ቬትናም መጪውን ትውልድ ከሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ለመከላከል እየሠራች እንደምትገኝ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2008 እስከ 2023 ባሉት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ሰለባ የሚሆኑ ሰዎች ቁጥር ከአራት እጥፍ በላይ መጨመሩ ሲነገር፥ ይህ ማለት ከ 30,000 ወደ 134,000 ከፍ ማለቱን በሰኔ ወር ይፋ የተደረገው ስታቲስትካዊ ዘገባ ሲያስታውቅ፥ ከፍተኛ ጭማሪ የታየባት አገር ቬትናም መሆኗን ፊደስ የተሰኘ የቫቲካን ዜና ወኪል ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት ሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪ ዎንጀለኞች ተጎጂዎችን ለማሳሳት እና ለማታለል በአካል መገናኘት እንደማያስፈልጋቸውም ተደርሷል። የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ለወንጀለኞች ምቹ ዘዴን የፈጠረላቸው ሲሆን፥ የበይነ-መረብ ላይ ማጭበርበሮች በርካታ የቬትናም ዜጎች ወደ ካምቦዲያ፣ ላኦስ፣ ማያንማር፣ ቻይና እና ወደ ጎረቤት አገሮች እንዲዛወሩ ማድረጉ ብሔራዊ ቀውስን እና አካባቢያዊ ማኅበራዊ ጉዳቶችን ማስከተሉ ታውቋል።
የወደፊት ትውልዶችን ከጉዳት መጠበቅ
በቬትናም የሃንግ ሆዋ ሀገረ ስብከት ካቶሊካዊ የዕርዳታ ድርጅት ባልደረባ እህት ቴሬዛ ፋም ካንህ ሃው የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል አስከፊነት እና የሚያስከትለውንም አደጋ በማስመልከት ከ100 በላይ ወጣቶችን ሰብስበው ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን መስጠታቸው ታውቋል። በመረጃ ተደራሽነት እጥረት ምክንያት በአገሪቱ ውስጥ በሩዝ ምርት በሚትታወቅ የቲየን ኖን ቁምስና ደህንነቱን በጠበቀ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር እና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ግንዛቤ ውስን መሆኑ ታውቋል።
በቬትናም የሚገኘው “ካሪታስ” ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት ደህንነቱ ያልተጠበቀ ስደት እና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በተቋቋመው ኮሚቴ በኩል መመሪያን እና አስተማማኝ መረጃዎችን በመስጠት፣ በተለይም በበይነ-መረብ አማካይነት የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችን ለማስቀረት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ታውቋል።
የአገሪቱ የሕዝብ ደኅንነት ሚኒስቴር እንደገለጸው፥ ቬትናም በቅርቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የበይነ-መረብ ላይ ማጭበርበሮችን ከመረመረቻችው በኋላ ወደ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በመሸጋገር በርካታ ሰዎችን ከጉዳት ማትረፏ እና ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የግንኙነት መረቦች በአገር ውስጥ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲዘጉ ማድረጓ ታውቋል።
ለለውጥ መሥራት
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2024 ዓ. ም. ብቻ 163 የሚሆኑ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ጉዳዮች በሕግ አስከባሪ ኤጀንሲዎች በኩል ታውቀው ምርመራ የተደረገባቸው ሲሆን፥ በ2025 የመጀመሪያ አጋማሽ 120 ጉዳዮች መታየታቸው ታውቋል።
ከሕዝቧ መካከል 73% የሚሆነው ማኅበራዊ ሚዲያን እንደሚጠቀም የሚነገርላት ቬትናም ከፍተኛ የኢንተርኔት እና የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ካሉባቸው አገራት መካከል አንዷ ስትሆን የተጠቃሚዎች ቁጥር ከ72 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ፣ 17% የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 24 ዓመት ያላቸው እንደሆኑ፣ 97% የሚሆኑት ወይም ወደ 24.7 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕጻናት በየቀኑ ከ5 እስከ 7 ሰዓታት ያህል ኢንተርኔት የሚጠቀሙ መሆናቸውን ፊደስ የዜና ወኪል በዘገበው አስታውቋል።
ወጣቶች እና ጎልማሶች መመሪያ እና ታማኝ መረጃ ከሌላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ዓለም የበይነ-መረብ ላይ ማጭበርበር እና ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋ ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ በአገሪቱ ውስጥ ድጋፎችን በማድረግ ላይ የሚገኘው ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት “ካሪታስ” አስታውቋል።