የሚደርሰው ስጋት ሌሎችን አደጋ ላይ መጣሉ የማይቀር መሆኑን አሳስቧል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ነሐሴ 16 በሃይማኖት ወይም በእምነት ላይ የተመሰረቱ የአመጽ ድርጊቶች ሰለባዎችን ለማሰብ ከሚከበረው ዓለም አቀፍ ቀን ቀደም ብሎ ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ግብረ ሰናይ ድርጅት የሆነው እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው አብያተ ክርስቲያናት ድጋፍ የሚያደርገው ‘ኤይድ ቱ ዘ ቸርች ኢንኒድ’ በሃይማኖት ነፃነት ላይ የሚፈጸሙ ጥሰቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመሩ መምጣታቸውን አስጠንቅቋል።

ተቋሙ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነትን አስመልክቶ ያወጣው ዘገባ ዋና አዘጋጅ የሆኑት ማርታ ፔትሮሲሎ በሰጡት መግለጫ በእርግጥ ይህ ዘገባ በመላው ዓለም በሚገኙ በመቶ ሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች እውን ቢሆንም ይህን ድርጊት ችላ የማለት ዝንባሌ መኖሩን ገልጸው፥ “የሃይማኖት ነፃነት ጥሰት በብዙ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር በእንደዚህ ዓይነት ሪፖርት ግንዛቤን ማስጨበጥ ለእንዲህ ዓይነቱ ጥቃት ሰለባዎች አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

እ.አ.አ. በ 1999 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው የኤሲኤን የሁለት ዓመት የሃይማኖት ነፃነት ሪፖርት መጪው ዓመት ጥቅምት 11 ላይ ድጋሚ እንደሚወጣ አስታውሰው፥ ሪፖርቱ ለየት ያለ እንደሆነ፣ ምክንያቱም በሁሉም ሀገራት እና በሁሉም የሃይማኖት ቡድኖች ውስጥ ያለውን የእምነት ነፃነት ሁኔታ የሚመረምር ብቸኛው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሪፖርት በመሆኑ ተአማኒነት እንዳለው ገልጸዋል።

አንድ ቡድን የእምነት ነፃነት ከተነፈገ ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ሌሎችም ጋር መድረሱ የማይቀር ጉዳይ እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተው የገለጹት ወይዘሮ ማርታ ፔትሮሲሎ፥ ይህም በመሆኑ ችግሩን በጊዜ መቅረፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዓለም አቀፍ ውድቀት
ከመጀመሪያው እትም ጀምሮ ሪፖርቶቹ በሃይማኖት ላይ የሚደርሱ የከፉ ሁኔታዎችን ሲመዘግብ እንደነበረ ያስታወሱት ወይዘሮ ማርታ ፔትሮሲሎ፥ ያለመታደል ሆኖ ይህ በሚቀጥለው እትም በተለይም በአንዳንድ የዓለም አካባቢዎች የባሰ ሁኔታ ሆኖ እንደሚቀጥል ይጠበቃል ብለዋል።

ሦስት ዋና ዋና የሃይማኖት ስደት ወይም ጥቃት ዓይነቶች እንዳሉ የጠቆሙት ሃላፊዋ፥ እነዚህም በመንግስት የሚመራ ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ጭቆና፣ የጽንፈኞች ዓመፅ እና የብሔር ተኮር ሃይማኖት እንቅስቃሴ እንደሆኑ አብራርተዋል።

አፍሪካ ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ በዚህ ችግር እየታመሰች መሆኗን ያመላከቱት ወይዘሮ ማርታ፥ የኃይማኖት ጽንፈኝነት እየተስፋፋ እና ተጨማሪ ጥቃቶችን እያባባሰ መምጣቱን ገልጸው፥ የእምነት ማህበረሰቦች በታሪክ በሰላም ሲኖሩባት በነበረችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በቅርቡ ክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ጥቃት እንደደረሰባቸው አስታውሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በአንድ ወቅት የተረጋጋ ሰላም እንዳላት ሲነገርላት የነበረችው ቡርኪናፋሶ በአሁኑ ወቅት ‘በዓለም ላይ በርካታ የጂሃዲስት ጥቃቶች ከሚፈጸሙባቸው ቦታዎች አንዷ እንደሆነች የገለጹት ወይዘሮ ማርታ፥ በእስያ የብሔር ተኮር ሃይማኖተኝነት መጨመሩን፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን አለመረጋጋት እና በላቲን አሜሪካ እየጨመረ የመጣውን ጥሰቶች ጠቅሰዋል።

ተስፋ እና ስጋት
ወይዘሮ ማርታ ምንም እንኳን መጥፎ አመለካከት ቢኖርም በሲቪል ማህበረሰቡ እና መንግስታት መካከል ያለው ግንዛቤ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፥ ይህም የሃይማኖት ነፃነት ጥሰቶችን ለመግታት በሚደረገው ጥረት ላይ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ነገር ግን በምዕራቡ ዓለም ያለውን ስጋት በማንሳት በአንዳንድ የእምነት ቡድኖች ላይ የሚደርሰው ጥቃት መጨመር፣ በአብያተ ክርስቲያናት ላይ የሚደርሰው ጥፋት፣ በጋዛ ጦርነት ምክንያት ፀረ-ሴማዊ እና ፀረ-እስልምና አመለካከቶች መበራከታቸውን አስጠንቅቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ‘የበላይነት የተሞላበት ሃይማኖታዊ ስደት’ የሚሉትን ጨምሮ፣ ሃይማኖትን ከአደባባይ ለማግለል የሚደረገውን ጥረት በማስጠንቀቅ፥ ከዚህም በተጨማሪ በጤናው ዘርፍ የሕሊና መብቶችም ስጋት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አደጋዎች ቢኖሩትም ችግሮቹን መናገር
ወይዘሮ ማርታ ፔትሮሲሎ የኤ.ሲ.ኤን. ዘገባ በእምነት ቡድኖች ላይ የበቀል እርምጃ ሊያስነሳ ቢችልም፣ ችግሮችን ለመገምገም ሁልጊዜ እውነተኛ እና ተጨባጭ እንደሆነ በአፅንዖት በመግለጽ፥ ‘በእርግጥ የበቀል እርምጃ ሊወሰድ ይችላል የሚል ስጋት አለ፥ ነገር ግን ይሄንን ፈርተን ዝም ማለት አንችልም፥ ነገሮችን መቀየር የሚቻልበት መንገድ ይህ ነው ብዬ አምናለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

እ.አ.አ. በ 2010 ዓ.ም. ‘የአምላካችንን ስም በክፉ አንስተሻል’ በማለት የፓኪስታን ፍርድ ቤት የሞት ፍርድ የፈረደባትን ፓኪስታናዊቷን የክርስትና እምነት ተከታይ ኤስያ ቢቢን ያስታወሱት ወይዘሮ ማርታ፥ ኤሲያ ከእስር የተፈታችው ከጠንካራ ዓለም አቀፍ ጫና በኋላ እንደሆነ እና ይህ ባይደረግ ኖሮ ምናልባት አሁንም ድረስ በእስር ላይ ትገኝ እንደነበር አስታውሰዋል።

ለተግባር የተደረገ ጥሪ
እምነትን መሰረት ባደረገ ጥቃት ሰለባ ለሆኑት ወገኖች መተባበር እንደሚያስፈልግ ገልፀው፥ ብዙዎቹ የጥቃቱ ሰለባዎች የተረሱ ሆነው ስለሚሰማቸው ለእነዚህም ተጨባጭ የሆነ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል።

ወይዘሮ ማርታ ፔትሮሲሎ በመጨረሻም በየደረጃው የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የጸሎት፣ የቁሳቁስ እርዳታ እና ተሟጋችነትን በማበረታታት፥ የእምነት ነፃነት ሰብአዊ መብት ቢሆንም፥ ነገር ግን የጋራ ሃላፊነትም ጭምር እንደሆነ አስታውሰው፥ “ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነ ሰብአዊ መብት በሁሉም ቦታ እኩል እንዲሰጥ ማድረግ የኛ ፈንታ ነው” በማለት አጠቃለዋል።

22 Aug 2025, 13:42