የአሜሪካ መንግስት ለእርዳታ ድርጅቶች ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ ማቋረጡ ጥልቅ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ተጽእኖ እንደሚኖረው ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም. የስፔን ከተማ በሆነችው ሴቪሌ የተጀመረ ሲሆን፥ የዓለም መሪዎች የዓለም የፋይናንስ ሥርዓቶች በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን በተሻለ ሁኔታ መደገፍ የሚችሉባቸውን መንገዶች ለማፈላለግ ውይይት እያደረጉ እንደሚገኝ ተገልጿል።
“ፋይናንስ ለልማት 2025” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኘው በዚህ ጉባኤ የአሜሪካ መንግስት ለውጪ ሃገራት ሲያደርግ የነበረውን እርዳታ ማቋረጡ በሚያስከትላቸው ጉዳቶች ላይ በሰፊው መወያየቱ የተገለጸ ሲሆን፥ የመፍትሄ ሃሳቦችንም ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ. ቅነሳዎች የሰብአዊ እርዳታ ላይ ያለው ተጽእኖ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ.) አማካይነት ለውጭ ሰብዓዊ እርዳታ ትሰጥ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ከመጋቢት ወር ጀምሮ 80 በመቶ የሚሆኑ መርሐ ግብሮችን መሰረዛቸው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተጨማሪ 14 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ ሊያደርግ እንደሚችል ዘ ላንሴት የተባለው ተቋም የሕክምና ሪፖርት የጠቆመ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 4.5 ሚሊዮን የሚሆኑት ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ እና ደቡብ እስያ አካባቢዎች መሆናቸውን ጥናቱ አመላክቷል።
ከሞት መጠን መጨመር በተጨማሪ የኤችአይቪ ሕክምና ሊቀንስ እንደሚችል የተጠቆመ ሲሆን፥ እንደ ሄይቲ ያሉ ሀገራት የኤችአይቪ መድሀኒት እጥረት እያጋጠማቸው እንደሆነ እና ከ150,000 የሚበልጡ ሄይቲዎች በአሁኑ ጊዜ በበሽታው እየተሰቃዩ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ከህክምና አገልግሎት እጦት ጋር በተያያዘ የዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ. ቅነሳ በተለይ እንደ ሱዳን፣ የመን እና ጋዛ ባሉ የግጭት ቀጣናዎች የምግብ ርዳታ አቅርቦትን ይቀንሳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ነፍሰ-ጡር እናቶች እና ህጻናት ተገቢውን እንክብካቤ እና ምግብ እንዲያገኙ የሚረዱ መርሃ ግብሮች በተለያዩ ሀገራት መቋረጣቸው ተነግሯል።
ለአስቸኳይ እርዳታ ዓለም አቀፍ ምላሾች
የዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ. መቋረጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካሳደረባቸው በአውሮፓ ውስጥ ካሉት ትልልቅ የሰብዓዊ ድርጅቶች መካከል ካሪታስ አውሮፓ አንዱ ሲሆን፥ ድጋፉ በመቆሙ ምክንያት ተቋሙ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታዎቹን ለማቋረጥ እንደተገደደ፣ ብሎም የምግብ እና የጤና አገልግሎቱ እንደተስተጓጎለበት ተገልጿል።
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሰብአዊ እርዳታ ኤጀንሲ የሆነው ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ የበለጸጉ ሀገራት በጣም የተቸገሩትን የማገልገል የሞራል ሃላፊነት እንዳለባቸው በመግለጽ፥ የዓለም መንግስታት አሜሪካ የዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ. ቅነሳን ሃሳብ እንድትቀይር ጫና እንዲያደርጉባት ጥሪውን ያስተላለፈ ሲሆን፥ ካሪታስ አውሮፓ የዓለም መሪዎች በዚህ ወቅት ከፍተኛ እርዳታ የሚፈልጉ ሀገራትን እንዲደግፉ አሳስቧል።
የተባበሩት መንግስታት ጉባኤ ግቦች እና መፍትሄዎች
ከ50 በላይ የዓለም መሪዎች በሴቪሌ ተሰባስበው ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ የተሻሉ መንገዶች ላይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፥ በዚህ ጉባኤ ላይ ከንግድ ተቋማት እና ከሲቪል ማህበራት የተውጣጡ ወደ 4,000 የሚጠጉ ተወካዮች ተገኝተው መርዳት ስለሚችሉባቸው ምርጥ መንገዶች ዙሪያ በሰፊው መወያየታቸው ተገልጿል።
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ የምትሰጠው እርዳታ ለ90 ቀናት እንዲቆም ያስተላለፈው ውሳኔ ከፍተኛ ጫና ከሚያስከትልባቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን፥ በ 2016 ዓ.ም. ሃገሪቷ ከአሜሪካ 1.2 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ እንዳገኘች የአሜሪካ መንግሥት የውጪ እርዳታ ለሕዝብ ይፋ በሚያደርግበት ድረ-ገጽ የሰፈረ መረጃ ይጠቁማል።
ድርጅቱ እና ከድርጅቱ የዕርዳታ ገንዘብ የተቀበሉ አጋር ድርጅቶች ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሃገራት በዓለም ዙሪያ የዕርዳታ ሥራቸውን ያቆሙ ሲሆን፥ የፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ እስካሁን ተፈጻሚ ያልሆነባቸው የዕርዳታ መስኮች፣ የነፍስ አድን እና የአስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቶች እንደሆኑም ይታወቃል።
የጉባዔው ዓላማ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓትን በአዲስ መልክ በመቅረጽ በማደግ ላይ የሚገኙ ሃገራትን አስቸኳይ ፍላጎቶች በተቻለ ፍጥነት ማሟላት የሚቻልበትን መንገድ ለመፈለግ እንደሆነ ተገልጿል።
በዚህም አግባብ መሪዎቹ የዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ. ቅነሳዎች አማካይነት ሊመጣ በሚችለው አሳሳቢ የሞት መጠን ላይ ከተወያዩ በኋላ መፍትሄ የሚሏቸውን ሃሳቦች ያነሱ ሲሆን፥ ከታቀዱት የመፍትሄ ሃሳቦች መካከል አንዱ የተቸገሩትን ለመርዳት የተለያዩ ገቢዎች መፍጠር እንደሚገባ፥ ከእነዚህም ውስጥ ከከፍተኛ ባለሃብቶች ላይ ከአንድ እስከ ሁለት በመቶ የሚደርስ ዓመታዊ ግብር መሰብሰብ የሚለው ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻያዎችን መተግበር፣ የሥነ ምግባር ማሻሻያ ማድረግ እና የግሉ ሴክተርን ማነቃቃት የሚሉት ይገኙበታል።