ሰላም እና ሰብዓዊ መብቶችን ማክበር አብረው የሚሄዱ መሆናቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋዛ ውስጥ ለተከሰተው ሰው ሠራሽ ረሃብ እና ለተፈጸመው ጥቃት ምላሽ የሚሰጥ ጠንከር ያለ መግለጫ ሰኞ ነሐሴ 19/2017 ዓ. ም. ማውጣቱ ታውቋል።
በዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ የሁለገብ ሰብዓዊ ዕድገት ዳይሬክተር ሚስተር ቪክቶር ጄኒና ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ድርጅቱ የተጠቀመባቸውን ጠንካራ ቃላት በማብራራት በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የደረሰውን ረሃብ በጽኑ አውግዘዋል።
ሲቪሎች ጉዳቱን ተሸክመዋል
የእስራኤል ወታደሮች ነሐሴ 14/2017 ዓ. ም. ጋዛ ከተማን ከወረሯት ከሁለት ቀናት በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በክልሉ ውስጥ ረሃብ መኖሩን በይፋ ማወጁን እና ዓለም አቀፉ ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት በአስከፊ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚገኙ ሲቪሎች ምላሽ መስጠት እንደሚፈልግ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ጋዛ ውስጥ ከ250 የሚበልጡ ሕጻናት በረሃብ መሞታቸውን የገለጹት ሚስተር ቪክቶር ጄኒና፥ መከራው ወደ ፍጻሜ እንዲደርስ ድርጅታቸው የሚፈለገው ለዚህ እንደሆነ ገልጸው፥ “በዚህ መከራ ውስጥ የተሳተፉት ባለስልጣናት በሰላማዊ ሰዎች እና የጤና ሠራተኞች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያቆሙ እንጠይቃለን” ብለዋል።
ከ200 በላይ ጋዜጠኞችን እና ከ180 በላይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞችን ጨምሮ በጥቃቱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ60,000 በላይ መድረሱን የጠቀሰው የካሪታስ መግለጫ፥ ባለስልጣናቱ ሆን ብለው በሲቪል ሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን ረሃብ አስታውሷል። ከዚህም በላይ የእስራኤል ወታደሮች መሠረተ ልማቶችን በሙሉ በማውደማቸው ሕይወት በአከባቢው ለሚኖሩ ሰዎች ፈጽሞ የማይቻል መሆኑን አፅንዖት ሰጥቷል።
በዚህ ብቻ ያላቆሙት ዳይሬክተሩ በተጨማሪም፥ ካሪታስ የበጎ አድራጎት ድርጅት “ከ1,000,000 የሚበልጡ ሲቪሎችን በስተደቡብ በሚገኘው ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ለማስፈር የተዘረጋውን እቅድ በማውገዝ ምንም ዓይነት ተቀባይነት የለውም ሲሉ አጥብቀው አውግዘዋል።
ሁሉም ሰው የሚጋራው ዘላቂ ሰላም ነው
የ “ካሪታስ” በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ግብ ሌሎች ሰዎች የሚጋሩት ዘላቂ ሰላም መሆኑን አስምሮበት፥ ድርጅቱ በማኅበረሰቦች መካከል ያለው የጥላቻ እና የብጥብጥ አዙሪት ሲወገድ ማየት እንደሚፈልግ አስታውቋል።
“ሁሉም የእስራኤል ታጋቾች እና በዘፈቀደ የታሰሩት ፍልስጤማውያን እንዲፈቱ የምንፈልገው እንዲሁም የሁሉም ሲቪሎች ሰብዓዊ ክብር እንዲመለስላቸው የምንጠይቀው ለዚህ ነው” ሲሉ የድርጅቱ ዳይሬክተር ሚስተር ቪክቶር ጄኒና ገልጸዋል።
በጋዛ ሰርጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ለረሃብ የተጋለጡ ሲሆን፥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ደግሞ ልዩ ልዩ አቅርቦቶችን እና የሕክምና ዕርዳታን እንደሚፈልጉ ታውቋል። በዚህም ምክንያት የ “ካሪታስ” በጎ አድራጎት ድርጅት መግለጫ፥ የተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎች ድርጅቶች የታመሙትን እና የተጎዱትን እንዲያክሙ እንዲሁም ለተራቡት የምግብ ዕርዳታን እንዲያድሉ ጥያቄ ማቀርቡን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ከሰላም ጋር ፍትህም እንዲኖር ያስፈልጋል
ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት “ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ” መግለጫን በማብራራት ዳይሬክተሩ፥ ድርጅቱ አፋጣኝ እና ዘላቂ የሆነ የተኩስ ማቆም ጥያቄ “እንዲሁም ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት አማካሪ አስተያየትን ሙሉ በሙሉ በማክበር ሕገ-ወጥ ወረራ እንዲያበቃ ጥሪውን አቅርቧል።
የዓለም አቀፍ ሕግ መከበር እና የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ የሚያሳስበው የበጎ አድራጎት ድርጅቱ፥ ይህም ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም እና ለወደፊቱ የዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ላይ ተጽዕኖ እንደሚሳድር የድርጅቱ ዳይሬክተር ሚስተር ቪክቶር ጄኒና አስረድተዋል።
ትልቁን ምስል ማየት እና አሁን ባለው ሁኔታ የረጅም ጊዜ ተፅእኖ ላይ ማተኮር አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፥ ዓለም አቀፍ የፍትህ ማዕቀፎችን ሙሉ በሙሉ ችላ ማለቱ ብዙ ብጥብጦችን እንደሚያመጣ አክለው አስረድተዋል።