MAP

በሮም የኢዮቤልዩ በዓላቸውን በማክበር ላይ የሚገኙት ወጣቶች በሮም የኢዮቤልዩ በዓላቸውን በማክበር ላይ የሚገኙት ወጣቶች   (ANSA)

የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል በሮም በድምቀት እየተከበረ ይገኛል

በወጣቶች መንፈሳዊ ነጋዲያን የኢዩቤሊዩ በዓል መርሐ-ግብር መሠረት ከሰኞ ሐምሌ 21-27/2017 ዓ. ም. ድረስ የተለያዩ ዝግጅቶ በሮም ውስጥ በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ታውቋል። ለአንድ ሳምንት በሚቆይ በዚህ በዓል ላይ 146 ሀገራትን የሚወክሉ ከአምስት መቶ ሺህ በላይ ወጣቶች ወጣቶች እንደሚሳተፉ የተገለጸ ሲሆን፥ ከእነዚህ መካከል 78 በመቶ የሚሆኑት ከአውሮፓ፣ 22 በመቶ ግጭት ውስጥ ከሚገኙ እንደ ኢራቅ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሊባኖስ የመጡ፣ የተቀሩት ከሌሎች የዓለማችን ክፍሎች የሚመጡ እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለበዓሉ በወጣው መርሃ-ግብር መሠረት፥ ሰኞ ሐምሌ 21/2017 ዓ. ም. ከጥዋቱ ሦስት ሰዓት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ የአቀባበል እና የምዝገባ ሂደት ከተከናወነ በኋላ ማክሰኞ ሐምሌ 22/2017 ዓ. ም. በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ረዳት ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት በርካታ ወጣቶች ከአመሻሹ አንድ ሰዓት ላይ የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴን ማሳረጋቸው ታውቋል።

ሮም ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ አደባባዮች ላይ በተዘጋጁ መድረኮች የተለያዩ ዝግጅቶች በመቅረብ ላይ እንደሚገኙ የተመለከተ ሲሆን፥ በዚህ መሠረት ረቡዕ እና ሐሙስ ከረፋዱ አራት ሰዓት ተኩል ጀምሮ እስከ አመሻሹ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ የተለያዩ ባሕላዊ፣ ጥበባዊ እና መንፈሳዊ ዝግጅቶ ቀርበዋል።

ዓርብ ሐምሌ 25/2017 ዓ. ም. ከረፋዱ አራት ሰዓት ተኩል እስከ አመሻሹ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ የሕሊና ምርመራ እና የንስሐ ሥነ-ሥርዓት እንደሚፈጸም፣ በነጋታው ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ከዘጠኝ ሰዓት እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ ሮም ውስጥ ቶር ቬርጋታ በተባለ ሰፊ አደባባይ ላይ የመዝናኛ፣ የሙዚቃ እና የሕይወት ምስክርነት ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ ታውቋል።

ከዚያ በመቀጠል ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል እስከ ሦስት ሰዓት ተኩል ድረስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የሚገኙበት የዋዜማ ሥነ-ሥርዓት ከተከናወነ በኋላ እሑድ ሐምሌ 27/2017 ዓ. ም. ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ተኩል ጀምሮ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሚመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት የጎርጎሮሳውያኑ 2025 ዓ. ም. የወጣቶች ኢዩቤሊዩ በዓል የሚጠናቀቅ መሆኑን የኢዮቤልዮ ጠቅላላ መርሐ-ግብር ያመለክታል።

31 Jul 2025, 17:11