ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፥ “ፍቅር እና እርግዝና”
እርግዝና አስቸጋሪ ነገር ግን፣ ድንቅ ጊዜ ነው። አንዲት እናት የአዲስ ሕጻን ተአምር ለማሳየት ከእግዚአብሔር ጋር ትተባበራለች። እናትነት “የሴት አካል ለአዲስ ሰው ጽንሰትና ልደት የታለመ ልዩ የፈጠራ እምቅ ኃይል” (183) ውጤት ነው። “እያንዳንድዋ ሴት በእያንዳንዱ ልደት በሚታደስ የፍጥረት ምሥጢር ትሳተፋለች” (184)። መዝሙረኛው፥ “በእናቴ ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ” ይላል (መዝ. 139፡13)። በእናቱ ማሕፀን ውስጥ የሚያድግ እያንዳንዱ ሕጻን፡- “በማሕፀን ሳልሠራህ አወቅሁህ፤ ከመወለድህ በፊት ለየሁህ” (ኤር. 1፡5) የሚለው የእግዚአብሔር አብ የዘላለማዊ ዕቅድ አካል ነው። እያንዳንዱ ሕጻን ከጥንት ጀምሮ በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ቦታ አለው፤ እርሱ ወይም እርስዋ አንዴ ከተፀነሱ፣ የፈጣሪ ዘላለማዊ ሕልም እውን ይሆናል። ስለዚህ፣ ከጽንሰት ጀምሮ ያለውን የዚያን ፅንስ ታላቅ ዋጋ እናስብ። እርሱንም ምንጊዜም ከመልክ ባሻገር በሚመለከተው በእግዚአብሔር ዐይን እንመልከተው።
እርጉዝ ሴት ስለ ልጅዋ እያለመች በእግዚአብሔር ዕቅድ ትሳተፋለች። “ለዘጠኝ ወራት እያንዳንድዋ እናትና እያንዳንዱ አባት ስለ ልጃቸው ያልማሉ… ያለ ሕልም ቤተሰብ ሊኖራችሁ አይችልም። አንድ ቤተሰብ ማለም ካልቻለ፣ ሕጻናት አያድጉም፣ ፍቅር አያድግም፣ ሕይወትም ይደርቅና ይሞታል”። ለክርስቲያን ባለትዳሮች፣ ጥምቀት የዚያ ሕልም አካል መስሎ መታየቱ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ወላጆች በጸሎት ለጥምቀት ይዘጋጃሉ፣ ገና ከመወለዱ በፊት ሕጻን ልጃቸውን ለኢየሱስ አደራ ይሰጣሉ።
ዛሬ ያለው የሳይንስ ዕድገት የልጅን የጸጉር ቀለም ለመምረጥ ወይም ሊያጋጥሙት የሚችሉ የበሽታ ዐይነቶች ምን እንደ ሆኑ አስቀድመን እንድናውቅ ያስችለናል። ምክንያቱም ሥጋዊ ባህርያት ሁሉ ገና በጽንስ ደረጃ በሰው ዘረ-መል ቀመር ውስጥ ተጽፈው ይገኛሉና። ሆኖም ስለ ሕጻኑ ሙሉ በሙሉ የሚያውቀው ፈጣሪው እግዚአብሔር አብ ብቻ ነው። የሕጻኑን ውስጣዊ ማንነትና ዋጋ የሚያውቀው እርሱ ብቻ ነው። ነፍሰ ጡር እናቶች ልጆቻቸውን በጥልቀት ለማወቅና በማንነታቸው ለመቀበል የሚያስችላቸውን ጥበብ እንዲሰጣቸው እግዚአብሔርን መለመን ያስፈልጋቸዋል። አንዳንድ ወላጆች ልጃቸው በጥሩ ጊዜ እንዳልመጣ ይሰማቸዋል። እንዲፈውሳቸውና እንዲያበረታቸው እንዲሁም ልጃቸውን በሙሉ ልብ ለመቀበል እንዲረዳቸው እግዚአብሔርን መለመን ይኖርባቸዋል። ያም ሕጻን ተፈላጊ መሆኑ እንዲሰማው ማድረግ ጠቃሚ ነው። ሕጻኑ ተጨማሪ ዕቃ ወይም የሆነ የግል ፍላጎት ማርኪያ አይደለም። ሕጻን ልጅ ትልቅ ዋጋ ያለውና ለግል ጥቅም ሲባል ከቶ ሊገለገሉበት የማይገባ ሰብአዊ ፍጡር ነው። ስለዚህ፣ ይህ አዲስ ሕይወት ለእናንተ ምቹ ይሁን አይሁን፣ ወይም እናንተን የሚያስደስቱ ባሕርያት ይኑሩት አይኑሩት ወይም ከእናንተ ዕቅድና ምኞት ጋር ይስማማ አይስማማ እምብዛም አይገድም።
ምክንያቱም “ሕጻናት ስጦታ ናቸው… እያንዳንዱም ልዩና ምትክ የሌለው ነው… ልጆቻችንን የምንወደው ውብ ስለ ሆኑ፣ እኛን ስለሚመስሉ ወይም እንደ እኛ ስለሚያስቡ ወይም የምኞታችን ተምሳሌት ስለ ሆኑ ሳይሆን፣ ልጆች ስለ ሆኑ ነው። የምንወዳቸው ልጆች ስለ ሆኑ ነው። ልጅ ልጅ ነው”። የወላጆች ፍቅር እግዚአብሔር አባታችን የራሱን ፍቅር የሚያሳይበት መንገድ ነው። እርሱ የእያንዳንዱን ሕጻን መወለድ በጉጉት ይጠባበቃል፣ ያንን ሕጻን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ይቀበለዋል፣ በደስታና በነጻነትም ያስተናግደዋል።
እኔም የወደፊት እናቶችን ሁሉ በታላቅ ፍቅር እንዲህ በማለት አበረታታቸዋለሁ፡- ደስተኞች ሁኑ፣ ውስጣዊ የእናትነት ደስታችሁ እንዲወሰድባችሁ አትፍቀዱ። ልጃችሁ የእናንተ ደስታ ያስፈልገዋል። ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ የሌሎች ሰዎች አስተያየት ወይም ማናቸውም ችግር አንድን አዲስ ሕይወት ወደዚህች ዓለም ለማምጣት የእግዚአብሔር መሣሪያ የመሆናችሁን ደስታ አይቀንስባችሁ። ለልጃችሁ ልደት ያለ ፍርሃት ተዘጋጁ፣ “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፤ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ትደሰታለች፤ እርሱ የባሪያይቱንውን ውርደት ተመልክቶአልና” (ሉቃ. 1፡ 46-48) በሚለው በማርያም የውዳሴ መዝሙር ተካፈሉ። ይህን ድንቅ ስሜት በብዙ ጭንቀቶቻችሁ መካከል ለመለማመድ ሞክሩ፣ ወደ ልጃችሁ ታስተላልፉ ዘንድ ጌታ ደስታችሁን እንዲጠብቅላችሁ ለምኑት።
የአንድ እናትና የአንድ አባት ፍቅር
“ልጆች አንዴ ከተወለዱ ከምግብና ከእንክብካቤ በተጨማሪ መወደዳቸውን በእርግጠኝነት የማወቅ መንፈሳዊ ስጦታንም መቀበል ይጀምራሉ። ይህንንም ፍቅር ለእነርሱ ማሳየት የሚቻለው የግል ስም በማውጣት፣ ቀን ቀን በመጋራት፣ በፍቅር ዐይን በመተያየትና ብሩህ ፈገግታ በማሳየት ነው። በዚህ ዓይነት፣ የሰብአዊ ግንኙነቶች ውበት ነፍሳችንን እንደሚማርክ፣ ነጻነታችንን እንደሚሻ፣ የሌሎችን ልዩነት እንደሚቀበል፣ በውይይትም ላይ እነርሱን እንደሚያውቅና እንደ አጋር እንደሚቀበል ሕጻናት ይማራሉ… ፍቅር ማለት እንዲህ ነው፣ የእግዚአብሔርን የፍቅር ፍንጣቂ የያዘ ነው!”። እያንዳንዱ ሕጻን ከእናቱና ከአባቱ ፍቅርን የማግኘት መብት አለው፤ ሁለቱም ለሕጻኑ የተቀናጀና ኅብር ላለው እድገት አስፈላጊ ናቸው። የአውስትራሊያ ጳጳሳት እንዳመለከቱት፣ እያንዳንዱ ወላጅ “ለልጁ ዕድገት ልዩ አስተዋጽኦ ያበረክታል። የልጅን ክብር መጠበቅ ማለት የእርሱን ወይም የእርስዋን እናትና አባት የማግኘት ፍላጎትና የተፈጥሮ መብት ማረጋገጥ ነው”።
የምንናገረው በተናጠል ስለ አባትና ስለ እናት ፍቅር ሳይሆን፣ የሰው ሕይወት ምንጭና የቤተሰብ ጠንካራ መሠረት ተደርጎ ስለሚታሰበው ስለ ጋራ ፍቅራቸው ጭምር ነው። ይህ የጋራ ፍቅር ከሌለ፣ አንድ ሕጻን ተራ መጫወቻ ይሆናል። ባልና ሚስት፣ አባትና እናት፣ ሁለቱም “ከፈጣሪ እግዚአብሔር ፍቅር ጋር ይተባበራሉ፣ በልዩ መንገድ የእርሱ አስተርጓሚዎችም ናቸው”። ለልጆቻቸው የጌታን እናታዊና አባታዊ ፊት ያሳያሉ። በጋራ ሆነው አጸፋ የመመለስን፣ ልዩነቶችን የማክበርን እንዲሁም የመስጠትና የመቀበል ችሎታ የማዳበርን ጥቅም ያስተምሩአቸዋል። በአይቀሬ ምክንያት አንድ ወላጅ ባይኖር፣ ስለ ሕጻኑ ጤናማ የወደፊት እድገት ሲባል ለዚህ ጉድለት የሚሆን ማካካሻ መፈለግ ያስፈልጋል።
ብዙ ልጆችንና ወጣቶችን የሚጎዳው የወላጅ አልባነት ስሜት ዛሬ ከምናስበው በላይ ሥር የሰደደ ሆኖአል። ዛሬ ሴቶች ያላቸው የመማር፣ የመሥራት፣ ክህሎታቸውን የማዳበርና የግል ግብ የማስቀመጥ ፍላጎት ተገቢና በእርግጥም አስፈላጊ እንደ ሆነ እናውቃለን። በተመሳሳይ፣ በተለይ በመጀመሪያዎቹ የሕይወት ወራት የእናትን መኖር የሚሹ ሕጻናትን ፍላጎት ችላ ማለት አንችልም። በእርግጥ፣ “በውስጥዋ የተፀነሰውና እያደገ ያለው የአዲስ ሰብዓዊ ሕይወት ባለቤት የሆነችው ሴት እንደ እናትነትዋ ከወንድ ትቀድማለች”። የዚህ እናታዊ መገኘት ከሴትነት ባሕርዩ ጭምር መዳከም ለዓለማችን ከባድ ሥጋት ፈጥሮአል። ተመሳሳይነትን ለማይጠይቅ ወይም እናትነትን ለማያቃልል ለሴቶች የጾታ እኩልነት አስተሳሰብ በእርግጥ ዋጋ እሰጣለሁ። ምክንያቱም የሴቶች ታላቅነት ከማይገሰስ ሰብአዊ ክብራቸው ብቻ ሳይሆን፣ ለኅብረተሰብ አስፈላጊ ከሆነው የሴትነት ተሰጧአቸው የመነጩ መብቶችን ሁሉ የያዘ ነው። በተለይ የእነርሱ እንስታዊ ችሎታዎች፣ በተለይ እናትነት፣ ኃላፊነትንም ያዘለ ነው፤ ምክንያቱም ሴትነት በዚህ ዓለም ላይ ልዩ ተልእኮ ያለው ሲሆን፥ ይህንንም ተልእኮ ኅብረተሰቡ ለሁሉም የጋራ ጥቅም ሲል ሊጠብቀውና ሊንከባከበው ይገባል።
“እናቶች ራስን ማዕከል ላደረገ ግለሰባዊነት መስፋፋት ብርቱ ማርከሻ ናቸው።… የሕይወትን ውበት የሚመሰክሩት እነርሱ ናቸው”። በእርግጥ “አንድ ኅብረተሰብ ያለ እናቶች ሰብአዊ ክብር አይኖረውም። ምክንያቱም እናቶች ሁልጊዜ በክፉ ጊዜያት ጭምር፣ የርህኅራኄ፣ የቁርጠኝነትና የግብረ ገብ ጥንካሬ ምሥክሮች ናቸው። እናቶች ብዙውን ጊዜ ልጆቻቸው በሚማሩአቸው የመጀመሪያ ጸሎቶችና ሥራዎች አማካይነት የመንፈሳዊ ተሞክሮን ጥልቅ ትርጉም ያስተላልፋሉ።… ያለ እናቶች፣ አዲስ ምእመን አለመኖር ብቻ ሳይሆን እምነት ራሱ ቀላሉንና የመሠረታዊ ግለቱን ዋና ክፍል ያጣል።… ውድ እናቶች ሆይ፣ አመሰግናችኋለሁ። በቤተሰባችሁ ውስጥ ስለ ሆናችሁት ነገር፣ ለቤተክርስቲያንና ለዓለም ስለምትሰጡት ነገር አመሰግናችኋለሁ”።
ልጅዋን በርኅራኄና በደግነት የምትንከባከብ እናት በራስ መተማመንን እንዲዳብርና ዓለም ጥሩና ማራኪ ቦታ መሆኑን እንዲያውቅ ትረዳለች። ይህም ልጁ በራስ በመተማመን እንዲያድግና በአንጻሩም ከሰው ጋር የመቀራረብና ለሰው የማዘን ችሎታውን እንዲያዳብር ይረዳዋል። አባት በበኩሉ፣ የሕይወትን ገደቦች እንዲመለከት፣ ለሰፊው ዓለም ተግዳሮቶች ዝግጁ እንዲሆንና የከባድ ሥራንና የብርቱ ልፋትን አስፈላጊነት እንዲያውቅ ልጁን ይረዳዋል። ግልጽና ሰላማዊ የወንድነት ባህርይ ያለው እንዲሁም ለሚስቱ ፍቅሩንና ክብካቤውን የሚያሳይ አባት የተንከባካቢ እናትን ያህል አስፈላጊ ነው። ከእያንዳንዱ ቤተሰብ ተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሣት፣ በሥራ ድርሻዎችና ኃላፊነቶች ረገድ አንዳንድ ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን፣ የሁለቱም የወንድና የሴት በግልጽና በታወቀ መንገድ መኖር ለልጁ የተሻለ ዕድገት አመቺ የሆነ ከባቢን ይፈጥራል።
ብዙውን ጊዜ የእኛ “ኅብረተሰብ አባት አልባ” ነው ሲበል እንሰማለን። በምዕራባውያን ባህል፣ የአባት ተምሳሌትነት የለም፤ ጎድሎአል ወይም ጠፍቶአል። እናትነት ራሱ ጥያቄ ውስጥ የገባ ይመስላል። ውጤቱም ያለ ጥርጥር አደናጋሪ ሆኖአል። “በመጀመሪያ፣ ይህ እንደ ነጻነት ይቆጠር ነበር፤ እንደ ጌታ ከሚታየው አባት፣ ከውጭ የመጣ ሕግ አስከባሪ ተደርጎ ከሚታሰበው አባት፣ የልጆቹን ደስታ የመወሰን ሥልጣን ካለውና ለወጣቶች ነጻነትና ራስን መቻል እንቅፋት ከሆነ አባት እጅ አርነት እንደ መውጣት ይቆጠር ነበር። በመሆኑም፣ በአንዳንድ ቤቶች ውስጥ ፈላጭ ቆራጭነት አልፎ አልፎም ጭቆና ነግሦ ነበር።” ሆኖም ብዙ ጊዜ እንደሚሆነው፣ ሰው ከአንዱ አጥናፍ ወደ ሌላው አጥናፍ ሊሄድ ይችላል። በዘመናችን፣ ችግሩ የአባት አለቅነት መሆኑ ቀርቶ የአባት በዚያ አለመገኘት፣ አለመኖር ይመስላል። አባቶች ብዙውን ጊዜ በራሳቸውና በሥራቸው እጅግ ስለሚጠመዱ፣ ቤተሰቦቻቸውን ችላ ይላሉ።
ጨቅላዎችንና ለጋ ወጣቶችን ለብቻቸው ይተውአቸዋል። ለመገናኛ እና ለመዝናኛ የሚሰጠው ጊዜም በአባት መኖርና በአባት ሥልጣን ላይ ጫና አሳድሮአል። ዛሬ ሥልጣን አብዛኛውን ጊዜ እንደ ጥርጣሬ፣የዐዋቂዎች አያያዝም እንደ ብልግና መታየት ጀምሮአል። እነርሱ ራሳቸው እርግጠኞች ስላልሆኑ፣ ለልጆቻቸው እርግጠኛና ጠንካራ አመራር መስጠት አይችሉም። የወላጆችና የልጆች ሚና መቀያየር ጤናማ አካሄድ አይደለም፤ ምክንያቱም ልጆች ሊለማመዱት የሚገባውን ትክክለኛ የዕድገት ሂደት ያደናቅፋል፤ ለመጎልመስ የሚያስፈልጋቸውን ፍቅርና አመራር ይነፍጋቸዋል።
እግዚአብሔር አባትን በቤተሰብ ውስጥ ያስቀመጠው በወንድነቱ “ለሚስቱ ቅርብ እንዲሆንና ሁሉንም ነገር፣ ደስታንና ሐዘንን፣ ተስፋና መከራን ሁሉ እንዲጋራ ነው። እንዲሁም ልጆቹ ሲያድጉ፣ ሲጫወቱና ሲሠሩ፣ ሲዝናኑና ሲደበሩ፣ ሲለፈልፉና ጸጥ ሲሉ፣ ሲደፍሩና ሲፈሩ፣ ሲቅበዘበዙና ወደ ትክክለኛው መንገድ ሲመለሱ ለእነርሱ ቅርብ እንዲሆን ነው። ሁልጊዜ የሚገኝ አባት እንዲሆን ነው። ‘መገኘት’ ስል ‘መቆጣጠር’ ማለቴ አይደለም። ቁጥጥር የሚያበዙ አባቶች ልጆቻቸውን ይጋርዳሉ፤ እንዲያድጉ አይፈቅዱላቸውም።” አንዳንድ አባቶች ዋጋ ቢስ ነን ወይም አላስፈላጊ ነን ብለው ያስባሉ፡፡ እውነታው ግን “ልጆች ችግር ገጥሞአቸው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የሚጠብቃቸው አባት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ነው። ልጆች ችግሩን ላለመቀበልና ላለማሳየት ይጥራሉ፣ ነገር ግን አባት ያስፈልጋቸዋል”። አባት ማጣትና ያለ ዕድሜአቸው ቀድሞ ማደግ ለልጆች ጥሩ አይደለም።
ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 168-177 የተወሰደ
አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በረገኔ