MAP

በሜክሲኮ የአናፕራ ነዋሪ የሆነች ህፃን ልጅ አሜሪካ ውስጥ ካለ ሌላ ሰው ጋር ሁለቱን ሃገራት ከሚለየው የድንበር አጥር በኩል እጅ ለእጅ ሲነካኩ በሜክሲኮ የአናፕራ ነዋሪ የሆነች ህፃን ልጅ አሜሪካ ውስጥ ካለ ሌላ ሰው ጋር ሁለቱን ሃገራት ከሚለየው የድንበር አጥር በኩል እጅ ለእጅ ሲነካኩ  (AFP or licensors)

የአሜሪካ ብጹአን ጳጳሳት ነፍሰ-ጡር እናቶችን እና ልጆቻቸውን መጠበቅ እንደሚገባ አሳሰቡ

የዩናይትድ ስቴትስ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ የትራምፕ አስተዳደር ነፍሰ ጡር እና ድህረ ወሊድ እናቶችን አስመልክቶ በአሜሪካ የጉምሩክ እና የድንበር ጥበቃ ስር ያሉትን ነባር ፖሊሲዎች በመሻሩ ምክንያት ይህን በመቃወም መግለጫዊ ምላሽ ሰጥተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ (USCCB) የትራምፕ አስተዳደር በቅርቡ የዩናይትድ ስቴትስ የጉምሩክ እና የድንበር ጥበቃ (CBP) መመሪያን በመሻር ነፍሰ ጡር እና ድህረ ወሊድ ሴቶች እንዲሁም አዲስ የተወለዱ ልጆቻቸው በተቋሙ ቁጥጥር ስር እያሉ ያገኙት የነበረውን ጥቅም መከልከሉን በማስመልከት ምላሽ ሰጥቷል።

መሰረታዊ ፍላጎቶችን መካድ 'ይቅር የማይባል' ጉዳይ ነው
በቴክሳስ ግዛት የኤል ፓሶ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ማርክ ሴይትዝ በዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ የስነ-ህይወት እንቅስቃሴዎች ኮሚቴ ሊቀመንበር ሲሆኑ፥ “የነፍሰ ጡር እናቶችን እና ጨቅላ ልጆቻቸውን መሰረታዊ ደህንነት ለመጠበቅ የታቀዱ እርምጃዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር እያሉ መሰረዙ “በጣም አሳሳቢ እና ይቅር የማይባል ጉዳይ” መሆኑን ጠቁመዋል።

የተሻረው ፖሊሲ ለእነዚህ ሴቶች እና ህጻናት ልጆቻቸው በዩናይትድ ስቴትስ የጉምሩክ እና የድንበር ጥበቃ ቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎች ዝቅተኛ የእንክብካቤ መስፈርቶች የተባሉትን እንደ ምግብ፣ ውሃ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ የመኝታ ቦታ እና መደበኛ ክትትል እንዲሁም “በተቻለው አቅም የተመቻቸ ማረፊያ ቦታዎችን እንዲያገኙ የሚያስችሉ መስፈርቶችን አስቀምጧል።

ፖሊሲውን ለመሻር የቀረበው ምክንያት “ጊዜ ያለፈበት ወይም አሁን ካለው የኤጀንሲው መመሪያ እና የኢሚግሬሽን ማስፈጸሚያ ቅድመ ሁኔታዎች ጋር የተዛመደ ነው” የሚል እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህ በተጨማሪ በቁጥጥር ስር ሆነው በህክምና ላይ ያሉ ግለሰቦችን እንክብካቤን በተመለከተ ሌላ ፖሊሲም እንደተሰረዘ እና የተሻሩትን ለመተካት የሚያስችል ሌላ መመሪያ እንዳልቀረበም ጭምር ተገልጿል።

የስደተኞች እስራት የተረጋገጠ ጉዳት
ብጹአን ጳጳሳቱ በመግለጫቸው “የስደተኞች እስራት በቤተሰብ እና በተለይም በትናንሽ ሕፃናት ላይ እያደረሰ ስላለው የተረጋገጠ ጉዳትን” አስመልክተው መልእክታቸውን ደጋግመው በመግለጽ፥ ባለማወቅም እንኳን ቢሆን የእናቶችን እና የልጆቻቸውን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ የቸልተኝነት እና የትንኮሳ ሁኔታዎች መኖራቸውን አስጠንቅቀዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ብጹአን ጳጳሳት ፖሊሲዎቹን የመሻር ውሳኔን በተመለከተ “አስተዳደሩ በተመሳሳይ ሁኔታ ደህንነቱ በተጠበቀ እና የበለጠ ወጪ ቆጣቢ በሆኑ የእስር አማራጮች ምትክ የቤተሰብ እስራትን ያጠናክራል” በማለት በአፅንዖት ገልጸዋል።

መግለጫው “ነፍሰ ጡር እናቶችንና ልጆቻቸውን መጠበቅ ‘ጊዜ ያለፈበት’ ተደርጎ ሊወሰድ እንደማይችል በማሳሰብ፥ ከዚህም በተጨማሪ ብጹአን ጳጳሳቱ “ይህ በማያሻማ ሁኔታ በስደት ቁጥጥር ውስጥ ያሉ እና ዜግነት የሌላቸው ዜጎችም ቢሆኑ ከአምላክ የተሰጣቸው ክብር ስላላቸው እነሱንም የሚመለከት ጉዳይ ነው ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ መግለጫ በመጨረሻም አስተዳደሩ “በመንግስት ቁጥጥር ስር እያሉ” ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ህዝቦችን እንክብካቤ እና ጥበቃን ለመጨመር መመሪያ አዲስ እንዲያወጣ በማሳሰብ አጠቃሏል።
 

22 May 2025, 16:19