ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ቤተ ክርስቲያን መከራ ውስጥ የሚገኙትን የጋዛን ህዝብ በፍጹም አትተዋቸውም አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ማክሰኞ ዕለት እንደተናገሩት “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጋዛ ተለይቶ አያውቅም” ያሉ ሲሆን፥ ኢየሱስ ዘወትር በሥፍራው እንደሚገኝ፣ በመስቀሉ ቁስል ከቆሰሉት ጋር፣ በፍርስራሹ ውስጥ ተቀብረው ከሚገኙት፣ እንዲሁም በእያንዳንዱ የምሕረት ተግባር ውስጥ፣ በእያንዳንዱ በጨለማ ውስጥ የሚበራ ሻማ እና እጆቻቸው ለመከራ በተዘረጉ ሰዎች ውስጥ እንደሚኖር ገልጸዋል።
የእየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ሣልሳዊ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ወደ ስፍራው የመጡት የቤተክርስቲያን መሪዎች በቅርቡ በጋዛ ያደረጉትን የሃዋሪያዊ ጉብኝት ተከትሎ እንደሆነ ገልጸው፥ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በመክፈቻ ንግግራቸው ሁለቱ ፓትርያርኮች በጦርነት ወደምትታመሰው የፍልስጤም ግዛት የመጡት እንደ ፖለቲከኛ ወይም ዲፕሎማት ሳይሆን እንደ ቤተክርስቲያ መሪ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን፥ ተልእኳቸው ለአንድ የተወሰነ ቡድን ሳይሆን ለሁሉም “ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞች፣ አማኞች፣ ስደተኞች እና ህፃናት” መሆኑን በማጉላት፥ ቤተክርስቲያን የጋዛን ህዝብ በፍጹም እንደማትተው አጥብቀው ተናግረዋል።
‘መከራ የደረሰበት የክርስቶስ አካል አገልጋዮች’
ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ሳልሳዊ በበኩላቸው ወደ ሥፍራው የመጡት “መከራ የደረሰበት የክርስቶስ አካል አገልጋዮች” ሆነው እንደሆነ ገልጸው፥ ምንም ዓይነት መከራ ቢደርስባቸውም ክብራቸው ሳይናወጥ በአከባቢው በሚገኙ በቆሰሉት፣ በሐዘንተኞች፣ በተፈናቀሉት እና በምእመናን መካከል ለመገኘት ወደ ጋዛ እንደመጡ በመጥቀስ የብጹእ ካርዲናሉን ስሜት አስተጋብተዋል።
ብጹእነታቸው አክለውም በጋዛ ባደረጉት ሃዋሪያዊ ጉብኝት በከባዱ ጦርነት ምክንያት መከራ የደረሰባቸው፣ በውስጣቸው ግን የእግዚአብሔርን መልክ የሚያንፀባርቁ ሕዝቦች እንዳጋጠሟቸው ገልጸዋል።
የግሪክ ኦርቶዶክሱ ፓትርያርክ “ቤተ ክርስቲያን በጥፋት ጊዜ የምትሰጠው ተልእኮ የተመሠረተው በመገኘት አገልግሎት፣ ከሚያዝኑ ጋር በመቆም፣ የሕይወትን ቅድስና በመጠበቅ እና ዬትኛውም ጨለማ የማይቋቋመውን ብርሃንን በመመስከር ላይ ነው” ብለዋል።
ሰብዓዊ እርዳታ የህይወት ወይም የሞት ጉዳይ መሆኑ
ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በበኩላቸው የሰው ልጅን ከዚህ የመከራ ባህር ውስጥ ለማውጣት ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ለሚታገሉ ለሁሉም የሰብአዊነት ተዋናዮች ቤተክርስቲያን የምትሰጠውን ድጋፍ አፅንዖት ሰጥተው በማረጋገጥ፥ ‘የሰብአዊ እርዳታ አስፈላጊ የሚባል ብቻ ሳይሆን የህይወት እና የሞት ጉዳይ ነው’ ብለዋል።
ይሄንን አለመቀበል አደገኛ መሆኑን የገለጹት ብጹእነታቸው፥ ያለ ምግብ፣ ውሃ፣ መድኃኒት እና መጠለያ መቆየት በየሰዓቱ ለከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ አስታውሰው፥ “ሰብአዊ እርዳታን መከልከል ከሥነ ምግባር አኳያ ተቀባይነት የሌለውና ምክንያታዊነት የጎደለው ነው” ብለዋል።
ጦርነቱ እንዲቆም የተደረገ የጋራ ጥሪ
በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ሁለቱ ፓትርያርኮች ለዓለም መሪዎች እና ውሳኔ ሰጪዎች በጋራ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ ‘ጦርነቱ እንዲቆም፣ እስረኞች እንዲፈቱ እንዲሁም ለጋዛ እና ለመላው ቅድስት ምድር ህይወትን እና ክብርን የሚያድስ እውነተኛ የፈውስ ሂደት’ እንዲጀመር ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱ የቤተክርስቲያን መሪዎች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ባለፈው እሑድ ሐምሌ 13 ቀን 2017 ዓ. ም. በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ግቢ ውስጥ ከተገኙት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባደረሱበት ወቅት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያስተላለፉትን ጥሪ በማስተጋባት ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ እንዲከበር፣ ሰላማዊ ሰዎችን የመጠበቅ ግዴታን እንዲያከብሩ፣ እንዲሁም የወል ቅጣትን የሚከለክለውን ህግ እንዲያከብሩ፣ ብሎም ከልክ በላይ የሆነ የኃይል አጠቃቀምን እና ህዝቡን በግዳጅ እንዲፈናቀሉ ማድረግን ማቆም እንደሚገባ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
“ይህን ከንቱ ጦርነት የምናስቆምበት እና የሰዎችን የጋራ ጥቅም የምናስቀድምበት ጊዜ አሁን ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ፣ እርሳቸውና ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ሳልሳዊ “ነጻነት የተነፈጉት ሁሉ እንዲፈቱ፣ የጠፉት እንዲመለሱ፣ የታሰሩት እና በሁሉም አቅጣጫ ለረጅም ጊዜ በትዕግሥት የቆዩ ቤተሰቦች ፈውስ እንዲመጣላቸው” ሲጸልዩ እና ጥሪ ሲያቀርቡ እንደ ነበር አስታውሰዋል።
ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ በበኩላቸው ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ባስተላለፉት መልዕክት ‘ሌሎች በመከራ ውስጥ በሚገኙበት ጊዜ ዝም ማለት ሕሊናን መክዳት እንደሆነ’ ጠቅሰው፥ ቤተ ክርስቲያን ሁሌም ቢሆን ከጋዛ ህፃናት ጎን እንደምትቆም ካረጋገጡ በኋላ፣ በመጨረሻም “ሰላም ፈጣሪዎች ብፁዓን ናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” በማለት ኃይልን ያለአግባብ ለሚጠቀሙ ሁሉ የጌታን ትእዛዝ በቀጥታ በማስተጋባት አጠቃለዋል።