MAP

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ራያን ጂሜኔዝ፥ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ራያን ጂሜኔዝ፥  

በፓስፊክ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ትንሽ ብትሆንም አስደናቂ የአምልኮ ሥርዓቶች እንዳሏት ተገለጸ

በምዕራብ ፓሲፊክ ውቅያኖስ የአጋና ጉዋም ደሴት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ራያን ጂሜኔዝ፥ በቅርቡ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር ስላደረጉት ስብሰባ እና በፓስፊክ ውቅያኖስ ያለውን የሕይወት ውጣ ውረድ እና ደስታን በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያጎላ ጥንታዊ የሥርዓተ አምልኮ አልባሳትን ለመቀበል በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ እሑድ ሰኔ 22/2017 ዓ. ም. ከተገኙት 54 የሜትሮፖሊታን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል የአጋና ጓም ሊቀ ጳጳስ አቡነ ራያን ጂሜኔዝ ይገኙበታል።

የ53 ዓመት ዕድሜ ሊቀ ጳጳስ ፊሊፒናዊ ተወላጅ አቡነ ራያን ጂሜኔዝ፥ የፓስፊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ (ሲኢፒኤሲ) ፕሬዝደንት ሲሆኑ፥ ጉባኤው በዓለም ውስጥ ከሚገኙ የካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች መካከል ትልቁ እንደሆነ ይታወቃል።

በ17 ሀገረ ስብከቶች ተዋቅሮ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በሚሾሙት ጳጳስ የሚመራ ይህ ራስ ገዝ ሐዋርያዊ አስተዳደር፥ ሰፊውን የፓስፊክ ውቅያኖስ አካባቢ የሚያጠቃልል እና የአሜሪካ ግዛት ከሆነችው ጉዋም በስተምዕራብ በኩል እስከ ደቡብ ምሥራቅ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ታሂቲ ደሴት ድረስ ያለውን ቦታ የሚያጠቃልል ነው።

የሎጂስቲክስ ችግሮች

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ራያን ጂሜኔዝ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ክልሉ ልዩ ልዩ አካባቢዎችን የሚያካትት ሰፊ ክልል በመሆኑ በሐዋርያዊ አስተዳደር ላይ ጫናን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው፥ በክልሉ የሚገኙ ደሴቶች በአንፃራዊነት እርስ በርስ የሚቀራረቡም ቢሆንም ወደ እያንዳንዱ ደሴት ለመድረስ የሚደረግ የአውሮፕላን ጉዞ እጅግ ውድ በመሆኑ የተነሳ የክልሉ ጳጳሳት በየሁለት ዓመት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ እንደሚገናኙ አስረድተዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ራያን ጂሜኔዝ በአካባቢው ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በሚካሄዱ የፓስፊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ላይ ዘወትር የተወሰኑ ጳጳሳት እንደማይገኙ ገልጸው፥ ይህም የሚሆነው የበረራ ቲኬት ለመግዛት አቅም ባለመኖራቸው እንደሆነ ተናግረው፥ “የበይነ-መረብ ላይ ግንኙነት እንኳ ቢሆን ከችግር የጸዳ እንዳልሆነ እና በመስመር መቋረት የተነሳ ብዙውን ጊዜ ስብሰባዎች በድንገት እንደሚቋረጡ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ራያን ጂሜኔዝ ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው የጎርፍ መጥለቅለቅ
የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው የጎርፍ መጥለቅለቅ   (AFP or licensors)

የአየር ንብረት ለውጥ እና ስደት

በክልሉ ውስጥ ትልቁ ችግር የአየር ንብረት ለውጥ ሲሆን ይህም የባሕር ከፍታ መጨመርን ማስከተሉን እና በውቅያኖስ ሙቀት መጨመር እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተለይም ዝቅተኛ የፓስፊክ ውቅያኖስ ደሴቶች በከባድ ችግር ውስጥ እንደሚወድቁ አስረድተዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ራያን ጂሜኔዝ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በተፈጸመው ሥነ-ሥርዓት ላይ ጥንታዊ የሥርዓተ አምልኮ አልባሳትን ከተቀበሉ ከጥቂት ቀናት በኋላ ረቡዕ ሰኔ 25/2017 ዓ. ም. ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር በግል መገናኘታቸውን እና ቀደም ብሎም በቱቫሉ የሚገኙ አንድ የሐዋርያዊ አገልግሎት ባልደረባ፥ “በከባድ ችግር ውስጥ እንደምንገኝ ለቅዱስነታቸው ንገሩልኝ” ማለታቸውንም ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ራያን ጂሜኔዝ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ውይይት ካደረጉባቸው አጄንዳዎች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ እና ስደት ትልቅ ትኩረት የተሰጡባቸው እንደ ነበር ታውቋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ራያን ጂሜኔዝ በሁለቱ ክስተቶች መካከል ላለው የጠበቀ ግንኙነት አፅንዖት ሲሰጡ እንደተናገሩት፥ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በርካታ የፓሲፊክ ደሴት ነዋሪዎች ወደ አውስትራሊያ ለመሰደድ መገደዳቸውን ጠቁመዋል።

በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት መኖሩን የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ራያን ጂሜኔዝ፥ ነዋሪዎቹ የተወለዱበትን እና ያደጉበትን አካባቢ መልቀቅ እንደማይፈልጉ፥ በሌላ ወገን “ቤታቸው ቀስ በቀስ በውሃ እየተሸፈነ በመምጣቱ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው ከመሄድ ሌላ ምንም አማራጭ የላቸውም” ብለዋል።

ነፍስሔር ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በአካባቢው ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት
ነፍስሔር ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በአካባቢው ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት   (AFP or licensors)

የአካባቢው ቀለም እና ውበት

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ራያን ጂሜኔዝ፥ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ከማጠቃለላቸው በፊት እንደተናገሩት፥ በፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ ስለሚኖሩት ተግዳሮቶች ብዙ ከማሰብ ይልቅ ስለ ደስታም መወያየት አስፈላጊ እንደ ሆነ ገልጸዋል።

ከደስታዎቹ መካከል በጉዋም ከቻሞሮ እስከ ካሮሊኒያን ድረስ ባለው ሀገረ ስብከት ውስጥ የተለያዩ አገር በቀል ጎሳዎች ወይም ቡድኖች መገኘታቸውን ገልጸው፥ “ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው፥ ምክንያቱም የእያንዳንዱ አካባቢ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በባሕሎቻቸው መካከል ያለውን ልዩነት የሚገልጽ በመሆኑ እና ልዩነቱ በቤተ ክርስቲያን ሁሉ አቀፍነት ውስጥ ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ራያን ጂሜኔዝ በተጨማሪም፥ በፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ በሚገኙ አብዛኛዎቹ ክልሎች ውስጥ ያለች ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዝቅተኛ የምዕመና ቁጥር ያላት ቢሆንም ነገር ግን በጥራት ቀዳሚ፣ በሚያምሩ አስደናቂ ቀለማት ያሸበረቁ ረዥም የአምልኮ ሥርዓቶች እንዳላት አስረድተዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ራያን ጂሜኔዝ፥ እሑድ ሰኔ 22/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በተፈጸመው ሥነ-ሥርዓት ላይ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያጎሉ ጥንታዊ የሥርዓተ አምልኮ አልባሳትን በተቀበሉ ዕለት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር በአጭር ለመነጋገር ዕድል እንደ ነበራቸው አስታውሰው፥ ቅዱስነታቸው በዚህ ወቅት፥ “በሀገረ ስብከትህ ውስጥ ብዙ ፈተናዎች ያሉብህ ቢሆንም ነገር ግን እግዚአብሔር ዘወትር ካንተ ጋር እንዳለ እወቅ” ማለታቸው አስታውሰዋል።

 

07 Jul 2025, 17:02