MAP

2024.01.27 Gesù scaccia il demonio a Cafarnao 2024.01.27 Gesù scaccia il demonio a Cafarnao 

የነሐሴ 04/2017 ዓ.ም ዘክረምት 6ኛ እለተ ሰንበት ቅ. ወንጌል እና የቅ. ወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት

1.      1ቆሮ 8፡ 1-13

2.     1ጴጥ 4፡ 1-5

3.     ሐዋ 26፡ 1-23

4.    ማቴ 12፡ 38-50

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ማረጋገጫ ምልክት ስለ መሻት

ከዚያም አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንና ፈሪሳውያን፣ “መምህር ሆይ፤ ከአንተ ታምራዊ ምልክት ማየት እንፈልጋለን” አሉት። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይጠይቃል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ ነበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ቈየ፣ እንዲሁ የሰው ልጅ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በምድር ሆድ ውስጥ ይቈያል። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ዕለት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው  ይፈርዱበታል፤ እነርሱ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና። እነሆ፤ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ።

በፍርድ ዕለት የደቡብ ንግሥት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና። እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ። “ርኩስ መንፈስ ከሰው ከወጣ በኋላ ዕረፍት ለማግኘት ውሃ በሌለበት ደረቅ ቦታ ይንከራተታል፤ የሚሻውን ዕረፍት ግን አያገኝም። ከዚያም፣ ‘ወደ ነበርሁበት ቤት ተመልሼ ልሂድ’ ይላል፤ ሲመለስም ቤቱ ባዶ ሆኖ፣ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። ከዚያም ይሄድና ከራሱ የባሱ ሌሎች ሰባት ክፉ መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ እነርሱም ሰውየው ውስጥ ገብተው ይኖራሉ። የዚያም ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከፊተኛው የከፋ ይሆናል። በዚህ ክፉ ትውልድም ላይ እንዲሁ ይሆንበታል።”

የኢየሱስ እናትና ወንድሞች

ኢየሱስ ለሕዝቡ ሲናገር ሳለ፣ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። አንድ ሰውም፣ “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” አለው። ኢየሱስም፣ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል መለሰለት። በእጁም ወደ ደቀ መዛሙርቱ እያመለከተ እንዲህ አለ፤ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው፤ በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ ወንድሜ፣ እኅቴና እናቴም ነውና።

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

 

ክፉ ነገርን አለመቀበል (12፡38-42)

በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ “መምህር ሆይ! ከአንተ ምልክት ማየት እንፈልጋለን” አሉት (ማቴ 12፡38)፣ ይህ ደግሞ ምክንያታዊ የሆነ ጥያቄ ይመስላል። ኢየሱስ ተአምራትን እና ምልክቶችን ሲያደርግ ነበር። ታዲያ ትልቁ ጉዳይ ምንድነው? ለምን ኢየሱስ የሚጠየቀውን ሁሉ ምልክት አላሳየም? ለምንድነው ይህ ጥያቄ በቀሪው የማቴዎስ ወንጌል 12 ውስጥ የሚገኝ የማስተማሪያ ርዕስ የሚሆነው?

አሁን ይህ አዲስ አንቀጽ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል። ይህ ቢያንስ ከምዕራፍ 12 ግማሹ ጋር የተመለከትነው ተመሳሳይ ተዋንያኖች ይገኙበታል። ጻፎችና ፈሪሳውያን ኢየሱስ የተናገረውን እየመለሱ ነው። ኢየሱስ በአጋንንት ተይዞ የነበረውን ዕውርና ዲዳ ሰው እንደፈወሰ አስታውሱ። ሰዎቹ አሁን ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲህ፣ የዳዊት ልጅ እንደሆነ እያሰቡ ነበር (ማቴ. 12፡22-23)። ፈሪሳውያን ኢየሱስ ተአምራትን የሚያደርገው በሰይጣን ኃይል እንደሆነ በማወጅ ይህን አልተቀበሉም። ኢየሱስ ይህ የሚቻል እንዳልሆነ ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥቷል። በተጨማሪም ኢየሱስ በጣም ግልጽ የሆነ ፍሬ ነጥብ ተናግሯል፡- የኢየሱስ ፍሬ ነጥብ ሰይጣንን እንዳሸነፈ ያሳያል። የፈሪሳውያን ፍሬ ክፉ እና ለፍርድ ብቁ መሆናቸውን ያሳያል።

ጻፎችና ፈሪሳውያን ኢየሱስ የተናገረውንና ያደረጋቸውን ነገሮች መልሰው በመጠየቅ ላይ ናቸው። "መምህር ሆይ ከአንተ ምልክት ለማየት እንሻለን?" የሚለውን ይህንን ቃል ለአፍታ አስቡበት። አሁን ምን ተፈጠረ? ኢየሱስ ማየትና መናገር ይችል ዘንድ በአጋንንት የተያዘውን ዕውርና ዲዳ የነበረውን ሰው ፈውሷል። ኢየሱስ ብቻ ነው ይህንን የመሰለ ምልክት የሚሰጣቸው። ምልክቱ በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ ህዝቡ ኢየሱስን ተስፋ የተደረገለት አዳኝ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት ነበር። ኢየሱስ ማንነቱን ለማሳየት ሁሉንም ዓይነት ተአምራት ሲያደርግ ቆይቷል። የኢየሱስ ፍሬ እርሱ ከእግዚአብሔር የተላከ አዳኝ መሆኑን ያሳያል።

ለዚህ ነው ኢየሱስ "ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይፈልጋል" (ማቴ 12፡39) በማለት የሚመልሰው ለዚሁ ነው።  ችግሩ ምንድን ነው? ችግሩ ኢየሱስ ማን እንደሆነ የሚረጋገጥ እውነተኛ ማረጋገጫ አለመፈለግ ነው። ኢየሱስ ማንነቱን ለማረጋገጥ ተአምራትን እያደረገ ነው። ሐዋርያትም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የሚሰብኩትን በመልእክት ለማረጋገጥ ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ። ስለዚህ ችግሩ ሊረጋገጥ የሚችል ማስረጃ አለመፈለግ ነው። ኢየሱስ እየኮነነው ያለው ይህን አይደለም። ችግሩ ኢየሱስ ምልክቶችን እያደረገ ነው፣ ነገር ግን እነዚህ ምልክቶች በቂ አይደሉም። እነዚህ ተቃዋሚዎች ተጨማሪ ነገር ይፈልጋሉ። ኢየሱስ ያደረገው ነገር ለእምነት በቂ እንዳልሆነ እየነገሩት ነው።

ይህ ዛሬ ይከሰታል ወይ? ብለን ራሳችንን ስንጠይቅ መልሱ አዎ! ዛሬም እየተከሰተ ይገኛል የሚለው ነው። ሰዎች ስለ አምላክ ተመሳሳይ አዋጅ አውጀዋል። እግዚአብሔር ሊያዩት የሚፈልጓቸውን ምልክቶች ቢያደርግ እንደሚያምኑ ይናገራሉ። ኢየሱስ ግን ይህን ክፉ እና አመንዝራ ብሎ ይጠራዋል። ለምን? ኢየሱስ ይህንን የተናገረው ችግሩ ማስረጃ መፈለግ ሳይሆን ማስረጃውን ውድቅ ለማድረግ የሚፈልግ ልብን ነው ያወገዘው። ኢየሱስ በፊታቸው ሌላ ተአምር ቢያደርግ በድንገት የሚያምኑ ይመስላችኋል? እንደዚያ ካሰባችሁ ኢየሱስ በዓይናቸው ፊት ያደረገውን ብዙ ተአምራት አላነበባችሁም ማለት ነው። ሁሉንም ዓይነት ተአምራት አይተዋል። “ተጨማሪ የተለየ ማስረጃ እፈልጋለሁ” በማለት ምሁራዊ እና አሳቢ መሆን በጣም ቀላል እንደሆነ እናያለን። ኢየሱስ ልብን እያነበበ ያለው ማስረጃው ችግሩ እንዳልሆነ እየተናገረ ነው። ችግሩ እናንተ እንድታምኑ ለማድረግ ኢየሱስ ምን ማድረግ እንዳለበት ለእግዚአብሔር ልንነግረው እንችላለን ብለን እናስባለን። ክፉ ልብ እግዚአብሔር አንድ ነገር ሊያደርግልኝ ይገባል ይላል። ክፉ ልብ እግዚአብሔር በእኔ ቃል ሊገኝ ይገባል ይላል። ክፉ ልብ እግዚአብሔር የምፈልገውን ነገር እስካላደረገ ድረስ አላምንም ይላል። ኢየሱስ በዚህ ምሁራዊ ገጽታ ውስጥ ዘልቆ በመግባት ትክክለኛው ጉዳይ ምን እንደሆነ እያሳየ ነው።

ነገር ግን ኢየሱስ (ማቴ 12፡39) ላይ እንዳደረገው የተናገረውን ልብ እንበል። ኢየሱስ ለሁሉም ሰዎች ጨዋታ መለወጫ ሊሆን የሚችል አንድ ተጨማሪ ወሳኝ ምልክት አለው። ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምንም ምልክት አይሰጥም። ዮናስ በትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀንና ለሊት እንደ ነበረ ሁሉ ኢየሱስም በምድር ልብ ውስጥ ሦስት ቀንና ሌሊት ይኖራል። የኢየሱስ ታላቅ ምልክት ከሞተ ከሦስት ቀናት በኋላ ትንሣኤው ይሆናል። ትንሳኤ የእምነት ምልክት ነው። እያንዳንዱ ሰው ከዚህ ምልክት ጋር መታገል አለበት። ኢየሱስ ከሞት ተነሳ። በዛ መረጃ ምን ታደርጋላችሁ? ለኢየሱስ ትንሳኤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምስክሮች አሉ፣ እናም ከተቃዋሚዎቹ መካከል አንዳቸውም ሊክዱ አይችሉም። የኢየሱስ ነጥብ በጣም ቀላል ነው። ትንሣኤ እምነትን ካላመጣ ሌላ ተጨማሪ ምልክት እምነትን ሊያመጣ አይችልም። የእሱ ትንሣኤ ብቸኛው አስፈላጊ ምልክት ነው።

አሁን ኢየሱስ (ማቴ 12፡41-42) ላይ አስደንጋጭ ነገር ተናግሯል። የነነዌ ሰዎች ይህን ትውልድ ያወግዛሉ ምክንያቱም በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና ኢየሱስ ከዮናስ እጅግ እንደሚበልጥ ግልጽ ነው። ነነዌ የአሦር ግዛት ዋና ከተማ እንደነበረች እና ያቺ ጨካኝ እና ክፉ ግዛት እንደነበረች ማስታወስ አስፈላጊ ነው። ዮናስ ወደ እነርሱ በመጣ ጊዜ ንስሐ ገቡ። ኢየሱስ የመጣው ጨካኞች ላልሆኑ፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቅዱሳን ሰዎች ናቸው ወደሚባሉት ነው። ነገር ግን ንስሐ እየገቡ ሳይሆን ኢየሱስን እየተቃወሙ ነው።

በተጨማሪም በሰሎሞን ዘመን የደቡብ ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ብዙ ርቀት እንደሄደች እናነባለን። እሷም አህዛብ ነበረች፣ ነገር ግን ወደ ሰሎሞን መሄድ አስፈላጊ መሆኑን ተረድታለች። ኢየሱስ ከሰሎሞን እንደሚበልጥ ግልጽ ነው፤ ሆኖም እነዚህ ሰዎች ወደ እሱ ለመምጣትና የሚያስተምረውን ነገር ለመስማት ፈቃደኞች አይደሉም። ከዮናስ እና ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ። ነገር ግን ሌላ ነገር ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ እየጠየቅን ወይም እየፈለግን እርሱን ለመቃወም ሰበብ እንፈጥራለን። ኢየሱስ ከዚህ በላይ ምን እንዲያደርግ ትፈልጋላችሁ? ከዚህ በላይ ምን በቂ ምልክት አለ ብላችሁ ታስባለችሁ?

ውድቅ የተደረገበት ምሳሌ (12፡43-45)

አሁን ወደ (ማቴ. 12፡ 43-45) ስንመጣ ኢየሱስ ርዕሰ ጉዳዮችን ሙሉ በሙሉ የቀየረ ሊመስል ይችላል። ወዲያው ኢየሱስ ስለርኩሳን መናፍስት በመናገር ሰውን ትተው ከሄዱ በኋላ እንደገና ወደ ሰው እንደሚመለሱ መናገር ጀመረ። ነገር ግን ይህ ስለ እርኩሳት መናፍስት የሚደረግ ውይይት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ስለ ርኩሳት መናፍስት የሚናገረው እውነት በልባቸው ውስጥ እየደረሰ ያለውን ውድቅ የማድረግ ችግር ለማሳየት እየተጠቀመበት ነው። ምሳሌው በሰውየው ላይ የተከሰተውን መንጻት እና ማጽዳት ያሳያል። ነገር ግን ቤቱ (ሰውየው) ባዶ ሆኖ ይቀራል፣ ሰባት ተጨማሪ መንፈሶች እንዲመለሱ ብቻ ይፈቅዳል።

ስለዚህ ምሳሌው ምን ማለት ነው? (ማቴ. 12፡45) መጨረሻ ላይ ኢየሱስ “ይህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆናል” እንዳለ ልብ እንበል። ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተጠቀመው ካለመቀበል ጋር በተያያዘ መልኩ ነው። ክፉ ነገሮችን ጠርገው አውጥተዋል፣ ነገር ግን በመንፈሳዊ ሕይወት አልተተካም። ቤቱ ባዶ ሆኖ ቀርቷል። ሰውዬው ምንም አልተማረም እና አሁንም በተመሳሳይ የአጋንንት ተጽዕኖ ውስጥ ነው። ለእዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ምላሽ ባለመስጠቱ ዘለቄታዊ በሆነ ችግር ውስጥ ይገኛል ማለት ነው።

ይህ የእስራኤል ችግር ነበር። እስራኤላውያን ከባርነት ጸድተዋል።  ነገር ግን ሰዎቹ በመንፈሳዊ ሕይወት ባዶ ሆነው ቆይተዋል፣ እናም ኃጢአታቸውን በእግዚአብሔር ሙሉ ህይወት አልቀየሩም። አሁን ሁኔታቸው ከቀድሞው የከፋ ነበር። የዕዝራና የነህምያ መጻሕፍትን ከነቢዩ ሐጌና ዘካርያስ ጋር ስናነብ የሕዝቡ ሁኔታ ይህ እንደነበረ እንረዳለን። የግዞት ቅጣት ያመጣባቸውን አንዳንድ ኃጢአቶችን አቁመዋል። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ አልነጹም። እናም ከዚያም ጌታን ለመፈለግ እና ለመውደድ በአዲስ ልብ አልታደሱም። የጌታን ቤት የሚገነቡበት ጊዜ አልደረሰም፣ ነገር ግን ስለ ራሳቸው ቤት ለመጨነቅ ራሳቸውን ሰጡ (ት. ሐጌ 1)። በዚህ ነጥብ ላይ ነበር ሚልክያስ ያስተዋለው ሕዝቡ አምልኳቸውንና መሥዋዕታቸውን ይዘው ወደ ቤተ መቅደሱ መሄድ ድካም ነው እያሉ ነው (ት. ሚልክያስ 1፡13) ብሎ ስለሁኔታው የገለጸው።

አሁን ይህ ለምን የከፋ ሁኔታ እንደሆነ ሊጠይቁ ይችላሉ። ራስን በማታለል ምክንያት ይህ የከፋ ሁኔታ ነው። አንዳንድ ኃጢአቶችን ስለማትሠራ ብቻ ለእግዚአብሔር ቅርብ እንደሆንክ ሆኖ ይሰማሃል። አንተ እንደ አለም መጥፎ ስላልሆንክ ወደ እግዚአብሔር የቀረበህ መስሎህ ሊሰማህ ይችል ይሆናል። ችግሩ ሕዝቡ ሕይወታቸውን ለጌታ ጥልቅ አምልኮ ለማድረግ ዳግመኛ አልሰጡም ነበር። ይህንን ለእኛ በቀጥታ ለመግለጽ እራሳችንን ከክፉ ድርጊቶች እና ከኃጢአት ማፅዳት እንችላለን። ነገር ግን ራሳችንን በእውነት ለኢየሱስ ለመስጠት ቃል ኪዳን የገባን ካልሆንን በስተቀር ሕይወታችን መንፈሳዊ ውድቀት ያጋጥመዋል። በህይወታችን ውስጥ ባዶ ነገር አለ እና በኢየሱስ ካልተሞላ የበለጠ በክፋት ይሞላል። አምላክ አንዳንድ የሥነ ምግባር ባህሪያትን ያቆሙ ሰዎችን ባዶ ዛጎሎች እየፈለገ አይደለም። እግዚአብሔር ልባቸው በእርሱ ፍቅር የተሞላውን ሕዝብ ይፈልጋል። እስራኤላውያን አንዳንድ ኃጢአቶችን በማጽዳት ግማሽ መንገድ ብቻ ሄዱ፣ ነገር ግን ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር በማደር አልሞሉትም። ኢየሱስ ሊሰራላቸው የመጣውን የማዳን ሥራ ማየት ባለመቻላቸው ሁኔታቸው ከበፊቱ የበለጠ የከፋ ነበር። በእግዚአብሔር እውቀት እና ፍቅር ካልተሞላን መጨረሻችን እግዚአብሔርን በመናቅ ሁኔታ ውስጥ እንገባለን። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስን ፈጽሞ ሊናፍቁትና ሊቀበሉት የሚችሉት በዚህ መንገድ ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ "ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ከዓለም ርኩሰት ካመለጡ በኋላ፥ ዳግመኛ በእርሷ ተጠልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሯቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ይሆንባቸዋል። የጽድቅን መንገድ ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደ ኋላ ከሚመለሱ ይልቅ የጽድቅን መንገድ ሳያውቁ ቀርተው ቢሆን ኖሮ በተሻላቸው ነበር። “ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፤” እንዲሁም “እርያ ብትታጠብ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች፤” የሚለው እውነተኛ ምሳሌ ደርሶባቸዋል" (2ኛ ጴጥ. 2፡20-22) የሚለውን ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።

አዲስ ቤተሰብ (ማቴ. 12፡46-50)

ኢየሱስ አሁንም እየተናገረ እንደሆነ እና አሁንም የእርሱን ንግግር እንዳቋረጡት ልብ እንበል (ማቴ 12፡46)። እናቱ እና ወንድሞቹ እሱን እየፈለጉት እና ሊያናግሩት እንደሚፈልጉ ለኢየሱስ መልእክተኛ ሲልኩበት ኢየሱስ የሚናገረውን በትክክል እንዳልተከታተሉት ይጠቁማል። ኢየሱስ ግን ይህን ለነገረው ሰው የሚከተለውን መልስ ሰጠው። "እርሱ ግን ለነገረው መልሶ እንዲህ አለው “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” አለው። እጁንም ወደ ደቀመዛሙርቱ ዘርግቶ “እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ፥ እኅቴም እናቴም ነውና” (ማቴ 12፡49-50) በማለት ይመልሳል።

የእግዚአብሔር ቤተሰብ ማን ነው? እስራኤላዊያን እንደሚያስቡት ስለ ደም መስመር ወይም የዘር ሐረግ ብቻ አይደለም የተነገረው። የአብርሃም ሥጋዊ ዘሮች በመሆናቸው ብቻ የእግዚአብሔር ቤተሰብ እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ። ይህንንም በማቴዎስ 3፡9 ላይ አጥማቂው ዮሐንስ ግልጽ ማድረግ ነበረበት። አብርሃም አባታችን ነው እንዳይሉ ነገራቸው። አንድ ሰው የእግዚአብሔር ቤተሰብ የሆነው በዚህ መንገድ አይደለም። የአብን ፈቃድ የሚያደርግ ማንኛውም ሰው በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ነው።

ግን በድጋሚ፣ ይህ ማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ላለው ታሪክ በዘፈቀደ የተደርገ የንግግር ማቋረጥ ዓይነት አይደለም። ልክ እንደ ርኩስ መንፈስ ምሳሌው ኢየሱስ የፈጠረውን አዲስ ሁኔታም እየገለጸ ነው። የእግዚአብሔር ቤተሰብ ከመሆናችሁ በፊት የአብርሃም፣ የይስሐቅ እና የያዕቆብ ሥጋዊ የደም መስመር ነበራችሁ። አሁን ግን ኢየሱስ የመጣው በአብርሃም ደም ያልታሰረ አዲስ ቤተሰብ ለመፍጠር ነው። ከዚህ ይልቅ አዲሱ የኢየሱስ ቤተሰብ በኢየሱስ ደም የታሰረ ነው።

ኢየሱስን በመከተል ወደ አዲስ ቤተሰብ እየገባን ነው እናም በዚህ መልኩ እርስ በርስ መተያየት አለብን። ይህ የአይሁዶች ችግር ብቻ አይደለም፣ የሌሎች ክርስቲያኖችም ችግር ጭምር ነው። በክርስቶስ የተገናኘን እንደ አንድ ቤተሰብ በህብረት በጥልቅ እንደተገናኘን ሆኖ ሊሰማን ይገባል።

እንግዲያው ትምህርቱን በምንሰማበት ጊዜ ኢየሱስ የሰጠንን እነዚህን ምስሎች አንድ ላይ እናንሳ። በመͶመሪያ፣ ኢየሱስን ለአንተ የበለጠ ሊያረጋግጥልህ የሚገባው ስለመሰለህ አትናቀው። ኢየሱስ ማንም ሰው ሊያደርገው ከሚችለው በላይ አድርጓል፣ ትልቁ ማረጋገጫውም ትንሣኤው ነው። መላው እምነታችን የቆመው በኢየሱስ ትንሣኤ ላይ ነው። እሱን ለመከተል የሚያስፈልገን ማስረጃ ይህ ነው። የተለየ ነገር እንዲያደርግልን እያሰበ ምልክቱን የሚጥል ክፉ ልብ አይኑረን። በሁለተኛ ደረጃ ወደ እምቢተኝነት ልብ እንዴት ቀስ በቀስ ተንሸራተን እንደምንገባ በማሳየት አስጠነቀቀን። ኢየሱስን መከተል አንዳንድ የሥነ ምግባር ባሕርያትን ከማቆም የበለጠ ነገር ነው። በክርስቶስ ፍቅርና እውቀት ካልተሞላን ከኃጢአት ጋር መዋጋት ከንቱ ይሆናል ቤታችንንም ባዶ ያደርገዋል። መጨረሻው ከፊተኛው የከፋ እንዳይሆን ከላይ ባለው ነገር ላይ ትኩረታችንን በማድረግ ወደ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መግባት ይኖርብናል። ኢየሱስ ለእኛ በሚያቀርበው አዲስ ሕይወት እንሞላ።ሦስተኛ፣ ሕይወታችን ከክርስቶስ ጋር ሲቀላቀል የምያሳየውን  ውጤት እንመልከት። ወደ አዲስ ቤተሰብ እየገባን ነው። እኛ የቤተ ክርስቲያን አካል ብቻ አይደለንም። ነፍሳችንን ለኢየሱስ መስጠት ክለብ እንደመቀላቀል አይደለም። ይህ ወደ እግዚአብሔር ቤተሰብ መሄድ ነው፣ ወደማይጠፋ መንግሥት እና በክርስቶስ ዘላለማዊ ቤተሰብ እንድትሆኑ ኢየሱስ ልባችንን ይለውጥና ሕይወታችንን በመንፈሱ ይሙላው።

09 Aug 2025, 08:57