MAP

በስፔን ሙርቻ ግዛት የተቀሰቀሰውን ጸረ-ስደተኛ አመጽ በስፔን ሙርቻ ግዛት የተቀሰቀሰውን ጸረ-ስደተኛ አመጽ  

አቡነ ሆሴ ማኑኤል ሎርካ፥ በስፔን ሙርቻ ግዛት የተቀሰቀሰውን ጸረ-ስደተኛ አመጽ አወገዙ

ብጹዕ አቡነ ሆሴ ማኑኤል ሎርካ፥ በስፔን የካርታሄና ሀገረ ስብከት ጳጳስ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በቶሬ ፓቼኮ ግዛት የሚገኙ የቀኝ ፖለቲካ ክንፍ ደጋፊዎች ከሰሜን አፍሪካ በመጡ ወጣት ስደተኞች ላይ የፈፀሙትን ጸረ-ስደተኛ ጥቃት አወገዙ። አቡነ ሆሴ ማኑኤል በተጨማሪም ውጥረቱ እየጨመረ በመምጣቱ የሰላም፣ የአብሮነት እና የክርስቲያን ምስክርነት እንዲሰፍን ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በስፔን ደቡብ ምሥራቅ ክልል በምትገኘው ቶሬ ፓቼኮ ከተማ የሚገኙ የቀኝ ፖለቲካ ክንፍ ደጋፊዎች ከሰሜን አፍሪካ በመጡ ወጣት ስደተኞች ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች እስካለፈው ሳምንት መጨረሻ የዘለቀ ሲሆን፥ ይህን በማስመልከት በስፔን የካርታሄና ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ሆሴ ማኑኤል ሎርካ የሰላም ጥሪ በማቅረብ የአካባቢው ማኅበረሰብ ለሰላም እና ለወንድማማችነት ምስክሮች ጸንተው እንዲቆሙ ጠይቀዋል።

በአካባቢው የሰፈነው ውጥረት

የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ክስተቶችን በማስመልከት እንደዘገቡት፥ ጥቃቱ ያነጣጠረው ከሰሜን አፍሪካ ማግሬብ ክልል በመጡ ስደተኞች ላይ እንደሆነ ሲነገር፥ የግጭቱ መንስኤ ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ 3/2017 ዓ. ም. በአካባቢው በሚኖር አንድ ጡረተኛ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ እንደሆነ እና ጥቃቱን የፈጸሙት ከሰሜን አፍሪካ የመጡ ወጣት ስደተኞች ናቸው መባሉን ተከትሎ እንደሆነ ታውቋል። ለድርጊቱ ምላሽ እንዲሆን ዓርብ ሐምሌ 4/2017 ዓ. ም. አመሻሽ ላይ የታዋቂው ሕዝባዊ ፓርቲ ተወካይ ከንቲባ ፔድሮ አንገል ሮካ በጠሩት ሰላማዊ ሰልፍ ላይ 2,000 የሚሆኑ የቶሬ ፓቼኮ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

ሆኖም ሰላማዊ ሰልፉ ብዙም ሳይቆይ የቮክስ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ በቀኝ አክራሪ ሃይሎች ተጠልፎ ፀረ-ስደተኛ መፈክሮችን ማሰማት መጀመሩ ታውቋል። እንደ ሕዝባዊ የአንድነት ጥሪ የጀመረው ሰልፉ ወደ ብጥብጥ ምዕራፍ ተሸጋግሮ ስደተኞች በየመንገዱ እየተባረሩ እና በድንጋይ ሲወገሩ እና ማስፈራሪያ ሲደርስባቸው የሚያሳይ ምስል በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ላይ በሰፊው ተሰራጭተዋል። የሕግ አስከባሪ አካላት በበኩላቸው ሁከቱን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተዋል።

የቀኝ ፖለቲካ ደጋፊ ማኅበራዊ አንቂዎች ሰሜን አፍሪካውያን ከሀገሪቱ እንዲባረሩ በሚል አጸያፊ የሆኑ የጥላቻ ቋንቋዎችን በመጠቀም እና በስደተኞች በሚተዳደሩ የንግድ ድርጅቶች ላይ ጥቃት እንዲሰነዘርባቸው ተጨማሪ የቅስቀሳ መልዕክቶችን ይዘው ሲንቀሳቀሱ በአውታረ-መረብ መድረኮች ላይ ታይተዋል። ሁከቱን ለማስቆም ከፍተኛ የፖሊስ ሃይል በሥፍራው ቢሰማራም የሞሮኮ ነዋሪዎች በብዛት በሚገኙባቸው ሠፈሮች ውስጥ አዲስ የጥቃት ክስተቶች ሲከሰቱ፥ አንዳንድ ስደተኞች ለጥቃቱ የቁጣ ምላሽ መስጠታቸው ታውቋል።

የውይይት እና አብሮ የመኖር ጥሪዎች

ከቶሬ ፓቼኮ አካባቢ ነዋሪ ሕዝብ መካከል ወደ አንድ ሦስተኛ የሚጠጋው የውጭ አገር ዜጋ ሲሆን፥ ከእነርሱ ብዙዎቹ ለክልሉ ኢኮኖሚ አስፈላጊ በሆነው በግብርናው ዘርፍ ተቀጥረው የሚሠሩ እንደሆኑ ታውቋል። ማኅበራዊ ውጥረት በነገሠበት አካባቢ የሚኖሩ የመንግሥት ባለስልጣናት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ቡድኖች ለውይይት እና በሰላም አብሮ የመኖር ጥሪዎችን አቅርበዋል።

የታዋቂው ሕዝባዊ ፓርቲ ተወካይ ከንቲባ ፔድሮ አንገል ሮካ የተቀሰቀሰውን ሁከት ለመረጋጋት እና ጠንካራ የፀጥታ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጥሪያቸውን በድጋሚ ያቀረቡ ሲሆን፥ ይህ በንዲህ እንዳለ በስፔን የሰሜን አፍሪካ ሠራተኞች ማኅበር ፕሬዝደንት ሳባህ ያኩቢ ጥቃቱን አውግዘው ፈጻሚዎችን “ተንኮለኛ” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

ብጹዕ አቡነ ሆሴ ማኑኤል ሎርካ፥ በስፔን የካርታሄና ሀገረ ስብከት ጳጳስ ለተከሰተው ችግር ሁከትን መቀስቀስ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል፥ ይልቅ ጥልቅ የሆነ የፍርሃት እና የመረበሽ ስሜት እንዲፈጠር የሚያደርግ መሆኑን በመግለጽ የሰላም ጥሪ አቅርበዋል። የቶሬ ፓቼኮ ሕዝብ የረጅም ጊዜ የአብሮነት እና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በማስታወስ በተለይም የሥራ ዕድል በመፍጠር እና ውህደትን በማጎልበት ላሳየው አብነት አመስግነዋል።

ብጹዕ አቡነ ሆሴ ማኑኤል ሎርካ አያይዘውም፥ የአካባቢው ምዕመናን እና ማኅበረሰብ ሰላምን እና ዕርቅን በማስፋፋት እያደረጉት ላለው ተግባር አመስግነው፥ ሁሉም ነዋሪዎች ከየትኛውም ዓይነት አክራሪነት በመራቅ የሰላም፣ የፍቅር እና የይቅርታ ምስክር በመሆን ክርስቲያናዊ ጥሪያቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

15 Jul 2025, 17:46