MAP

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኒኮላይ ጌናዴቪች ዱቢኒን፥ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኒኮላይ ጌናዴቪች ዱቢኒን፥ 

የሩሲያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ የሰላም ጥረት መደሰቷን ገለጸች

በሞስኮ የአምላክ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ረዳት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኒኮላይ ጌናዴቪች ዱቢኒን፥ ለቫቲካን ዜና እንደገለጹት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የጦር መሣሪያ ትጥቅ የሚያስፈታ ሰላም እንዲመጣ ያቀረቡት ጥሪ የሩስያን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን እና ሕዝብን ማስደሰቱን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የካቶሊካዊት ቤተ ክስቲያን ሐዋርያዊ መሪ ሆነው በተመረጡበት ሚያዝያ 30/2017 ዓ. ም.  ምሽት ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ማዕከላዊ ሰገነት ላይ ሆነው ያሰሙት የሰላም ንግግር የብዙ ሩሲያውን ልብ መንካቱ አይዘነጋም።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኒኮላይ ጌናዴቪች፥ ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባደረጉት ንግግር፥ የጦር መሣሪያ ትጥቅ ተፈትቶ ሰላም እንዲመጣ በማለት ያቀረቡት አቤቱታ እና ፅንሰ-ሀሳብ አድናቆት በማግኘት የሰላም ተስፋ መፍጠሩን ተናግረዋል።

በሞስኮ የአምላክ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ረዳት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኒኮላይ ጌናዴቪች አክለውም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለአንድነት በሰጡትን ትኩረት ብዙ ሩሲያውያን አድንቆታቸውን መግለጻቸውን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪነት አገልግሎታቸውን በጀመሩበት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከታቸው ስለ አንድነት ከስምንት ጊዜ ያላነሰ ደጋግመው መናገራቸው ለቤተ ክርስቲያናችን ብቻ ሳይሆን ለመላው ኅብረተሰብ ጠቃሚ ምክር ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

ታላቅ የመጽናኛ ምክር

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኒኮላይ ዱቢኒን በማከልም፥ የእርስ በርስ ውይይት፣ አንድነት እና የሚስዮናዊነት ቅንዓት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ካነሷቸው ሌሎች ቁልፍ ጭብጦች መካከል ጥቂቶቹ እንደ ነበሩ ገልጸው፥

“እነዚህ ጭብጦች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ቀጣይነት ያለው መስመር መኖሩን የሚያሳዩ፥ ትልቅ መፅናኛ እና አዲስ መነሳሳትን የሚሰጡን ናቸው” ሲሉ ተናግረው፥ “በግጭት የተፈተነች ቤተ ክርስቲያን ቁስል የሚፈውስ እና ጠብ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ያለማቋረጥ መጸለይ እንደሚገባ የሚያሳስቡም ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኒኮላይ ዱቢኒን፥ ቁምስናዎች ብሔራዊ፣ ባሕላዊ እና የአመለካከት አንድነት ምሳሌዎች በመሆናቸው የሩሲያ ቤተ ክርስቲያን ከፓርቲያዊ ክፍፍል በላይ ለመሆን የምትፈልግ መሆኗን አስረድተዋል።

“በዚህ ሁኔታ የሩሲያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሰዎችን ሕመም እና ስቃይ ሁሉ ትካፈላለች” ብለው፥ አስከፊ ክስተቶችን በቀጥታ መቀየር አለመቻላቸው በጥልቅ እንደሚሰማቸው፥ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ እየተመራን በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሰላም ጥረት እንተማመናለን” ብለዋል።

ለሰላም የተከፈተ ልብ ያላቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት

አዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በተመረጡበት ዕለት አብዛኛው የሩሲያ ማኅበረሰብ፣ ሌላው ቀርቶ ከቤተ ክርስቲያን ርቀው የሚገኙትም ጭምር ወዲያውኑ ጥሩ ስሜት በፈጠሩት ጳጳስ በመገረም አድንቆታቸውን መግለጻቸው ተነግሯል።

“ይህን ብዙ ሰዎች ገልጸውልኛል” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኒኮላይ ዱቢኒን፥ ወጣት፣ ጉልበት እና ጥልቅ ስብዕና ያላቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሲመለከቱ ብዙዎች እጅግ መገረማቸውን ገልጸው፥ የተከፈተ ልብ ኖሯቸው የሌሎችን ልብ ሊከፍቱ የሚችሉ ሰው እንደሆኑ እና ይህ ደግሞ በኅብረተሰባቸው ውስጥ ያሉትን ፍርሃቶች ለማሸነፍ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።

ለሩስያ ነጋዲያን ባስተላለፉት መልዕክትም፥ የሮም ከተማ ነዋሪዎች ጠባቂ የሆነች የእመቤታችን ቅዱስ ምስል ቅጂ  በመላው ሩሲያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን የሚጎብኙት እንደሆነ ጠቁመው፥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል፥ በርካታ የሩስያ ካቶሊካዊ ምእመናን የኢዮቤልዩ በዓልን ለማክበር ወደ ሮም መምጣት የማይችሉ መሆናቸውን በመገንዘብ በሞስኮ ካቴድራል ውስጥ እንዲቀመጥ ብለው የሰጡት የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስጦታ እንደሆነ ገልጸዋል።

የጋራ ውይይት አስፈላጊነት

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኒኮላይ ዱቢኒን፥ በሃይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረገውን ውይይትን በማስመልከት እንደተናገሩት፥ የሙስሊሞች ቡድን “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን!” የሚለውን የንፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ የወንድማማችነት እና የማህበራዊ ወዳጅነት ሠነድ ወደ አገሩ ቋንቋ መተርጎማቸውን ገልጸዋል።

“ሠነዱን ወደ ሩስያ ቋንቋ እየተረጎምን በምንገኝበት ወቅት ሙስሊሞች ቀድመው ተርጉመው ማሳተማቸው አስደስቶናል” ብለው፥ እንደዚህ ያለ ነገር ሲከሰት በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ እና ሠነዱ የውይይት መንፈስን በመቀስቀስ ሙስሊሞችም የሐዋርያዊ ሠነድ መልዕክት ለሰው ልጆች በሙሉ እንደሚናገር መገንዘባቸውን አስረድተዋል።

 

22 May 2025, 17:16