የሄይቲ ገዳማውያት የሕዝባቸውን ስቃይ ለማቃለል እየሠሩ እንደሚገኙ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በሄይቲ የሚገኙ የዶሚኒካን እህቶች የበጎ አድራጎት ድርጅት እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚገኙ የሄይቲ ነዋሪዎች ተስፋን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
ሄይቲ በድህነት፣ በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በብጥብጥ እና መላውን ሕዝብ የሚጎዳ የጤና ችግርን ጨምሮ በሌሎች በርካታ ችግሮች ውስት እንደምትገኝ ታውቋል።
በሄይቲ አስቸኳይ የሕክምና አገልግሎት፣ የትምህርት፣ የሥነ-ልቦና ድጋፍ እና የሰብዓዊ ዕርዳታዎች ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ገዳማውያቱ ለሕዝቡ የሚሰጡት የሕክምና ዕርዳታ እና ምግብ ብቻ ሳይሆን በጎነትን እና ሰብዓዊ ክብርን በማጎልበት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
በዚህ አውድ ውስጥ የሚገኙት እህት ማርያ ማርቴ ታሪካቸው ለሕዝባቸው ባላቸው ፍቅር ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ያላቸውን በሙሉ ለሌሎች በየቀኑ የሚሰጡ የበርካታ ገዳማውያት ሥራ ምሳሌ ሆኖ ተገኝቷል።
የእህት ማርያ ማርቴ ተልዕኮ የጀመረው፥ “የሚበሉትን ስጧቸው” ከሚለው የኢየሱስ ክርስቶስ ቀላል ግብዣ ሲሆን እነዚህ ቃላት ለሕዝባቸው ከፍተኛ ተጋላጭነት ምላሽ የሚሰጡ ሆነው ተግኝተዋል።
እህት ማርያ ማርቴ ከክሮክስ ዴ ቡኬትስ አውራጃ እስከ ፖርት ኦ-ፕሪንስ ድረስ የሰጡት አገልግሎት ከኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አገልግሎት ጋር ተመሳሳይነት ያለው እንደ ነበር ተመልክቷል። በማቴ. 14:17 ላይ “ከአምስት እንጀራ እና ሁለት ዓሣ በቀር በዚህ ምንም የለንም” የሚለውን ያስታወሱት እህት ማርያ ማርቴ፥ በእጃቸው ብዙ ባይኖራቸውም ነገር ግን እግዚአብሔር ሥራው እንዲፈጸም የሚፈልገውን ያህል አብዝቶ ሊሰጥ እንደሚችል ገልጸው፥ በሕመም ምክንያት ለሚሰቃዩት እና ለሚጮሁት ሕዝባቸው ምንም ዓይነት ማፅናኛ ይዘው ካልመጡ እንደሚያዝኑ ተናግረዋል።
እንደ ቅዱስ ዶሜኒኮስ የበጎ አድራጎት እህቶች ማኅበር፥ የሞት እና የአፈና ፍርሃትን በማሸነፍ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራቸውን ህያው ማድረግ እንደሚችሉ ተናግረው፥ ዕርዳታ የሚያስፈልገውን የሄይቲ ሕዝብ ለመርዳት በምናደርገው ጥረት መካከል በሕይወት መኖር ይሁን መሞት ግዴታቸው እንደሆነ እና የተልዕኳችን ቁልፍ ዓላማ ኢየሱስ ክርስቶስን ማወጅ እንደሆነ አስረድተዋል።
ያላቸውን ትንሿንም ለሌሎች ማቅረብ
የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል ቀጣይነት ያለውን የፍቅር እና የመተሳሰብ ተልዕኮዋቸውን በተጨባጭ ለመኖር ጥረት ማድረጋቸውን የገለጹት እህት ማርያ ማርቴ፥ በትምህርት ማዕከላት በጤና አጠባበቅ ዘርፍ የታመሙትን በመርዳት እና የመከላከያ ፕሮግራሞችን በማካሄድ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በሴንት እስፕሪት ክሊኒክ እርጉዝ ሴቶችን ጨምሮ ለተለያዩ ሕሙማን የሕክምና አገልግሎት፥ የቅድመ ወሊድ እና የወሊድ ምክሮችን፣ የሕፃናት ሕክምና እና የአመጋገብ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ማኅበራቸው በአሁኑ ወቅት ለፕሮግራሙ ማስኬጃ የሚሆን በቂ ምግብ ባይኖርም 125 ሕጻናትን እንደሚንከባከ፣ የክትባት መርሃ ግብሮችን እንደሚያካሂድ እና የስኳር በሽታ እና የደም ግፊት ላለባቸው ሰዎች ዕርዳታን እንደሚሰጥ አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪም ማኅበራቸው ለመልሶ ማቋቋሚያ ፕሮግራሞች ተግባራዊነት አስተዋፅኦን ሊያበረክቱ የሚችሉ፥ የአካል ጉዳተኞችን ለመርዳት ተሽከርካሪ ወንበሮችን ማቅረብ የመሳሰሉ እገዛዎችን እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ሕጻናትን በእድገታቸው ወቅት ለመርዳት የተነደፈ የህፃናት የሕክምና ማዕከል እንዳላቸው የገለጹት እህት ማርያ ማርቴ፥ ከዚህም በተጨማሪም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ልጆች ትምህርት ቤት ገብተው እንዲማሩ የሚያስችል የመዋዕለ ሕፃናት እና የውጭ ትምህርት ዕድል ፕሮግራሞችን እንደሚያካሂዱ ተናግረዋል።
የሕይወት ዋጋን ለሕፃናት በጨዋታ እና በተግባር እንደሚያስተምሩ የገለጹት እህት ማርያ ማርቴ፥ ለሕይወት ክብርን የመስጠት እና የመንከባከብ ባህልን በማሳደግ ቤተሰቦች አመፅን የሚቃወሙ እሴቶችን እንዲማሩ ለማነሳሳት እንደሚሞክሩ ገልጸዋል።
የሕክምና ዕርዳታ መስጠት፣ የትምህርት ዕድል ማመቻቸት፣ ከቤተሰቦች ጋር መሆን እና በሕመማቸው ወቅት ያለማቋረጥ በመካከላቸው መገኘት የተልዕኮዋቸው አካል እንደሆነ የገለጹት እህት ማርያ ማርቴ፥ያላቸው ነገር ትንሽ ቢሆንም እግዚአብሔር የበለጠ ብዙ እንደሚያደርገው እናምናለን ብለዋል።
በአደጋ መካከል ያለ ጥሪን
በጥንቃቄ የማስተዋል ጊዜን በመከተል ወደ አገራቸው ተመልሰው ሕዝባቸውን ለማገልገል እንደጀመሩ የገለጹት እህት ማርያ ማርቴ፥ ምንም እንኳን ፍርሃት እና ስጋት ቢገጥማቸውን፥ “በጸሎት እና ለማኅበረሰባቸው ባላቸው ቁርጠኝነት፣ በተልዕኮ ላይ እንደሚገኙ እና እስካሁን ምንም ዓይነት ክፉ ነገር እናዳላጋጠማቸው፥ ለማኅበረሰቡ የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ትንሽ ቢመስልም በየጊዜ መባዛቱ እንደሚቀጥል ልባቸው እርግጠኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
ተስፋ ያድጋል
ዳቦን እንደ ማባዛት፥ የእህት ማርያ ማርቴ ታሪክ እግዚአብሔር የእኛን ቀላል መስዋዕት ተቀብሎ ወደ ፍቅር ተዓምር እንደሚቀይር የሚያሳይ ተጨባጭ ምሳሌ ነው።
በሄይቲ ገዳማውያት እህቶች ተልዕኮ ኢየሱስ ክርስቶስ ያወጀው የመንግሥቱ ተጨባጭ ምልክት እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ፍቅር ባለበት ብዙ ነገሮችን ማድረግ ይችላል፤ ምክንያቱም እውነተኛ የዳቦው መባዛት በእርሱ ከመታመን፣ ከድነት እና ከፈውስ ፀጋው የሚገኝ ነውና።