የአሜሪካ ካቶሊካዊ ጳጳሳት በበጀት ረቂቁ የመጨረሻ ረቂቅ ላይ የተሰማቸውን ጥልቅ ስጋት ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“One Big Beautiful Bill Act” በሚል የአሜርካ ኮንግሬስ ባጸደቀው የበጀት ረቂቅ ላይ ምላሽ የሰጡት የአሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ (USCCB) ፕሬዝደንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቲሞቲ ብሮሊዮ፥ ሕጉ ተጋላጭ በሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚያስከትለው ጎጂ መዘዝ እጅግ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
ከሳምንታት ድርድር በኋላ ባብዛኛው የፓርቲዎች ድምጽ የጸደቀው ሕጉ ቀጣዩን የፌዴራል የበጀት ዓመት ለማሻሻል ያለመ ነው ተብሏል። በደጋፊዎቹ የታገዘው ሕጉ፥ ጠቅላላ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማነቃቃት እና ከፍተኛ የታክስ ለውጦችን በማድረግ ቢሮክራሲያዊ ደካማነትን ለመቀነስ፣ የማኅበራዊ ዕቅዶችን ማሻሻያ እና የፌዴራል የገንዘብ ዕርዳታ ቅድሚያ የሚሰጥባቸውን ዘርፎች ያካትታል። ረቂቅ ሕጉ የመንግሥት ወጪን በማሳለጥ የሥራ ዕድል ፈጠራን በማስፋፋት የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን እንደሚያበረታታ የድጋፍ ሰጪው የሕግ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ነገር ግን የአሜሪካ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሕጉ የመጨረሻ እትም ላይ የተጠቀሱት ቁልፍ ድንጋጌዎች ሊስከትሉ የሚችሉት መዘዞች መኖራቸውን አስጠንቅቀዋል።
የአሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ (USCCB) ፕሬዝደንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቲሞቲ ብሮሊዮ፥ሕጉ ከጸደቀ በኋላ ወዲያው በሰጡት መግለጫ፥ በእርሳቸው አመለካከት የሰውን ልጅ ክብር ለመጠበቅ እና የጋራ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት የሚገቱ ለውጦች መኖራቸውን በሐዘን ገልጸዋል።
የኑሮ አለመመጣጠንን የሚጨምር እና ፍጥረትን የሚጎዳ ሕግ
የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቲሞቲ ብሮሊዮ በመግለጫቸው፣ የሐዋርያዊ አገልግሎት ተባባሪ ከሆኑት ብጹዓን ጳጳሳት ጋር ሆነው፥ ሕግ አውጪዎች የበጀት ማስታረቅ ሂደትን ተጠቅመው ችግር ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን ለመርዳት፣ ድሆችን እና አቅመ ደካሞችን የሚጎዱ የሕጉ ማዕቀፎች እንዲቀየሩ ደጋግመው ማሳሰባቸውን ገልጸዋል።
በተለይ የጤና አጠባበቅ እና የምግብ ዕርዳታ መቋረጥ፣ ድህነትን ይበልጥ የሚያስፋፋ የግብር ጭማሪ፣ ቤተሰብን እና ሕፃናትን የሚጎዱ የኢሚግሬሽን ደንቦች እና እንዲሁም ፍጥረትን ከውድመት የሚታደጉ መርሃ ግብሮችን መቀነስ የመሳሰሉ ሕጎችን ጠቁመዋል።
ሕጉ ፅንስን ለማስወረድ የፌዴራል መንግሥት በሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ ላይ ጥብቅ ገደቦችን መጣሉ፣ በትምህርት ምርጫ ላይ ወላጆች ያላቸውን ከፍተኛ ተሳትፎ የሚደግፍ እና የፌዴራል የሥርዓተ-ፆታ ሽግግር ሂደቶችን የሚደግፉ ገደቦች እና የመሳሰሉት በጳጳሳቱ ተቀባይነትን ያገኙ የቀድሞው ድንጋጌዎችን የሚያካትት ነው። ሆኖም በኮንግሬሱ በጸደቀው ረቂቅ ውስጥ አብዛኛዎቹ እነዚህ እርምጃዎች ተዳክመዋል ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲሠረዙ ተደርገዋል።
በአሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መሠረት፣ የፌዴራል መንግሥት የእቅድ ወላጅነትን በተመለከተ ለልዩ ልዩ ድርጅቶች የሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ ገደብ ወደ አንድ ዓመት ዝቅ እንዲል ተደርጓል።
ለልጆቻቸው ትክክለኛ ትምህርት ቤትን መምረጥ በተመለከተ መጀመሪያ ላይ ወላጆች የነበራቸው ውሳኔን የመስጠት መብት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ተደርጓል። በተጨማሪም የሥርዓተ-ፆታ ሽግግር ሂደቶችን በተመለከተ የፌዴራል የገንዘብ ድጋፍ ገደብ ከመጨረሻው ረቂቅ ላይ ሙሉ በሙሉ መሠረዙ ታውቋል።
ተጨባጭ ሕይወት ያስከተላቸው ውጤቶች
የአሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ (USCCB) ፕሬዝደንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቲሞቲ ብሮሊዮ፥ውሳኔዎቹ በተጨባጭ ሕይወት ላይ የሚያመጡትን መዘዝ በመጥቀስ፥ ሕጉ ተፈጻሚ በሚሆንበት ጊዜ ለሰዎች የጤና አጠባበቅ ተደራሽነት እንደሚጎድል እና የምግብ ሸቀጦችን የመግዛት አቅም እንደሚቀንስ፣ በቤተሰብ አባላት መካከል መበታተንን እንደሚያስከትል እና ተጋላጭ ማኅበረሰቦች የአካባቢ ብክለትን እና ከባድ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም አቅም እንደሚያንሳቸው አስጠንቅቀው፥ እነዚህን አስከፊ ጉዳቶች ለመከላከል የበለጠ መደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለትብብር የቀረበ ጥሪ
የአሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ (USCCB) ፕሬዝደንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቲሞቲ ብሮሊዮ፥ ረቂቅ ሕጉ የሚጸድቅ ቢሆንም ካቶሊካዊ ምዕመናን እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች የበለጠ ተጋላጭ የሆኑትን ለመርዳት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
“ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሰብዓዊ ክብር እና የጋራ ጥቅም እንዲከበር በማለት የምታስተምረው ትምህርት፥ ጥረታችንን ይበልጥ እንድንጨምር እና ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ተጨባጭ ዕርዳታን እንድንሰጥ ያስገድደናል” ብለው፥ የአሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፥ ለተቸገሩት የተሻለ ዕድል ለመስጠት የሚያስችል ሕግ እንዲጸድቅ የሚያደርጉትን ጥረቶች እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።