ብጹዕ አቡነ አልቤርቶ፥ አፈሳን በመፍራት ከቅዳሴ የሚቀሩ ምዕመናን ጉዳይ በማስመልከት ውሳኔ አሳለፉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
አቡነ አልቤርቶ ሮያስ፥ ሐምሌ 1/2017 ዓ. ም. ውሳኔያቸውን ይፋ ያደረጉት ስደተኛ ካቶሊካዊ ምዕመናን የሚወሰድባቸውን እርምጃ በመፍራት መካፈል ካለባቸው የእሁድ መስዋዕተ ቅዳሴ የሚቀሩ ምዕመናን ሁኔታ በማገናዘብ ሲሆን፥ የሚቀጥለው ከፍተኛ አስገዳጅ ሕግ እስኪወጣ ድረስ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ መገኘት እንደሚገባ አሳስበዋል።
“በቁምስናችን ውስጥ በርካታ ምዕመናን በማንኛውም ዓይነት ሕዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ቢገኙ በስደተኞች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት መኰንኖች ተይዘው የመታሰር ከፍተኛ ስጋት አለ” ያሉት አቡነ አልቤርቶ ሮያስ፥ ቅጣቱ በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ የሚገኙትንም የሚጨምር መሆኑን ለመገናኛ ብዙኃን ሐምሌ 3/2017 ዓ. ም. ከሰጡት መግለጫ ጋር ይፋ ባደረጉት ውሳኔ እንደሆነ ታውቋል።
አቡነ አልቤርቶ ሮያስ፥ ለስደተኛ የምዕመናን ማኅበረሰብ ባስተላለፉት የማበረታች ቃል፥ “በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ቤተ ክርስቲያናችን ከምዕመናኑ ጋር መቆሟን እና አብራቸው መጓዟን እንዲያውቁ እፈልጋለሁ” ብለዋል።
የስተኞች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት መኰንኖች ይዞታነቱ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በሆኑ የሞንትክሌር እና ሃይላንድ ሁለት ቁምስናዎች ውስጥ በመግባት በርካታ ሰዎችን እንደያዙ የሀገረ ስብከቱ ሃላፊዎች ሰኔ 13/2017 ዓ. ም. ተናግረዋል።
የሳን ቤርናርዲኖ ሀገረ ስብከት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ጆን አንድሪው፥ በወቅቱ አንድ ምእመን ወደ እስር ቤት መወሰዱን ገልጸው፣ ወደ እስር ቤት የተወሰዱት የተቀሩት ሰዎች የቁምስናው አባላት ወይም በቁምስናው ውስጥ የሚሠሩ እንዳልሆኑ ተናግረዋል።
አቡነ አልቤርቶ ሮያስ በቅርቡ ባስተላለፉት መልዕክት፥ እነዚህ ክስተቶች በብዙ ስደተኛ ምዕምናን ውስጥ ፍርሃት እንዲጨምር ማድረጋቸውን አብራርተው፥ ቀደም ሲል በሰኔ 16/2017 ዓ. ም. በጻፉት መልዕክት፥ “የፖለቲካ መሪዎች እና ውሳኔ ሰጪዎች እነዚህን ዘዴዎች እንደገና በማጤን እንዲያስቆሙ እና ሰብዓዊ መብቶችን እና ክብርን የሚያስጠብቅ አቀራረብ ቶሎ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ለሰፊው ማኅበረሰብ ደህንነት አስተዋፅዖ የሚያደርጉ ሰዎች
አቡነ አልቤርቶ ሮያስ በሐምሌ 3/2017 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ስደተኛ ማኅበረሰቦች፥ በዚህች ሀገር ውስጥ ለዓመታት ያህል በህጋዊነት ከመኖር ሌላ ምንም ዓይነት ጉዳይ የሌላቸው፣ ለሰፊው ማኅበረሰብ ደህንነት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ናቸው” ብለው፥ በማከልም “ወደዚህ የመጡት አብዛኛዎቹ ስደተኞች ሌላ ምንም አማራጭ የሌላቸው እና ሕጋዊነት ኖሯቸው ቤተሰቦቻቸውን ከመከራ ለማዳን የሚፈልጉ ቢሆኑም ነገር ግን ማን ሊረዳቸው ይችላል?” ሲሉ ጠይቀዋል።
አቡነ አልቤርቶ ሮያስ በመልዕክታቸው፥ የስደተኞች ደንብ ማስፈጸሚያ እርምጃዎች ማለትም በአሜሪካ መንግሥት የተዘረጋው የኢሚግሬሽን እና የጉምሩክ ደንብ፥ ወረራን እና ፍርሃትን በማስከተል ከባድ ችግር ሊሆን እንደሚችል እና ለምእመናን መንፈሳዊ በጎነትም እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል በማስገንዘብ፥ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ መገኘት ያልቻሉት ስደተኛ ምዕመናን ከኢየሱስ ክርስቶስ እና ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር ያላቸውን መንፈሳዊ ግንኙነት በሌላ መንገድ እንዲያጠናክሩ በማለት በመልዕክታቸው አበረታተዋል።
“የግል ጸሎት ማቅረብን፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ የመቁጠሪያ ጸሎት ማቅረብ ወይም መስዋዕተ ቅዳሴን በቴሌቪዥን ስርጭት ወይም በማኅበራዊ መገናኛዎች በቀጥታ እንዲከታተሉ” በማለት ሃሳባቸውን አቅርበዋል።
ሐዋርያዊ አገልጋዮች በርኅራሄ የተሞላ ድጋፍ ሊሰጡ ይገባል
በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ የሚገኘው ስድስተኛው ትልቁ የሳን ቤርናርዲኖ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ አልቤርቶ ሮያስ በመልዕክታቸው፥ እነዚህን ምዕመን እያጋጠሟቸው ያለውን ጭንቀት እና ፍርሃት ግምት ውስጥ በማስገባት፥ በእሁድ ዕለት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የመገኘት ካቶሊክ ግዴታ መወጣት ባለመቻላቸው የሚሰማቸውን ሸክም ለማቃለል እንደሚፈልጉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አቡነ አልቤርቶ ሮያስ በመልዕክታቸው ላይ፥ የሀገረ ስብከቱ ሐዋርያዊ አገልጋዮች እና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባላት፥ በመንግሥት ውሳኔ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ርኅራሄን በማሳየት፣ በማኅበረሰቦቻቸው ውስጥ ተቀባይነት ያላቸው መሆኑ እንዲሰማቸው ለማድረግ የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
በካሊፎርኒያ የሳን ቤርናርዲኖ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ አልቤርቶ ሮያስ፥ በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ የሚገኙ ቁምስናዎች፥ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን በተከታታይ ማግኘት ለማይችሉ ምእመናን ትምህርተ ክርስቶስን እና ቅዱሳት ምስጢራትን እንዲቀበሉ ለማዘጋጀት ሌሎች አማራጮችን እንዲፈልጉ አደራ ብለዋል።