ካሪታስ ፓኪስታን በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እርዳታ ማድረጉ ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ነሃሴ 9 እና 10 በፓኪስታን በደረሰው አስከፊ የጎርፍ አደጋ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት እና መልሶ ለማቋቋም ካሪታስ ፓኪስታን በርካታ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ የካራቺ ሊቀ ጳጳስ እና የካሪታስ ፓኪስታን ፕሬዝዳንት የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ቤኒ ማሪዮ ትራቫስ የቫቲካን የዜና ወኪል ለሆነው ፊደስ የዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ቤተክርስቲያኒቷ ጉዳት ከደረሰባቸው ቤተሰቦች ጋር በጸሎት እና በድርጊት አብራ እንደምትቆም ገልጸው፥ ካሪታስ ፓኪስታን ለአደጋው በንቃት ምላሽ እየሰጠ እንደሆነ እና ይሄንንም አጠናክሮ ለመቀጠል ሁሉም ምእመናን እንዲሁም የሀገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ አጋሮች ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በደቡባዊ የህንድ ክልል በምትገኘው ሲንዲ ግዛት አዲስ የጎርፍ አደጋ እና ከባድ ዝናብ ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቂያ በመሰጠቱ በካራቺ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ የተነገረ ሲሆን፥ ቀደም ብሎ በደረሰው በጎርፍ አደጋ ቢያንስ ሰባት ሰዎች ህይወታቸው እንዳለፈ እና በአከባቢው በሚገኙ መሰረተ ልማቶች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን መረጃዎች አመላክተዋል።
እርዳታ እየደረሰ ነው
የካሪታስ ፓኪስታን ዋና ዳይሬክተር አምጃድ ጉልዛር እንደተናገሩት የጉዳቱን መጠን ግምት ውስጥ በማስገባት ሁኔታውን ብሄራዊ ድንገተኛ አደጋ ብለው የገለጹት ሲሆን፥ በጎርፍ አደጋው በተጎዱ አካባቢዎች ላይ አፋጣኝ እርዳታ እየተከፋፈለ መሆኑንም አስረድተዋል።
የካሪታስ ፓኪስታን ሰራተኞች የተጎጂዎችን ፍላጎት በመገምገም ላይ እንደሚገኙ እና የምግብ፣ የመጠለያ፣ የህክምና ድጋፎችን እያቀረቡ እንደሆነ፥ እንዲሁም የተጎዱ ቤተሰቦችን መልሶ ለማቋቋም በትጋት እየሰሩ እንደሆነ ዳይሬክተሩ የገለጹ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የካሪታስ ቡድን የደረሰውን ውድመት እየገመገመ እና የእርዳታ ጥረቶችን እያስተባበረ እንደሆነ አስረድተዋል።
በጎ ፈቃደኞች እና የግዛቱ ባለስልጣናት በጋራ በመተባበር የተጎጂዎችን ፍላጎት ለማወቅ አደጋው የደረሰባቸውን አካባቢዎችን እየጎበኙ እንደሆነ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በጎርፍ አደጋው የተጎዱ 2,500 ቤተሰቦች ወይም 17,500 የሚያህሉ ሰዎች የምግብ ፓኬጆችን፣ የንጽህና መጠበቂያ ዕቃዎችን እና የመጠጥ ውሃ እርዳታ ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ካሪታስ ፓኪስታን ከጐርፍ አደጋ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የተለመዱ በሽታዎችን ለመከላከል የሚረዱ 15 ነፃ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ካምፖችን ማቋቋሙ የተነገረ ሲሆን፥ ቤታቸውን ላጡ ሰዎች የመጠለያ ዕቃዎችን ማዘጋጀቱ ተገልጿል።
አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋል
በአሁኑ ወቅት በቅድሚያ እርዳታ የሚደረግላቸው በጣም የተጎዱ አካባቢዎች መሆናቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፥ ካሪታስ ፓኪስታን በመጀመሪያ ያተኮረው ‘የተገለሉ እና ተደራሽ ያልሆኑ ማህበረሰቦችን በማስቀደም’ ላይ እንደሆነ ጠቁመው፥ በነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች መሰረታዊ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ተንቀሳቃሽ የህክምና አገልግሎት እየተሰጡ እንደሆነ አብራርተዋል።
የካሪታስ ፓኪስታን ዋና ዳይሬክተር አምጃድ ጉልዛር በመጨረሻም ለሲቪሉ ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ለጋሾች እና አጋሮች በፓኪስታን ለተከሰተው ሰብአዊ ቀውስ ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪ በማቅረብ፥ ሕይወትን ለማዳን፣ ቤተሰቦችን ለመጠበቅ እና የተጎዱትን ሰዎች ሰብዓዊ ክብር ለመመለስ አፋጣኝ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ በማሳሰብ አጠቃለዋል።