ብፁዕ ካርዲናል ኩፒች በናጋሳኪ ዓመታዊ መታሰቢያ በዓል ላይ ‘ሰላም ፍርሃት ከሰፈነበት የእርቅ ስምምነት በላይ የሆነ ነገር ይፈልጋል' ማለታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
እ.አ.አ. ሃምሌ 3 ቀን 1945 ዓ.ም. በጃፓን ናጋሳኪ ከተማ ላይ የተፈጸመው የኒውክሌር ቦምብ ጥቃት መታሰቢያ በዓልን አስመልክቶ በተደረገው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ብፁዕ ካርዲናል ኩፒች ብሌሴ ባቀረቡት ቃለምዕዳን፣ አሜሪካ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የአቶሚክ ጦር መሳሪያ ለመጠቀም ያሳየችውን ውሳኔ አስመልክተው እንደ ቤተክርስትያን መሪ እንዲሁም እንደ አሜሪካዊ ዜጋ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል።
የቺካጎው ሊቀ ጳጳስ የቦምብ ጥቃቱ በዓለም አቀፍ ህግ እና በካቶሊክ የሞራል ትምህርት ውስጥ ያሉ ዋና ዋና መርሆዎችን የጣሰ እንደሆነ እና በተለይም በተዋጊዎች እና በሲቪሎች መካከል ያለውን ልዩነት ያላገናዘበ በመሆኑ “በጣም የተሳሳተ” እርምጃ እንደነበር በመጥቀስ፥ “በአስከፊው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ተዋጊ ያልሆኑ ሰዎች ዘንድ የነበረው ባሕላዊ ግትርነት ተንዷል” በማለት አብራርተዋል።
ብጹእነታቸው ከአቶሚክ ቦምብ ጥቃቱ በፊት የጃፓን ከተሞች ላይ ሲደርስ የነበረውን የእሳት አቀጣጣይ ቦምብ ጥቃትን በመጥቀስ፥ በ “ጠቅላላ የጦርነት” አመክንዮ መሰረት ንጹሃን ዜጎችን ኢላማ ማድረግ ትክክል እንዳልሆነ በማንሳት ድርጊቱን ተችተዋል።
ሌሎች ከተሞች ቀድሞውኑ በመውደማቸው ምክንያት ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ በከፊል መመረጣቸውን ያስታወሱት ብጹእ ካርዲናል ኩፒች፥ ይህም የሆነበት ምክንያት የአዲሱ መሣሪያ ሥነ ልቦናዊ ተፅእኖን ይቀንሳል ተብሎ ታስቦ እንደነበር አመላክተዋል።
አሜሪካዊው የኢየሱሳዊያን ማህበር አባል የሆነው ጆን ፎርድ እ.አ.አ. በ 1944 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ይህ “አውዳሚ የቦምብ ጥቃት” ከሥነ ምግባር አኳያ ተቀባይነት እንደሌለው በማውገዝ የጻፈውን ጽሁፍ የጠቀሱት ካርዲናል ኩፒች፥ የፎርድ ማስጠንቀቂያ በአሁኑ ወቅት በኒውክሌር ጦር መሳሪያ እገዳ ዙሪያ የሚነሱ የሞራል ጥያቄዎች መፍትሄ ባለማግኘታቸው ዛሬም ድረስ ያስተጋባል ብለዋል።
በሕዝብ አመለካከት ውስጥ ያለው ለውጥ
በአሁኑ ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያለው የሕዝብ አመለካከት እንደተቀየረ የጠቆሙት ብጹዕ ካርዲናል ኩፒች፥ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ የቦምብ ጥቃቶችን የሚቃወሙ በርካታ ሰዎች እንዳሉ ገልጸው፥ ሆኖም ግን በርካታ አሜሪካውያን አሁንም በዘመናዊ የግጭት ሁኔታዎች ውስጥ የኒውክሌር ጦር መሣሪያን የመጠቀምን ሐሳብ እንደሚደግፉ አንስተው ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል።
ብጹእነታቸው በቅርቡ በተካሄደው ጥናት መሰረት በመላምታዊ ጦርነቶች ውስጥ እንዲህ አይነት እርምጃዎች የአሜሪካን ወታደራዊ ህይወት የሚታደጉ ከሆነ ለሚደረጉ የኒውክሌር ጥቃቶች ህዝባዊ ድጋፍ መቀጠሉን እንደሚያሳይ ጠቅሰው፥ “ይህ የሚያመለክተው የዩናይትድ ስቴትስ ህዝብ የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ለመጠቀም እና የውጭ ዜጎችን ሆን ብሎ ለመግደል ያለው ፍላጎት ከ 1945 ዓ.ም. ጀምሮ ከነበረው ሃሳብ ብዙ ምሁራን እንደሚገምቱት ምንም አልተቀየረም” ብለዋል።
የቺካጎው ሊቀ ጳጳስ ጦርነት ግዴታ ከሆነ ፍትሃዊ የጦርነት ባህል ሊኖር እንደሚገባ ቤተክርስቲያን ያላትን አመለካከት በማጉላት፥ ከስልታዊ ስሌት ይልቅ በሥነ ምግባር እና አብሮነት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል።
ካርዲናሉ ከዚህም በተጨማሪ የሰላምን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ-ምህዳራዊ መሠረቶችን ለማደላደል በቅድስት መንበር የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የቀረበውን የጦር መሳሪያ ቅነሳ ጥሪን አስፈላጊነት ጠቅሰዋል።
የኑክሌር ጦር መሳሪያ እገዳ ሃሳብ
ብፁዕ ካርዲናል ኩፒች የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እገዳን በሚመለከት በሰጡት አስተያየት “ማስፈራሪያዎችን መጠቀም… በአብሮነት፣ በእውነተኛ ልማት እና በሰብአዊ መብቶች የተደገፈ ሥነ-ምግባር ሊያመጣ የሚችለውን በህዝቦች መካከል ሰላማዊ አብሮ መኖርን ፈጽሞ ሊያመጣ አይችልም” በማለት አሳስበዋል።
ብፁዕነታቸው የእርስ በርስ መቃቃርን ተከትሎ የሚፈጠረውን የሰላም እጦት በማስጠንቀቅ፥ በቅርቡ በኢራን እና በሰሜን ኮሪያ የተፈጠረውን የጂኦፖለቲካዊ ውጥረት በኒውክሌር ጦር መሳሪያ ምክንያት እየደረሰ ያለውን አደጋ በማስረጃነት ጠቅሰዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ሃላፊነት
አሜሪካዊው ካርዲናል ዩናይትድ ስቴትስ ከሩሲያ ጎን ለጎን ከዓለም ሁለቱ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ኃያላን ሃገራት አንዷ እንደመሆኗ መጠን፥ አገራቸው ልዩ ኃላፊነት እንዳለባት በመግለጽ፥ “ዩናይትድ ስቴትስ ከኒውክሌር ነፃ በሆነ መሠረት ላይ የታነፀ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ለመገንባት መንገዶችን መፈለግ አለባት” ሲሉ አሳስበው፥ አዲስ የጦር መሳሪያ ቅነሳ ጥረቶች እንዲደረጉ እና የገለልተኝነት ሁኔታ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ኩፒች በመጨረሻም ከአቶሚክ ቦምብ ጥቃት የተረፉት እና ‘ሂባኩሻ’ ተብለው የሚጠሩት ሰዎች ሰላም በምድራችን እንዲሰፍን ለአስርት ዓመታት ያክል ሲያደርጉት ለነበረው ቅስቀሳ ያላቸውን ክብር በመግለጽ፥ ድምፃቸው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ውድድርን ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት ማበረታታቱን መቀጠል እንዳለበት አሳስበው፥ “የሰው ልጅ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ውድድር እንዲቆም እራሱን መስጠት አለበት፤ ምክንያቱም ይህ ውድድር ማንንም አሸናፊ የማያደርግ፣ ነገር ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች የሚያልቁበት ውድድር ነው” በማለት አጠቃለዋል።