የሐምሌ 6/2017 ዓ.ም የ13ኛው እለተ ሰንበት ሣምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የእለቱ ንባባት
1. 1ኛ ነገሥት 19፡16፣19-21
2. መዝሙር 15
3. ገላቲያ 5፡1፣13-18
4. ሉቃስ 9፡51-62
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
ኢየሱስ የሚያርግበት ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና፤ እርሱም አስቀድሞ መልክተኞችን ላከ። ሄደውም ሊያሰናዱለት ወደ አንዲት የሳምራውያን መንደር ገቡ፤ ነገር ግን ወደ ኢየሩሳሌም ሊሄድ ፊቱን አቅንቶ ስለ ነበረ የመንደሩ ሰዎች አልተቀበሉትም። ደቀመዛሙርቱ ያዕቆብና ዮሐንስ አይተው፦ “ጌታ ሆይ! ከሰማይ እሳት ወርዶ እንዲበላቸው እንድናዝዝ ትወዳለህን?” አሉት። እርሱ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸው። ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ።
ኢየሱስን ለመከተል የፈለጉ ሰዎች
እነርሱም በመንገድ ሲሄዱ ሳሉ አንድ ሰው ኢየሱስን፦ “አንተ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ፤” አለው። ኢየሱስም፦ “ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች ጎጆ አላቸው፤ ለሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ምንም ስፍራ የለውም፤” አለው። ሌላውንም፦ “ተከተለኝ፤” አለው። እርሱ ግን፦ “ጌታ ሆይ! መጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ፤” አለ። ኢየሱስም፦ “ሙታኖቻቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት አስተምር፤” አለው። እንዲሁም ሌላው፦ “ጌታ ሆይ! እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን መጀመሪያ ሄጄ በቤቴ ያሉትን እንድሰናበት ፍቀድልኝ፥” አለ። ኢየሱስ ግን፦ “የሞፈሩን ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ማንም ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም፤” አለው።
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የተወደዳችሁ የእግዚብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!
በዛሬው ቅዱስ የወንጌል ክፍል (ሉቃ. 9፡51-62)፣ ቅዱስ ሉቃስ የኢየሱስን ወደ ኢየሩሳሌም የመጨረሻ ጉዞ ያደረገበትን ታሪክ በማቅረብ ይጀምራል፣ ይህም በምዕራፍ 19 ያበቃል። በመልካምድራዊ እና በቦታ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ እና በሥነ-መለኮት ደግሞ የመሲሑን ተልእኮ ፍጻሜ ለማድረግ የተፈጸመ ረጅም ጉዞ ነው። የኢየሱስ ውሳኔ ሥር ነቀል እና አጠቃላይ ነው፣ እናም እሱን የሚከተሉ ሰዎች ይህን እርምጃ እንዲወስዱ ተጠርተዋል። ዛሬ ወንጌላዊው ኢየሱስን እስከ መጨረሻው ለመከተል ከሚፈልጉ ሰዎች ምን እንደሚጠበቅባቸው ሙሉ በሙሉ የሚያብራሩ ሶስት ገፀ-ባህሪያትን - ሶስት የጥሪ ጉዳዮችን ልንለው እንችላለን ያቀርብልናል።
የመͶመሪያው ገፀ ባህሪ “አንተ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” (ሉቃስ 9፡57) በማለት አንድ ሰው ለኢየሱስ ቃል ይገባለታል። ለጋስ ሰው ነበረ! ነገር ግን ኢየሱስ የሰው ልጅ ጉድጓድ ካላቸው ቀበሮዎችና፣ ጎጆ ካላቸው ወፎች በተለየ መልኩ ራሱን የሚያስጠጋበት ቦታ እንደሌለው በመናገር መልስ ይመልስለታል (ሉቃስ 9፡58)። የኢየሱስን ፍጹም ድህነትን ያሳያል። በእርግጥም ኢየሱስ የወላጆቹን ቤት ትቶ የአምላክን መንግሥት ለሕዝቡ፣ ለጠፉት በጎች ለመስበክ ሲል ስለ ደኅንነቱን መጨነቅ ትቶ ነበር። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ለእኛ ለደቀ መዛሙርቱ፣ በአለም ላይ ያለን ተልእኮ ቋሚ ሳይሆን ተጓዥ፣ ተንቀሳቃሽ መሆኑን አመልክቷል። ክርስቲያን ተጓዥ ነው። ቤተክርስቲያን በተፈጥሮዋ ተንቀሳቃሽ ናት፣ በእሷ በራሷ ግቢ ውስጥ ተቀምጣ እና ተረጋግታ መቀመጥ የለባትም። እሷ ለሰፊው አድማስ ክፍት ነች፣ ተልካለች - ቤተክርስቲያን ተልዕኮ አላት፣ ወንጌልን በጎዳናዎች ላይ ለማድረስ እና ወደ ሰው እና ነባራዊ አከባቢዎች ለመድረስ። ይህ የመͶመሪያው ገጸ ባህሪ ነው።
ኢየሱስን የተገናኘው ሁለተኛው ገፀ ባህሪ ጥሪውን በቀጥታ ይቀበላል፣ ነገር ግን “ጌታ ሆይ፣ አስቀድሜ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” (ሉቃስ 9፡59) በማለት ይመልሳል። አባትህንና እናትህን አክብር በሚለው ትእዛዝ ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ ተማጽኖ ነው (ዘፀ. 20፡12)። ቢሆንም፣ ኢየሱስ “ሙታንን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው” (ሉቃስ 9፡60) በማለት ምላሽ ሰጥቷል። በእነዚህ ሆን ብሎ በተናገረው ቀስቃሽ ቃላት፣ እንደ ቤተሰብ ካሉ በጣም አስፈላጊ እውነታዎች በላይም ቢሆን፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የመከተል እና የማወጅ ቀዳሚነት አጽንዖት ለመስጠት አስቧል። የሞት ሰንሰለቶችን የሚሰብር እና የዘላለም ሕይወትን የሚያመጣውን ወንጌልን የማስተላለፍ አጣዳፊነት መዘግየትን አይፈቅድም፣ ነገር ግን ፈጣን እና ፍጹም ፈቃደኝነትን ይጠይቃል። ስለዚህ፣ ቤተክርስቲን ተጓዥ ነች፣ እናም እዚህ ቤተክርስቲያን ወሳኝ ነች፣ በፍጥነት፣ በቦታው ላይ፣ ሳይጠበቅ ትሰራለች።
ሦስተኛው ገፀ ባህሪ ደግሞ ኢየሱስን መከተል ይፈልጋል፣ ነገር ግን ይህንን የምያደርገው አንድ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ነው፣ ዘመዶቹን ከተሰናበተ በኋላ ሊከተለው እንደሚፈልግ ይገልጻል። እናም ይህ ከመምህሩ የተቀበለው ምላሽ ነው፡- “ “የሞፈሩን ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ማንም ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም፤” አለው (ሉቃስ 9፡ 62)። ኢየሱስን መከተል ጸጸትን እና ኋላቀር እይታዎችን አያካትትም፣ ነገር ግን የውሳኔ በጎነትን ይጠይቃል።
ኢየሱስን ለመከተል ቤተክርስቲያን ተጓዥ ነች፣ በዝግጁነት፣ በፍጥነት እና በቆራጥነት ትሰራለች። በኢየሱስ የተቀመጡት የእነዚህ ሁኔታዎች ዋጋ - ሚሲዮናዊነት፣ ፈጣንነት እና ውሳኔ ማድረግ የሚገባ ሲሆን በሕይወት ውስጥ ጥሩ እና አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች አለመገዛትን ይጠይቃል። ይልቁንም ትኩረቱ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን ዋናው ዓላማ ላይ ነው! በዋጋ የማይተመን የእግዚአብሄርን ጸጋ ለመመለስ እና ራስን ለማስተዋወቅ ያልተደረገ ነፃ እና ህሊና ያለው ምርጫ፣ በፍቅር የተሰራ መርጫ ያስፈልጋል። ይህ የሚያሳዝን ነው! ኢየሱስን ለመከተል ለራሳቸው ጥቅም፣ ማለትም ሥራቸውን ለማራመድ፣ አስፈላጊ ሆኖ እንዲሰማቸው ወይም ክብርን ለማግኘት ለሚያስቡ ወዮላቸው። ኢየሱስ ለእርሱ እና ለወንጌል ፍቅር እንድንሰጥ ይፈልጋል። ከልብ የመነጨ ስሜት ወደ ተጨባጭ የእጅ ምልክቶች የሚተረጎም ቅርበት፣ ፍቅር እና እንክብካቤ ከሚያስፈልጋቸው ወንድሞች እና እህቶች ጋር መቀራረብ የምያስፈልግ ሲሆን ይህም ልክ እሱ ራሱ እንደኖረ ሆኖ ለመኖር መሞከር ነው።
የተጓዥ ቤተክርስቲያን እናት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታ ኢየሱስን በደስታ እንድንከተል እና በአዲስ ፍቅር ለወንድሞች እና እህቶች የመዳንን ወንጌል እንድንሰብክ እርሷ በአማላጅነቷ ትርዳን።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ እና አዘጋጅ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ
ቫቲካን ሬዲዮ