የምስራቃዊ አቢያተ ክርስቲያናት መሪዎች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በምስራቃዊ አቢያተ ክርስቲያናት የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሚያዚያ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. አዲስ የተመረጡት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰበው ሕዝብ ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግራቸው ስለ ሰላም ማንሳታቸውን በመጥቀስ፥ ብጹእነታቸው በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
የቆስጠንጥንያው ክርስቲያናዊ አቢያተ ክርስቲያናት ፓትርያርክ ብጹእ አቡነ በርተሌሜዎስ የምርጫውን ውጤት የሰሙት በግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ ላይ ለክብራቸው በተዘጋጀ ዝግጅት ላይ እንደነበሩ ‘ዘ ኦርቶዶክስ ታይምስ’ ያወጣውን ዘገባ አይተው እንደሆነ አመላክተዋል።
የፓትሪያርኩ ጽህፈት ቤቱ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ባስተላለፈው የቪዲዮ መልእክት ፓትሪያርኩ አዲሱ የሮማ ጳጳስ በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለሰው ልጆች ሁሉ ጥቅም ሲባል መላው አቢያተ ክርስቲያናት አንድነት እንዲፈጥሩ እና ተቀራርበው እንዲሰሩ የተቻላቸውን እንደሚያደርጉ እና ተባባሪ እንደሚሆኑ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር በጋራ ውይይት እና በፍጥረት እንክብካቤ ዙሪያ ስለነበራቸው ትብብር ያስታወሱት ፓትሪያርክ በርተሎሜዎስ፥ “ከብጹእነታቸው ጋር በርካታ ሥራዎችን ሰርተናል” በማለት አስታውሰዋል።
የመጀመሪያው የኒቂያ ጉባኤ 1,700ኛ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ግንቦት ወር ላይ ኢዝኒክ ቱርክን ለመጎብኘት ተስፋ አድርገው የነበሩት የክርስቲያን አቢያተ ክርስቲያናት ፓትሪያርኩ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በኒቂያ ጉብኝት ወቅት እግረመንገዳቸውን ኅዳር 21 ቀን 2018 ዓ.ም. ከሚከበረው የቅዱስ እንድርያስ ክብረ በዓል ላይ ተገኝተው የክርስቲያን አቢያተ ክርስቲያናት ኦፊሴላዊ ጉብኝት ጋር ያገናኙታል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ጭምር ተናግረዋል።
ብጹእነታቸው በአቴንስ በተካሄደው ዝግጅት ላይ ለተሰበሰበው ህዝብ እንደተናገሩት “በአዲሱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ትልቅ ክርስቲያናዊ ተስፋ እናደርጋለን” ያሉ ሲሆን፥ በመጪው ግንቦት 10 ሮም በሚካሄደው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሐዋርያዊ መሪነት የመጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ለመገኘት እንዳሰቡ ተናግረዋል።
“ቤተክርስትያንን እና ዓለምን ከዓለም አቀፋዊ የነጻነት፣ የእኩልነት፣ የፍትህ እና የአብሮነት እሳቤዎች ጋር እንዲያነቃቁ እጸልያለሁ” ያሉት ብጹእነታቸው፥ በዩክሬን እና በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ ጦርነቶችን ለማስቆም የተቻላቸውን እንዲያደርጉ፣ እንዲሁም በህንድ እና በፓኪስታን መካከል ግጭት እንዳይፈጠር ጥረት እንዲያደርጉ በመመኘት፥ “በሁለትዮሽ ግንኙነታችን በምስራቅ እና በምዕራብ መካከል ባለው ግንኙነት ላይ አዲስ ምዕራፍ እንደምንከፍት ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት አክለዋል።
የኪየቭ-ሃሊች ሊቀ ጳጳስ ሲያቶስላቭ ሼቭቹክ በዩክሬን የግሪክ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ድህረ-ገጽ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ማዕከላዊ ሰገነት ላይ ሆነው የተናገሩት ቃል “ሰላም ለእናንተ ይሁን” የሚል እንደነበር አስታውሰው፥ “በመከራ ውስጥ ያለችው ዩክሬን እነዚህን ቃላት እንደ ተስፋ ቃል እና እንደ ልዩ የእግዚአብሔር በረከት ይቆጥራሉ” ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ ሼቭቹክ አክለውም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እነዚህን ቃላት ሲናገሩ ‘ለሁሉም ሃገራት እና ለመላው ዓለም እንደሚደርስ’ በመመኘት ነው ያሉ ሲሆን፥ አዲሱ የሮም ጳጳስ ለረጅም ጊዜያት በመከራ ውስጥ ለቆየው የዩክሬን ሕዝብ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመጣ ሰላም አብሳሪ እንደሚሆኑ ከልብ እናምናለን ብለዋል።
በሃንጋሪ የሃጅ-ዶሮግ ሰበካ የሃንጋራዊያን የግሪክ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ፉሎፕ ኮሲስ በበኩላቸው በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሰላም መልዕክት ላይ በሰጡት አስተያየት፥ “በእርግጥ ብጹእነታቸው ሰላምን መመኘታቸው ብቻ ሳይሆን፥ ሞትን ድል አድርጎ የተነሣውን እና ለሐዋርያቱ በተመሳሳይ መልኩ በዚሁ ቃል ሰላምታ ያቀረበውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማስታወሳቸው እንደሆነም ጭምር ጠቅሰው፥ “በእርግጥ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን የሚሰጠው ዓለም ከሚሰጥበት በተለየ መንገድ ስለሆነ፥ ከትንሣኤ በኋላ ያለው ሰላም ፈጽሞ የተለየ ነው” በማለት አክለዋል።
አዲሱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅርብ ዓመታት ውስጥ ሁለት ጊዜ ሃንጋሪን መጎብኘታቸውን ያስታወሱት ብጹእነታቸው፥ በመጀመሪያ በፔሩ የቺክላዮ ጳጳስ ሆነው መስከረም 2013 ዓ.ም. በቡዳፔስት በተካሄደው 52ኛው ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ኮንግረስ ላይ ለመገኘት ሲሆን፥ በመቀጠልም ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. በቅድስት መንበር የብጹአን ጳጳሳት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሆነው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የግሪክ ካቶሊካዊ ቤተ ክርስቲያንን ጉብኝትን ያካተተውን በሐንጋሪ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት እንደሆነ ገልጸዋል።
የሃንጋሪ ሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ ኮሲስ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን የስም ምርጫ አስመልክተው እንደተናገሩት ብጹእነታቸው ማህበራዊ መስተጋብር ላይ ያላቸውን አቋም እና ፍላጎት ያንፀባርቃል ያሉ ሲሆን፥ ምክንያቱም እንደ ጎረጎሳዊያኑ የዘመን አቆጣጠር ከ 1878 እስከ 1903 ዓ.ም. ድረስ ቤተክርስቲያኒቷን ለ 25 ዓመታት የመሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛ በካቶሊክ ማሕበራዊ አስተምህሮ ላይ በሰሩት ታላቅ ሥራ እና በ 1891 ዓ.ም. ደግሞ የሠራተኞች መብትን አስመልክተው በፃፉት ‘ሬረም ኖቫረም’ ተብሎ በሚጠራው ሃዋሪያዊ መልዕክታቸው ስለሚታወሱ እንደሆነ ገልጸው፥ ከዚህም በተጨማሪ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛ በ 1894 ዓ.ም. ‘ኦሪዬንታይም ድግኒታቲስ’ ተብሎ በሚታወቀው ሃዋሪያዊ መልዕክታቸው በካቶሊካዊ ህብረት ውስጥ ለምስራቃዊ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ክብር እውቅና የሰጡ የመጀመሪያው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እንደነበሩ ገልጸዋል።
ሊቀ ጳጳስ ኮሲስ ምስራቃዊ ካቶሊኮች በስም ምርጫው ላይ ያላቸውን ስሜት ሲገልጹ ‘ሊዮ’ የሚለው ስም ለእኛ በጣም ተወዳጅ ነው ያሉ ሲሆን፥ አዲሱ ተመራጭ ስማቸውን ‘ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ 2ኛ’ የሚለውን ስም ሊመርጡ ይችላሉ ብለው አስበው የነበረ ቢሆንም፥ ሆኖም ግን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የጥንቱን ትውፊት ለማስታወስ ያደረጉትን ጥረት አደንቃለው ብለዋል።
“ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በውይይት እና ድሆችን በማካተት ላይ ባላቸው ጠንካራ አቋም የተነሳ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ አስተሳሰብ ጋር ተመሳሳይ መስመር ላይ እንደሆኑ እርግጠኛ ነኝ” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ኮሲስ፥ “ሁለቱም በጣም ጥሩ ተባባሪዎች ነበሩ፤ ብዙ ነገሮችን በጋራ ተወያይተዋል” በማለት አክለዋል።
በአሜሪካ የኒውዮርክ የግሪክ ኦርቶዶክስ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ኤልፒዶፎሮስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመመረጣቸው የተሰማቸውን ወንድማዊ ክብር በመግለጽ፥ “በትህትና፣ ግልጽነትና በመከባበር መርህ ላይ በመመራት በአብያተ ክርስቲያኖቻችን መካከል የሚደረገውን ውይይት እና ኅብረት ለማጠናከር ቤተክርስቲያኗ ያላትን የማያወላውል ቁርጠኝነት ያድሳሉ” በማለት ገልጸዋል።
“በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ አርአያነት በጥልቅ በመነሳሳት በአገልግሎት ዘመናቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በርተሎሜዎስ ለክርስቲያን አቢያተ ክርስቲያናት ውይይት፣ እርቅ እና በመካከላችን በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ለመንከባከብ የሰጡትን ዘላቂ ቁርጠኝነት በጽኑ ያስተጋባል” ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተወለዱበት በቺካጎ የቅዱስ ቶማስ ሲሮ-ማላባር ካቶሊካዊ ሰበካ አባል የሆኑት ማር ጆይ አላፓት በበኩላቸው “የምስራቅ ካቶሊኮች የአምልኮ ሥርዓቶችን የሚያከብር እና ከጥንታዊ ትሁፊቶቻችን ጋር እውነተኛ ውይይት የሚያደርግ ሲኖዶሳዊነት ላይ አዲስ ትኩረት እንደሚሰጥ ይጠብቃሉ” ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሚያዝያ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ከተመረጡ በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰበው ሕዝብ ባስተላለፉት የመጀመሪያ መልእክት እንደ ሲኖዶሳዊ ቤተ ክርስቲያን የመመላለስን አስፈላጊነት አስምረውበታል።
ማር አላፓት ይሄን አስመልክተው እንደተናገሩት አዲሱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በካርዲናልነት ከ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በቅድስት መንበር የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጽህፈት ቤት አባል ሆነው ሲያገለግሉ እንደነበር በማስታወስ፥ “በነዚህም ጊዜያት በምስራቅ እና በምዕራብ መካከል ያለውን ሁለንተናዊ የካቶሊክ ኅብረት ውብ አንድነትን ተረድተዋል” ብለዋል።
አላፓት በማከልም “ቀደም ሲል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በፔሩ በነበራቸው አገልግሎት በእውነት የሚያዳምጡ፣ ከማኅበረሰቡ ጋር በትሕትና የሚጓዙ፣ እና ድምፃቸው ከድንበር ተሻግሮ የሚሰማ አገልጋይ ነበሩ” ያሉ ሲሆን፥ “ለድሆች ያላቸው ጥልቅ ፍቅር እና በአገሬው ተወላጆች መካከል የነበራቸው መገኘት በዓለም ዙሪያ ባሉ የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት የሚመሩትን ብዙ ተልእኮዎችን በጠንካራ ሁኔታ ያንፀባርቃል” ብለዋል።
በተለይም በማዕከላዊ እና በሰሜን ህንድ ውስጥ በሚገኙት ሚስዮናዊ ግዛቶች ውስጥ በሲሮ-ማላባር ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በርካታ ሃዋሪያዊ እና የበጎ አድራጎት ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቺካጎ እና ፔሩ ያዳበሩት የሃዋሪያዊ ሥራ መንፈስ አሁን በምስራቅ በኩል ላላቸው አገልግሎት ጥሩ መንገድ ይከፍታል ያሉት አላፓት፥ “የእሳቸው መመረጥ የሚስዮናዊ ጥሪያችንን በላቀ ድፍረት እና ርህራሄ እንድንቀበል ያነሳሳናል” ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አባል የሆኑበት የቅዱስ አውገስጢኖስ ማህበር በድህረ ገጹ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በ 2015 ዓ.ም. ካርዲናል ተብለው ሲሾሙ የሰጡትን ቃለ ምልልስ ያወጣ ሲሆን፥ በዚህም ቃለ ምልልስ “ሁሉንም ሰው እንዴት ማዳመጥ እንዳለባት የምታውቅ ሲኖዶሳዊ ቤተክርስቲያን መሆን በግል እምነትን መምራት ብቻ ሳይሆን በእውነተኛ ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ማደግ ነው” ማለታቸው ተጠቅሷል።
በዚህ ቃለ ምልልስ “ቤተክርስትያን ሙሉ በሙሉ ወደዚህ ደረጃ የምታድገው በእውነት እና ከልብ ስታዳምጥ ብቻ ነው” ያሉት ብጹእነታቸው፥ “ቤተክርስቲያን በአስደናቂ ብዝሃነቷ እንደ አዲስ የእግዚአብሔር ሕዝብ በጋራ ስትጓዝ፥ ለወንጌል እና ለእግዚአብሔር መንግስት መስፋፋት የበኩሏን የጥምቀት ጥሪ በቀጣይነት ታረጋግጣለች” ብለዋል።