ሮም የምሥራቅ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት ኢዮቤልዩ በዓልን በማስተናገድ ላይ እንደምትገኝ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በቫቲካን ከግንቦት 4-6/2017 ዓ. ም. ድረስ በተከታታይ በሚከበረው የኢዮቤልዩ በዓል ላይ የምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን እና ቤተ ክኅነት እንዲገኙ ተጋብዘዋል።
በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በኢትዮጵያ ሥርዓት ሰኞ ግንቦት 4/2017 ዓ. ም. ከጠዋቱ በሁለት ሰዓት ተኩል ላይ የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ በኅብረት የመሩት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ አብያተ ክርስቲያናት አባቶች ሲሆን፥ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከሮም እና ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ካኅናት፣ ደናግል እና ምዕመናን ተካፋይ ሆነዋል።
እንደዚሁም የአርመኒያ ቤተ ክርስቲያንም ከቀኑ በሰባት ሰዓት ላይ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁ ባዚሊካ ውስጥ የአምልኮ ሥርዓቷን የተከተለ መስዋዕተ ቅዳሴን በማቅረብ በዓሉን ያከበረች ሲሆን፥ በባዚሊካው ውስጥ በዘጥኝ ሰዓት ላይ የግብጽ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በኮፕት ሥርዓት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ተፈጽሟል።
የግንቦት 5/2017 ዓ. ም. መርሃ ግብር
በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ግንቦት 5/2017 ዓ. ም. ከቀኑ በሰባት ሰዓት የአዳይ እና ማሪ የቁርባን ጸሎት ያለበት ጥንታዊ የምሥራቅ ሶርያ የአምልኮ ሥርዓት መስዋዕተ ቅዳሴ የሚቀርብ ሲሆን፥ ሥነ-ሥርዓቱን የከለዳውያን እና የሲሮ-ማላባር አብያተ ክርስቲያናት በኅብረት እንደሚመሩት ታውቋል።
በዕለቱ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁ ባዚሊካ ውስጥ ከምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ ላይ በሶርያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ በማሮናዊት ቤተ ክርስቲያን እና በሲሮ-ማላንካራ ቤተ ክርስቲያን የተዘጋጀ የማታ ጸሎት ከቀረበ በኋላ በመጨረሻም ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ላይ በባይዛንታይን የአምልኮ ሥርዓት ወደ እግዚአብሔር እናት የምስጋና መዝሙር በባዚሊካው ፊት ለፊት እንደሚቀርብ ታውቋል።
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የመገናኘት ዕቅድ
የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የተስፋ ኢዮቤልዩ ነጋዲያ የመጨረሻ ቀናቸው በሆነው ረቡዕ ግንቦት 6/2017 ዓ. ም ከረፋዱ በአራት ሰዓት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛው ጋር በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ እንደሚገናኙ መርሃ ግብሩ ሲያመለክት፥ ቀጥሎም ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በባይዛንታይን ሥርዓት የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴ በግሪክ የመልቃይት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ የዩክሬይን ግሪክ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ የሮማኒያ ግሪክ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና ሌሎች የባይዛንታይን የአምልኮ ሥርዓትን የሚከተሉ አብያተ ክርስቲያናት በኅብረት ሆነው የሚያሳርጉት እንደሚሆን ተገልጿል።
የምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ሙሉ ግንኙነት ኖሯቸው ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ሃያ ሦስት የምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ያሉ ሲሆን፥ እነሱም በምሥራቅ የክርስትና እምነት ላይ የተመሠረቱ ልዩ የአምልኮ ሥርዓቶችን፣ ሥነ-መለኮታዊ አስተምህሮች እና ወጎችን ጠብቀው የቆዩ ናቸው።
ከእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አብዛኛዎቹ ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ ማኅበረሰቦች እና ከሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የመነጩት እና ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው፥ በምሥራቅ አውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በህንድ፣ በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የዳያስፖራ ማኅበረሰቦችን ያካተቱ እንደሆኑ ታውቋል።