MAP

የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚዬም ዓርማ የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚዬም ዓርማ 

የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ጠቅላላ ጉባኤ በኪጋሊ እየተካሄደ ይገኛል

የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚዬም (SECAM) “የተስፋ፣ የእርቅ እና የሰላም ምንጭ የሆነው ክርስቶስ” በሚለው ጭብጥ ላይ ያተኮረ 20ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ ውስጥ እየተካሄደ ሲሆን፥ ከሐምሌ 23-28/2017 ዓ. ም. ድረስ በሚካሄደው በ20ኛው የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከ250 በላይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች ተገኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚዬም ዓላማ የቤተ ክርስቲያኒቱን የመዳን መሣሪያነት ሚናን በማስተዋወቅ እንደ እግዚአብሔር ቤተሰብ በሁሉም የአፍሪካ አገራት እና ደሴቶች ውስጥ ባሉ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች መካከል ኅብረትን፣ መተጋገዝን እና የጋራ ተግባርን ማሳደግ መሆኑን የሲምፖዚዬሙ ፕሬዚዳንት እና የኪንሻሳ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ተናግረዋል።

የሲምፖዚዬሙ የዘንድሮው ጉባኤ ብፁዓን ካርዲናሎችን፣ ጳጳሳትን፣ ካኅናትን፣ ገዳማውያንን እና ገዳማውያትን፣ ከምዕመናን ወገን የተውጣጡ መሪዎችን እና እንዲሁም ከሌሎች አህጉራት የመጡ የአጋር ድርጅቶች ተወካዮችን እያሳተፈ እንደሚገኝ ታውቋል።

በጉባኤው ወቅት ተሳታፊዎቹ በጋና አክራ ውስጥ በ2014 ዓ. ም. ከተካሄደው ጉባኤ ጀምሮ ያሉትን ሂደቶች የሚገመግሙ ሲሆን፥ የዘንድሮ ርዕሦች የጉባኤውን የረዥም ጊዜ ራዕይ ሠነድ ከማቅረብ ጋር በአሥራ ሁለት መሠረታዊ ርዕሦች ላይ እንደሚወያይ እና ከእነዚህም መካከል ስብከተ ወንጌል፣ የቤተሰብ አመራር፣ የወጣቶች ተሳትፎ፣ የፍጥረት እንክብካቤ፣ ዲጂታል ተልዕኮ እና ፖለቲካዊ ኃላፊነት የሚሉት ይገኙበታል።

ጉባኤው በተጨማሪም ከአንድ በላይ ማግባት በሚሉ ውስብስብ ባሕላዊ እውነታዎች ላይ መወያየትን የሚያካትት ሲሆን እንዲሁም በአስተዳደር፣ በፍትህ፣ በሰላም፣ በሃይማኖቶች መካከል በሚደረግ ውይይት፣ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ውይይት እንደሚያደርግ ታውቋል። 20ኛው የሲምፖዚዬሙ ጉባኤ ዋና ነጥብ የ2017/ 2020 የሦስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ይፋ ማድረግ እና እንደ መተዳደሪያ ደንቡ መሠረት አመራሮችን ማደስ እንደሆነ ታውቋል።

የሲምፖዚዬሙ ታሪካዊ አመሠራረት

የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚየም (SECAM) የተመሠረተው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1962-1965 በተካሄደው ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ማግሥት በወጣት የአፍሪካ ጳጳሳት በጎ ፈቃድ እንደ ነበር ሲታወስ በአንድ ድምፅ መናገር ፈለጉ። በዚህ መሠረት የአፍሪካን ራዕይ ለመላዋ ቤተ ክርስቲያን ለማቅረብ የሚያግዝ አህጉራዊ መዋቅርን ለመገንባት ያደረጉት ውሳኔ ውጤት እንደ ሆነ ታውቋል።

እንዲህ ያለ ማኅበር ለአፍሪካ ያለውን ጠቀሜታ በመመልክት በቅድስት መንበር የሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጉባኤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1968 ዓ. ም. የክልል ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ፕሬዚዳንቶች እንዲመክሩበት መጋበዙ ይታወሳል። ከአንድ ዓመት በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚየምን ለመመሥረት መልካም አጋጣሚ ሆኗል።

የሲምፖዚዬሙ መሥራች አባቶች “ጉባኤ” ከሚለው ይልቅ “ሲምፖዚየም” የሚለው በመምረጥ ለኅብረት እና ለወዳጅነት ያላቸውን ፍላጎት ግልጽ አድርገዋል። በግሪክ ሲምፖዚየም የሚለው ቃል ማዕድን የሚያመላክት ሲሆን፥ ብፁዕ ካርዲናል ዞውንግራና በጉባኤው የመክፈቻ ንግግራቸው፥ የወንድማማቾች እና እህትማማቾች ማኅበር የሚሰበሰበውን የቅዱስ ቁርባን መንበረ ታቦት ምስልን በመጠቀም ስለ ሲምፖዚየሙ ጽንሰ ሃሳብ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

31 Jul 2025, 17:15