የእስራኤል ጦር በጋዛ የሚገኘውን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በቦንብ መደብደቡ ተገለጸ!
የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
በጋዛ ሰርጥ የምትገኘው ብቸኛዋ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን "የቅድስት ቤተሰብ ቤተክርስቲያን" በመባል የምትታወቅ ሲሆን ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም ጠዋት ላይ በታንክ መደብደቧ ተገልጿል። በደረሰባቸው ጉዳት የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉ የተገለጸ ሲሆን የደብሩ ካህን አባ ገብርኤል ሮማኔሊን ጨምሮ ሌሎች ደግሞ ቀላል የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል ተብሏል።
የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ይህንን በተመለከተ ከቫቲካን ዜና ጋር ቆይታ አድርገው ነበር።
"ምንም እንኳን የእስራኤል የጦር ሰራዊ ድርጊቱ በስህተት የተፈጸመ መሆኑን ቢገልጽም፣ በእርግጠኝነት የእስራኤል ጦር ሰራዊት ታንክ ድርጊቱን መፈጸሙን እናውቃለን፥ ነገር ግን ድብደባው የተፈጸመው በስህተት ነው ስለሚለው ስለዚህ ጉዳይ እርግጠኛ አይደለንም፣ እነሱ በቀጥታ ቤተ ክርስቲያኗን፣ የቅዱስ ቤተሰብ ቤተ ክርስቲያን፣ የላቲን ቤተ ክርስትያንን መቱ" ብለዋል። "በከባድ ሁኔታ የቆሰሉ አራት ሰዎች አሉ፣ ከነዚህ አራቱ መካከል ሁለቱ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፣ ሕይወታቸው ከባድ አደጋ ላይ ነው" ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
"እንዲሁም ሌሎች የተጎዱ፣ ነገር ግን ከባድ የሆነ ቁስለት ያልደረሰባቸው ሰዎች አሉ፣ ከነሱም መካከል የሰበካ ቄስ ጨምሮ ሁሉም በቤ ተክርስቲያን ውስጥ ስለነበሩ ነው ይህ አደጋ ሊደርስ የቻለው" ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
"ዛሬ በጋዛ ውስጥ ስለተከሰተው ነገር የተሟላ መረጃ የለንም፣ ምክንያቱም በጋዛ ውስጥ ያለው ኮሙኒኬሽን ያን ያህል ቀላል አይደለም" ያሉ ሲሆን በተቻለ ፍጥነት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት እንደሚሞክሩ ገልጿል።
በፍፁም ብቻቸውን አንተወቸውም
ካርዲናል ፒዛባላ በጣሊያንኛ ቋንቋ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት በጋዛ ለተጎዱት ሰዎች ያላቸውን ቅርበት ገልፀዋል፣ “ሁልጊዜ በማንኛውም መንገድ ጋዛን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለመድረስ እንሞክራለን። አሁን ስለእነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ለመነጋገር ጊዜው በጣም ገና ነው፤ በተለይ ህዝባችንን ለመጠበቅ ምን እንደተፈጠረ፣ ምን መድረግ እንዳለበት በቅድሚያ መረዳት አለብን" ብለዋል።
ቀደም ሲል፣ የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ቤተ ክርስቲያኗ “በወረራ መመታቷን” የሚያረጋግጥ ጋዜጣዊ መግለጫ X በተሰኘው የቲውተር ገጻቸው ላይ አውጥተው ነበር። መግለጫው በአሁኑ ጊዜ “የተረጋገጠ የሞቱ ሰዎች ቁጥር መናገር አዳጋች ነው ብለዋል” ብሏል፣ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኗ ላይ ጉዳት አድርሷል ሲል መግለጫው አትቷል።
የካቶሊክ ፕሬስ ኤጀንሲ SIR እንደዘገበው፣ የቅድስት ቤተሰብ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ወቅት 500 የሚደርሱ የተፈናቀሉ ክርስቲያኖችን እያስተናገደች ትገኛለች።
ሞት፣ ስቃይ እና ውድመት በየቦታው አሉ።
በእለቱ በX የቲውተር ገጽ ላይ በተለጠፈው የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ በሰጡት መግለጫ “በቅዱስ ቤተሰብ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሰዎች ቤታቸው፣ ንብረታቸውና ክብራቸው ከተነጠቀ በኋላ በጦርነት አስፈሪነት የተነሳ ቢያንስ ሕይወታቸውን ሊተርፍ ይችላል ብለው በማሰብ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተጠለሉ ሰዎች ናቸው" ሲል መግለጫው አክሎ ገልጿል።
ለሟች ቤተሰቦች የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ "በመላው የቅድስት ሀገር ቤተ ክርስቲያን ስም" የቅዱስ ፓትርያርኩ ጸሎት እና ወረራውን በማውገዝ ጋዛን እና ህዝቦቿን ካጠፉት በርካታ ጥቃቶች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
መግለጫው "የላቲን ፓትርያርክ ይህንን አሳዛኝ እና ይህን በንጹሀን ዜጎች እና በተቀደሰ ቦታ ላይ ያነጣጠረ ጥቃትን አጥብቆ ያወግዛል። ሆኖም ይህ አሳዛኝ ክስተት በጋዛ ላይ በሰዎች ላይ ከደረሱት ሌሎች በርካታ ጥቃቶች የበለጠ ወይም አስፈሪ ብቻ አይደለም። ሌሎች ብዙ ንጹሃን ዜጎችም ተጎድተዋል፣ ተፈናቅለዋል እና ተገድለዋል። ሞት፣ ስቃይ እና ውድመት በሁሉም ቦታ አለ "ሲል መግለጫው አስነብቧል።
ተማͽኖ
በአስቸኳይ ተማͽኖ ጥሪውን የጀመረው መግለጫው “ይህን በሰውና በሥነ ምግባራር ላይ እየተፈጸመ የሚገኘውን ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት ለመግታት መሪዎች ድምፃቸውን የሚያሰሙበትና አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርጉበት ጊዜ ደርሷል” ብሏል።
"ይህ አሰቃቂ ጦርነት የሰውን ልጅ ክብር ወደ ነበረበት ለመመለስ ረዥሙን ስራ እንጀምር ዘንድ ሙሉ በሙሉ ማብቃት አለበት" ሲል መግለጫው አክሎ ገልጿል።
የላቲን ፓትርያርክ “በዚህ አሳዛኝ ሰዓት” ሟቾችን እየቀበሩ ያሉትን ለቤተ ክርስቲያኗ አባላት ያላቸውን ቅርበት ደጋግመው የገለጹት ሲሆን፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላሳዩት የአብሮነት እና የመቀራረብ መገለጫዎች ሁሉ አድናቆታቸውን ገልጸው ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ሕዝቡን ብቻውን እንደማይተውት በድጋሚ ቃል ገብተዋል።
"ከጋዛ ማህበረሰብ ጎን መቆማችንን እንቀጥላለን እና እነሱን ለመደገፍ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን" ሲል በመግለጫው አክለው መግለጻቸውም ተዘግቧል።