MAP

በባንኮክ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ሰልፈኞች የታይላንድ እና የካምቦዲያ የድንበር ውዝግብ እንዲቆም ጠየቁ በባንኮክ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ሰልፈኞች የታይላንድ እና የካምቦዲያ የድንበር ውዝግብ እንዲቆም ጠየቁ  (ANSA)

የታይላንድ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በካምቦዲያ እና ታይላንድ ድንበር አከባቢ በተከሰተው ግጭት ያላትን ስጋት ገለጸች

የታይላንድ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ከጣሊያን የካቶሊክ ዜና ወኪል ከሆነው ‘አጀንሲር’ (AgenSIR) ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የታይላንድ እና ካምቦዲያ ድንበር አከባቢ በተፈጠረው ግጭት ዙሪያ ያላቸውን ስጋት በመግለጽ የአብሮነት እና የወንድማማችነት ባህል እንዲፈጠር ጥሪ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የታይላንድ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት እና የባንኮክ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ዣቪየር ቪራ አርፖንዳራታና የጣሊያን የካቶሊክ ዜና ወኪል ከሆነው ‘አጀንሲር’ (AgenSir) ጋር ሃምሌ 19 ባደረጉት ቃለ ምልልስ “የታይላንድ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን በድንበር አካባቢ የተከሰተውን ወታደራዊ ውጥረት በጥልቀት  ትመለከታለች” ብለዋል።

በታይላንድ እና በካምቦዲያ ድንበር ላይ ሃምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ሃሙስ ዕለት በተከሰተው እና እስከ አሁን ድረስ በቀጠለው ወታደራዊ ግጭት በትንሹ 33 ሰዎች ሲሞቱ፣ ከ168,000 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው የተገለጸ ሲሆን፥ 800 ኪ.ሜ. ያህል ርዝማኔ ያለው እና ሁለቱን ሃገራት የሚያገናኘው ድንበር ሃገራቱን ለአሥርት ዓመታት ሲያከራከር የቆየ ቢሆንም ምንም ዓይነት ወታደራዊ ግጭቶች አልተከሰቱም ነበር።

ታይላንድ እና ካምቦዲያ እያንዳንዳቸው በዚህ የቅርብ ጊዜ ግጭት የመጀመሪያውን ጥይት በመተኮስ እርስ በርስ እየተካሰሱ የሚገኝ ሲሆን፥ ታይላንድ ጦርነቱ የተጀመረው የካምቦዲያ ጦር በድንበር አካባቢ የታይላንድ ወታደሮችን ለመሰለል ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ባሰማራ ጊዜ እንደሆነ ተናግራለች።

ካምቦዲያ በበኩሏ የታይላንድ ወታደሮች ወደ ክመር-ሂንዱ ቤተመቅደስ በመውጣት የቀደመውን ስምምነት ጥሰዋል በማለት ከስሳለች።

የሁለቱ አገራት ውዝግብ ከመቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን ፈረንሳይ ካምቦዲያን በወረረችበት ወቅት የሁለቱ አገራት ድንበር ማስመሯን ተከትሎ የመጣ እንደሆነ ይነገራል።

“የድንበር ውዝግቦች ምንም እንኳን የግዛት ጉዳይ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ለፖለቲካ ፍጆታ እንደሚውሉ ቤተክርስቲያኗ ሙሉ በሙሉ ታውቃለች” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አርፖንዳራታና፥ ‘እነዚህ ውጥረቶች የብሔርተኝነት ስሜትን ለመቀስቀስ፣ ሕዝቡን ከኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ለማዘናጋት እና የተወሰኑ የፖለቲካ ተዋናዮችን ጥቅም ለማስከበር’ ሊውሉ እንደሚችል በቃለ ምልልሱ ወቅት አስረድተዋል።

እንደ ሊቀ ጳጳሱ ገለጻ ይህ ‘የአጭር ጊዜ ፖለቲካዊ ጥቅም ያለው’ ግጭት የሕዝቡን ደኅንነት አደጋ ላይ እንደሚጥል እንዲሁም ሰላማዊ እና ዘላቂ የረዥም ጊዜ መፍትሔን እንደሚያደናቅፍ ተገልጿል።

የውይይት አስፈላጊነት
ከዚህም በተጨማሪ ቤተክርስቲያኒቱ ‘የጽንፈኛ ብሔርተኝነት አደጋዎችን’ እና ወደ ሰላማዊ ጉዞ የሚያመጣውን “እውነተኛ እርቅ እና ፍትሃዊ መፍትሄ” ማራመድ የሚፈልገውን የዚህ አይነት የድንበር ግጭቶች ከታሪካዊ ውስብስብ ችግሮች እና አለመግባባቶች የመነጩ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ስታስጠነቅቅ እንደነበር አስታውሰዋል።

የጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዘዳንቱ ቤተክርስቲያኒቷ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ውይይቶችን፣ ድርድርን እና ዓለም አቀፍ ሽምግልናን በጥብቅ እንደምትደግፍ እና በድንበር አካባቢ ለሚኖሩ ዜጎች ያላትን አብሮነት አጽንዖት ሰጥተው የገለጹ ሲሆን፥ “ህዝቡ ከቤት ንብረቱ እና መተዳደሪያው መፈናቀሉን እና በማያቋርጥ የጥቃት ስጋት ውስጥ ሆኖ እየተሰቃየ እንደሚገኝ አሳስበው፥ “እምነታችን ብሔሩ ወይም ዘሩ ምንም ይሁን ምን የእያንዳንዱን ሰው ተፈጥሯዊ ክብር እንድንገነዘብ ይጠራናል” ካሉ በኋላ “ከፋፋይ አስተሳሰቦችን በመቃወም የአብሮነት እና የእውነተኛ ወንድማማችነት ባህልን ማጎልበት አለብን” ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ አርፖንዳራታና በማከልም “ቤተክርስቲያኒቷ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ሁሉ በማያሻማ ሁኔታ እንደምታወግዝ” ገልጸው፥ ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግ መከበር እንዳለበት እንዲሁም ሴቶችን፣ ህጻናትን እና አረጋውያንን ጨምሮ በጦርነቱ ውስጥ ተሳትፎ የሌላቸው ሰዎች ሁልጊዜም ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ደጋግመን እናሳስባለን ብለዋል።

ቤተክርስቲያን በአከባቢው እርዳታ ስትሰጥ ቆይታለች
በተጨማሪም ቤተክርስቲያኑ የታይላንድ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ አካል በሆነው የካቶሊክ የአደጋ ጊዜ እርዳታ እና ስደተኞች ቢሮ (COERR) በኩል ለተጎዱ ሰዎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን፣ ሰብአዊ ርዳታ እና መንፈሳዊ አገልግሎት ስትሰጥ እንደነበር የገለጹት ብጹእነታቸው፥ በታይላንድ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትም በሃገሪቷ ሰላም እንዲሰፍን ልዩ መስዋዕተ ቅዳሴዎችን፣ ጸሎቶችን እና የመቁጠሪያ ጸሎት ሲያካሂዱ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የታይላንድ ጳጳሳት ጉባኤ በካምቦዲያ ውስጥ ከምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ‘ጠንካራ እና ጥልቅ የሆነ የወንድማማችነት ግንኙነት’ እንዳለው በቃለ ምልልሱ መጨረሻ ላይ ገልጸዋል።

30 Jul 2025, 15:23