MAP

ፓትርያርክ ፒዛባላ በእየሩሳሌም የሆሳዕና በዓል በተከበረበት ወቅት  ደብረ ዘይትን በሚያሳይ መልኩ የተነሱት ምስል ፓትርያርክ ፒዛባላ በእየሩሳሌም የሆሳዕና በዓል በተከበረበት ወቅት ደብረ ዘይትን በሚያሳይ መልኩ የተነሱት ምስል   (AFP or licensors)

ፓትርያርክ ፒዛባላ ተስፋ መቁረጥ እንደማይገባ አሳሰቡ

የኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ያደረጉትን የሰላም ጥሪ በመቀላቀል፥ የክርስቲያኑ ማህበረሰብ በጋዛ ውስጥ ስቃይ እየደረሰባቸው ለሚገኙት ፍልስጤማዊያን እርዳታ ለማድረስ የተቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እሑድ፣ ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም. የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪነት አገልግሎታቸውን በጀመሩበት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የሰላም ጉዳይ በዋናነት በድጋሚ የዕለቱ ዋና ቃል ሆኖ የነበረ ሲሆን፥ የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ሰሞኑን ባደረጉት ቃለ ምልልስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን በዕለቱ ባደረጉት ቃለ ምዕዳን ጦርነት በተከሰተባቸው የዓለም ክፍሎች የሚካሄደው ብጥብጥ እንዲቆም ያደረጉትን የሰላም ጥሪ በማስተጋባት ድምጻቸውን አሰምተዋል።

መልስ፡ ሰላም ከክርስቶስ
ፓትርያርክ ፒዛባላ ኤስ.አይ.አር. (SIR) ከተባለው የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “መልሱ ሰላም ነው” በማለት አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን፥ ነገር ግን ዓለም የሚፈልገው ሰላም፥ “የፖለቲካ ሰላም ወይም የጦርነት አለመኖር ብቻ” እንዳልሆነ በመጠቆም፥ ከዚህ ይልቅ በግጭት፣ በመከፋፈል እና በጥላቻ የተመሰቃቀለችውን ዓለም የሚረዳው ብቸኛው ሰላም “ከክርስቶስ የሚገኘው” ሰላም ነው ብለዋል።

የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ አክለውም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በእሁዱ ሥርዓተ ቅዳሴ ወቅት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሃዋሪያው ጴጥሮስ “ትወደኛለህን?” ሲል የተናገረው ቃል ላይ ተንተርሰው ያደረጉትን አስተንትኖ በመጥቀስ፥ ይህ “የክርስትና ሕይወት ምሳሌ ነው፣ ውጤቱም ሰላም ነው” ብለዋል።

“አንድ ሰው ለእግዚአብሔር እና ለባልንጀራው ፍቅር ካለው፥ ሰላምን በተፈጥሮአዊ መልኩ ያገኛል” ያሉት ብጹእነታቸው፥ ይህ ሰላም በዓለም ላይ በየትኛውም ቦታ፣ በተለይም በቅድስት አገር ሁላችንም የምንፈልገው ዓይነት ሰላም ነው” በማለት ገልጸዋል።

ረቂቅ ሀሳብ?
ፓትርያርክ ፒዛባላ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ “ሰላም” የሚለው ቃል ብዙ ጊዜ እንደተደጋገመ ጠቁመው፥ ለብዙ ሰዎች በተለይም ግጭት በተከሰተባቸው ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች “የወንድማማችነት ፍቅር" የሚለውን ሀሳብ ለመቀበል አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው፥ ብሎም “ከእውነታው የራቀ ረቂቅ ሃሳብ ይመስላቸዋል” በማለት አብራርተዋል።

ፓትርያርኩ በማከልም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልዕክት መላው የክርስትና እምነት ተከታዮች አንድነታቸውን እንዲጠብቁ፥ በተለይ ለእኛ ለራሳችን የተላለፈ ጥሪ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ይህ የአብሮነት ስሜት ከክርስቶስ ፍቅር የሚመነጭ እንጂ ሌላውን ከመፍራት እንዳልሆነ አሳስበው፥ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር በአደባባይ ውስጥ እንኳን ሳይቀር ጥብቅ ትስስርን ይፈጥራል በማለት ገልጸዋል።

ስለ ጋዛ ማሰብ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪነት የአገልግሎት መጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ነጋዲያን እና በዓሉ ላይ ከተገኙት እንግዶች ጋር በመሆን ባቀረቡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ሰብአዊ እርዳታ ተቋርጦባቸው በረሃብ እየተሰቃዩ ስለሚገኙት “ህፃናት፣ ቤተሰቦች እና አረጋውያን” አንስተው የነበረ ሲሆን፥ ፓትርያርክ ፒዛባላ በምላሹ “እኛ ተስፋ መቁረጥ ሳይገባን በጽናት መቆም አለብን” ሲሉ በአፅንዖት ከገለጹ በኋላ፥ ሁላችንም በአካባቢው የሚገኙትን ክርስቲያኖች የመርዳት ግዴታ እንዳለብን በመግለጽ “እርዳታ ለማቅረብ የተቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን” በማለት የማያሻማ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
 

20 May 2025, 14:46