ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ በጋዛ የተከሰተው ሰው ሰራሽ ረሃብ የዘር ማጥፋትን አስመልክቶ የተደረገ ስምምነትን ይጥሳል ማለቱ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ነሐሴ 14 የእስራኤል ወታደሮች በአሁኑ ወቅት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የተፈናቀሉ ሰላማዊ ዜጎች ተጠልለው የሚገኙባትን የጋዛ ከተማን መውረራቸውን ተከትሎ የተከሰተውን አስከፊ ቀውስ በማስመልከት ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ “ለዚህ አስከፊ ድርጊት ምስክር ነን” የሚል መግለጫ አውጥቷል።
ከካሪታስ መግለጫ ሁለት ቀናት በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአካባቢው ረሃብ እንዳለ በይፋ ያወጀ ሲሆን፥ ካሪታስ ችግሩ ቀድሞውኑ በከፍተኛ ሁኔታ መባባሱን አጽንኦት በመስጠት 112 ህፃናትን ጨምሮ 273 ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን ይፋ አድርጓል።
“ጥቆማው ማስጠንቀቂያ ብቻ አልነበረም” ያለው መግለጫው፥ ነገር ግን የሰብአዊ ድርጅቶች ለወራት ሲናገሩ የቆዩት አሳዛኝ ክስተት የሆነውን የጋዛ ነዋሪዎች ሆን ተብሎ ወደ ረሃብ የተወሰደበት ተግባር ማረጋገጫ እንደነበር አመላክቷል።
የተሰሉ ምርጫዎች
የካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ መግለጫ በማከልም እየተከሰቱ ያሉ ሞቶች አሳዛኝ ክስተቶች ብቻ እንዳልሆኑ በመግለጽ፥ ነገር ግን የጋዛን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማለትም መጠለያን፣ ምግብን እና ደህንነትን በመንፈግ ወደ ረሃብ እና ሞት የመውሰድ የተሰሉ ወይም የተቀነባበሩ ተግባራት ውጤት እንደሆኑ ገልጿል።
ይህ ጦርነት ሳይሆን የሲቪሉን ማህበረሰብ ህይወት ስልታዊ በሆነ መንገድ ማውደም እንደሆነ የጠቆመው የካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ መግለጫ፥ የጋዛን ከበባ “የጥፋት ማሽን” ሲል የገለጸው ሲሆን፥ በተፈጥሮ አደጋዎች ከሚመጣው በተለየ ሁኔታ ይህ ሰው ሰራሽ ረሃብ እንደሆነ በመጥቀስ “እርዳታ እንዳይገባ በመከልከል፣ የምግብ ማጓጓዣዎችን በቦምብ በመምታት፣ መሠረተ ልማቶችን በማውደም እና መሠረታዊ ፍላጎቶችን በመካድ” ሆን ተብሎ በተቀናጀ ስልት የተደረገ ሥራ ውጤት እንደሆነ አብራርቷል።
መግለጫው ሲቪሎች በተለይም ሴቶች እና ህፃናት በዚህ ረሃብ፣ የቦምብ ጥቃት እና ውድመት በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂ እንደሆኑ በማመላከት፥ መንግስታት፣ ድርጅቶች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ይህን የጋዛ ህዝብ ስቃይ በገንዘብ ድጋፍ፣ በወታደራዊ እርዳታ እና ዲፕሎማሲያዊ ከለላ በመስጠት ተባባሪ እንደሆኑ የገለጸ ሲሆን፥ “ዝምታቸው ገለልተኝነት ሳይሆን ተግባሩን እንደመደገፍ ይቆጠራል” ሲል አመላክቷል።
ባዶ ቃላት
በእነዚህ ጊዜያቶች በሙሉ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ባዶ መግለጫዎችን እና ቃላትን ብቻ ሲያቀርብ እንደነበረ ያስታወሰው መግለጫው፥ እነዚህ የዓለም አቀፉ መንግስታት ባዶ መግለጫዎች ለቀጣይ ጥፋት ጊዜ ለመግዛት ብቻ እንደሚያገለግሉ በመግለጽ፥ ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ በጋዛ በሰው ልጅ ክብር ላይ ሆን ተብሎ የሚደረግ ጥቃትን እና የሞራል ስርዓት ውድቀትን የአመራር፣ የኃላፊነት እና የሰብአዊነት ውድቀት አድርጎ ይመለከታል” በማለት አቋሙን ገልጿል።
ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ እነዚህን ሁሉ ድርጊቶች እና ግድፈቶች በጠንካራ መልኩ እንደሚጸየፍ አስረግጦ የገለጸው መግለጫው፥ ተግባራቱ ለሰብአዊነት እሴቶች እና መሠረታዊ መርሆዎች ግልጽ የሆነ ንቀትን እንደሚወክሉ፥ ብሎም ዓለም አቀፍ ህግን፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግን እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ህግን በግልፅ እንደሚጥሱ፥ እንዲሁም የዘር ማጥፋት ወንጀልን መከላከል እና ቅጣትን ጨምሮ የተወሰኑ የተባበሩት መንግስታት ስምምነቶችን እና በርካታ ድንጋጌዎችን በግልጽ እንደሚጥሱ አብራርቷል።
በእምነት ላይ የተመሰረተ ጥሪ
መግለጫው ነፍስኄር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሃዋሪያዊ መልዕክታቸው በሆነው ‘ፍራቴሊ ቱቲ’ ላይ “ወይ ሁላችንም በአንድነት እንተርፋለን ካልሆነ ደግሞ ሁላችንም በጋራ እንጠፋለን” ብለው የተናገሩትን ቃላት ያስታወሰ ሲሆን፥ ከቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥም መፅሃፈ ምሳሌ ላይ ያለውን “አፍህን ስለዲዳው ክፈት፥ ተስፋ ስለሌላቸውም ሁሉ ተፋረድ” የሚለውን፥ እንዲሁም የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25፡45 ላይ ያለውን “ከእነዚህ ከወንድሞቼ አነስተኛ ለሆነው ለአንዱ እንኳ ያላደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳላደረጋችሁት ነው” የሚለውን በመጥቀስ ወደ ተግባር መሄድ እንደሚያስፈልግ ገልጿል።
ከዚህም አንጻር ድርጅቱ ተከታታይ አስቸኳይ ሰብዓዊ ፍላጎቶችን ይፋ ሲያደርግ እንደነበር በመጠቆም፥ የምግብ፣ የመድኃኒት እና አስፈላጊ ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን ለማድረስ ያልተገደበ አቅርቦት እንዲኖር ከመጠየቅ ጎን ለጎን አፋጣኝ እና ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ ሲያደርግ እንደነበር አስታውሷል።
ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም ታጋቾች እንዲለቀቁ እና በዘፈቀደ የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ ብሎም የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ሃይል በአከባቢው እንዲሰፍር አጥብቆ የጠየቀ ሲሆን፥ ካሪታስ በጦርነቱ ተሳታፊ ያልሆኑት በተለይም ህጻናት፣ ሴቶች እና አረጋውያን ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው፥ እንዲሁም ወንጀለኞችን እና ተባባሪዎቻቸውን በሃገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች አቅርቦ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጿል።
መግለጫው በተጨማሪም ሃምሌ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. የዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት እስራኤል በሃይል ከያዘቻቸው የፍልስጤማዊያን ግዛት ውስጥ በአስቸኳይ እንድትወጣ የሚጠይቀውን ምክረ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በማጉላት፥ ይህም የሰፈራ እንቅስቃሴን ማቆም፣ ሰፋሪዎችን ማስወጣት፣ የካሳ አቅርቦትን እና የተባበሩት መንግስታት አካላት ወረራውን እንዲያከትም አስገዳጅ እርምጃዎች መውሰድን እንደሚያካትት ገልጿል።
‘የሥነ ምግባር ታማኝነት ፈተና’
መግለጫው በመጨረሻም በጋዛ የተከሰተው ሰው ሰራሽ ረሃብ የሞራል ታማኝነት ፈተና እንደሆነ እና አብዛኛውም እንዳልተሳካ በመግለጽ፥ ህዝብን ማስራብ ህይወትን ማዋረድ እንደሆነ ብሎም ‘ዝም ማለት ተባባሪ መሆን እንደሆነ’ በአጽንዖት ገልጿል።
ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ ሁሉም እምነት እና ህሊና ያላቸው ሰዎች ድምፃቸውን እንዲያሰሙ፣ መንግስታቶቻቸው ላይ ጫና እንዲያሳድሩ እና ፍትህን እንዲጠይቁ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፥ ዓለም ጉዳዩን እየተመለከተ እና ታሪኩም እየተመዘገበ እንደሆነ በመጥቀስ፥ ጋዛ የምትጠብቀው ባዶ ቃላትን ሳይሆን ድህንነት እና ተጨባጭ የሆነ ተግባር እንደሆነ በማሳሰብ አጠቃሏል።