MAP

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ወገን የሆነው ማነው? የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ወገን የሆነው ማነው?  (@Vatican Media)

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ወገን የሆነው ማነው?

ሰዎች ሁሉ በተለያዩ መንገዶች ወደዚህ ሕዝበ እግዚአብሔር ካቶሊካዊ አንድነት ገብተዋል ወይም እንዲመጡ ተጠርተዋል። ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጋር ሙሉ ህብረት አላቸው የሚባሉት የክርስቶስ መንፈስ ኖሮአቸው ከቤተክርስቲያኒቱ ጋር በእምነት ምስክርነት፣ በምሥጢራት፣ በቤተክርስቲያናዊ አስተዳደርና ሱታፌ ጥምረት የፈጠሩት ናቸው። ሙሉ ካቶሊካዊ አንድነት የሌላቸው፣ ነገር ግን ምሥጢረ ጥምቀትን የተቀበሉ ምእመናን ፍጹምም ባይሆን ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጋር የተወሰነ ሱታፌ አላቸው።

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከአይሁድ ሕዝብ ጋር ያላት ግንኙነት ምንድነው?

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር ቃሉን እንዲቀበሉ ከሁሉ አስቀድሞ ከመረጣቸው የአይሁድ ሕዝብ ጋር ልዩ ግንኙነት አላት። «ልጅነት፣ ክብር፣ ኪዳናት፣ የሕግ መሰጠት፣ የመቅደስ ሥርዓት፣ የተስፋው ቃላት፣ አበው» የአይሁድ ሕዝብ ናቸው፤ «ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ» (ሮሜ. 9፡4፣5)። የአይሁድ እምነት፣ ከሌሎች ክርስቲያን ያልሆኑ ሃይማኖቶች በተለየ መልኩ፣ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ለእግዚአብሔር መገለጥ ምላሽ የሰጠ ነው።

በካቶሊክ ቤተክርሰቲያንና ክርስቲያን ባልሆኑ ሃይማኖቶች መካከል ያለው ግንኙነት ምንድነው?

በተለይ የሰው ዘር በሙሉ የጋራ መነሻና መድረሻ አንድ በመሆኑ በሁሉም ሕዝቦች መካከል ግንኙነት አለ። በሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም በጎ ነገር ወይም እውነት ከእግዚአብሔር የመጣና የእርሱም እውነት ነፀብራቅ እንደሆነ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትገነዘባለች። በመሆኑም ይህ መልካም ነገር ወይም እውነት ወንጌልን ለመቀበል ሊያዘጋጅና የሰውን ልጅ በክርስቶስ ቤተክርስቲያን አንድ እንዲሆኑ ሊያነቃቃ ይችላል።

«ከቤተክርስቲያን ውጭ መዳን የለም» የሚለው እርግጠኝነት ትርጉሙ ምንድነው?

ይህ አባባል መዳን አካሉ በሆነችው በቤተክርስቲያን በኩል ራስ ከሆነው ከክርስቶስ መሆኑን የሚያመለክት ነው። ስለዚህ፣ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ የተመሠረተችና ለደኅንነት አስፈላጊ መሆንዋን እያወቁ ወደ እርስዋ ለመግባት ወይም በእርሷም ውስጥ ለመቆየት እምቢ ያሉ ሊድኑ አይችሉም። እንደዚሁም፣ ለክርስቶስና ለቤተክርስቲያኑ ምስጋና ይግባቸውና፣ የራሳቸው ባልሆነ ስሕተት የክርስቶስ ወንጌልና ቤተክርስቲያኑን የማያውቁ ነገር ግን እግዚአብሔርን ከልብ የሚፈልጉና፣ በጸጋ ተነሣሥተው፣ ኅሊናቸው በነገራቸው መንገድ ፈቃዱን ለመፈጸም የሚጥሩ ሰዎች ዘላለማዊ መዳንን ሊቀዳጁ ይችላሉ።

ቤተክርስቲያን ወንጌል ለመላው ዓለም የምትሰብከው ለምንድነው?

ቤተክርስቲያን ይህንን ማድረግ የሚገባት ክርስቶስ «ስለዚህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀመዛመርቴ አድርጉአቸው» (ማቴ. 28፡19) ብሎ ስላዘዘ ነው። የዚህ የጌታ ተልዕኮአዊ ሥልጣን መነሻው ልጁንና መንፈስ ቅዱስን የላከው የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ፍቅር ነው፤ ምክንያቱም «እርሱ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ ይፈልጋል» (1ኛ ጢሞ. 2፡4)።

ቤተክርስቲያን ልዑክ የሆነችው በምን መልኩ ነው?

ቤተክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ እየተመራች በታሪክ ሂደት ውሰጥ የራሱን የክርስቶስን ተልእኮ ትቀጥላለች። ሰለዚህ፣ ክርስቲያኖች ክርስቶስ ያመጣውን ወንጌል ለሰው ሁሉ መሰበክ ይኖርባቸዋል፤ የእርሱንም መንገድ በመከተል፣ እስከ ሰማዕትነት ድረስ ራሳቸውን መሥዋዕት ለማድረግ መዘጋጀት አለባቸው።

ምንጭ፡ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ በአጭሩ ከተሰኘው መጽሐፍ ከንቀጽ 836 -873 ላይ የተወሰደ።

17 Jul 2025, 16:30