የሴኡል ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለ2027 የዓለም ወጣቶች ቀን እንደ ቅድመ እይታ የወጣቶች ፌስቲቫልን ማስተናገዷ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በኢዮቤልዩ ዓመት እና በጥሪዎች ሰንበት አውድ ውስጥ ለሦስት ቀናት የተካሄደው ዝግጅት በጎረጎሳዊያኑ 2027 ዓ.ም. ለመካሄድ የታቀደውን ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ወጣቶች ስብሰባ ቅድመ እይታ ለማድረግ ታስቦ እንደተዘጋጀ ተገልጿል።
አዘጋጆቹ እንዳስታወቁት ፌስቲቫሉ የኮሪያ ህዝብ ባህሪያት መገለጫ በሆኑት “ብርሀን” ፣ “ተስፋ” እና “ደስታን” በሚገልጹ መርሃ ግብሮች አማካይነት “ደማቅ፣ በወጣቶች የሚመራ የእምነት፣ የጥሪ እና የማህበረሰብ ክብረ በዓል ለማቅረብ ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይሄንን የሙዚቃ ኮንሰርቶችን፣ የስርዓተ አምልኮ በዓላትን እና አካታች የሆኑ አውደ ትርኢቶችን ያካተተው ፌስቲቫል በማቀድ እና በማስፈጸም ረገድ ወጣቶች ወሳኙን ሚና እንደተጫወቱ የተገለጸ ሲሆን፥ እንደ አዘጋጆቹ ገለጻ፣ ዝግጅቱ “በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ እንዲሁም የተለያየ ዜግነት እና ሃይማኖት ያላቸው ሰዎችን ማሳተፉን እና በደስታ መቀበሉን በመግለጽ፥ ይህም የጋራ ደስታን እና በተለያዩ ባህሎች ዙሪያ የመወያየት ዕድልን ይፈጥራል ብለዋል።
ለዓለም ወጣቶች ቀን ቅድመ እይታ መሆኑ
የዓለም ወጣቶች ቀን ላይ የሚከናወኑ ድርጊቶችን ለማስተዋወቅ ተብሎ የተዋቀረው የሴኡል ዝግጅት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን፣ የምሥክርነት ጊዜያትን፣ የፈጠራ ትርኢቶችን፣ የጸሎት መርሃ ግብሮችን እና ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. በካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የሱንግሲን ካምፓስ “ትሩዝ ዞን” ተብሎ የተሰየመውን የማጠቃለያ መስዋዕተ ቅዳሴን ማካተቱ የተገለጸ ሲሆን፥ ይሄንን የማጠቃለያ መስዋዕተ ቅዳሴ የመሩት የሴኡል ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ፒተር ሶን-ታክ ቹንግ፥ ወጣቶች የእግዚአብሔርን ጥሪ እንዲያዳምጡ ማሳሰባቸው ተመላክቷል።
ሊቀ ጳጳሱ “በዚህ ዓመት ልዩ በሆነ መልኩ ወደ 2027 የዓለም ወጣቶች ቀን በኢዮቤልዩ መንፈስ ስንጓዝ፣ የ ‘ሄ፣ ሄ፣ ሄ” የወጣቶች ፌስቲቫል ብዙ ወጣቶች ልባቸውን ለጌታ ጥሪ እንዲከፍቱ ብሎም በድፍረት እና በእምነት ምላሽ እንዲሰጡ እንደሚያበረታታ ከልቤ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
“ቤተ ክርስቲያኒቷ አዳዲስ ጥሪዎችን ስታበረታታ ታድጋለች፣ ፍሬም ታፈራለች” ያሉት ብጹእነታቸው፥ አክለውም “ዓለማችን በብዙ መንገድ ክርስቶስን መከተል የእውነተኛ ደስታ ምንጭ እንደሆነ በሕይወታቸው የሚመሰክሩትን ‘የተስፋ ምስክሮች’ ለማግኘት ይናፍቃል” ብለዋል።
በመንፈሳዊ ዝማሬዎች እና ምስክርነቶች እንዲሁም ለመንፈሳዊ ጥሪዎች ከፍተኛ ትኩረት በሰጠው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ 3,500 የሚገመቱ ሰዎች እንደተገኙም ጭምር ተገልጿል።
ሶስት ዞኖች፣ አንድ ተልዕኮ
በዓሉ በሦስት ዋና ዋና ጭብጦች የተዋቀሩ ማለትም እውነት፣ ሰላም እና ፍቅር በሚሉ ዞኖች ተከፍሎ የተከበረ ሲሆን፥ እያንዳንዳቸው ወደ ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚያደርሱ ልዩ መግቢያና ምሥክርነት ይሰጣሉ ተብሏል።
- የእውነት ዞን ተብሎ የተሰየመው ዞን የበዓሉ መንፈሳዊ ማዕከል ሆኖ ያገለገለ ሲሆን፥ ግንቦት 2 የተካሄደውን የቅስቀሳ መርሃ ግብር እና ግንቦት 3 የተከናወነውን መስዋእተ ቅዳሴ ማስተናገዱ ተነግሯል።
- ሁለተኛው እና በዶንግ-ሰንግ መለስተኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተዘጋጀው የሰላም ዞን ተብሎ የተሰየመው ዝግጅት፡ በአካባቢ የጥሪ ምስረታ ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ በዚህ ዝግጅት በኮሪያ የሚገኙ የሃይማኖት ጉባኤዎች የአኗኗራቸውን ተመክሮ ለማካፈል የተለያዩ ዳሶችን በማዘጋጀት፥ “ከሀይማኖተኞች ጋር ማውጋት” በሚል ርዕስ የተከናወነው መርሃ ግብር ላይ ወጣቶች ከገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ጋር መደበኛ ያልሆነ ውይይት ያደረጉበት ዝግጅት ትኩረት የሚስብ ነበር ተብሏል።
ሌላኛው በአቅራቢያው የተካሄደው የ “ኦሴዮ ኮንሰርት” በሃይማኖታዊ ማህበረሰቦች አማካይነት ደመቅ ያሉ ትርኢቶች የቀረቡበት ሲሆን፥ በዚህም ዝግጅት ልዩ ልዩ አገልግሎታዊ ተግባሮቻቸውን ያሳዩበት እንደሆነ ተገልጿል።
- የፍቅር ዞን ተብሎ የተሰየመው ሦስተኛው ዝግጅት ላይ፡ ከመኪና እንቅስቃሴ ነፃ በሆነው ዳኢሃክ-ሮ ጎዳና ላይ ወጣት ካቶሊካዊ ቡድኖች እና አጋር ድርጅቶች ያዘጋጁት የመረጃ ልውውጥ አውደ ርዕዮች እና የማዳረስ ጥረቶች አስደሳች ድባብ ፈጥረው የነበረ ሲሆን፥ ግንቦት 3 የተካሄደው የውይይት ኮንሰርት ወጣቶችን፣ ካህናትን እና አርቲስቶችን አንድ ላይ በማሰባሰብ ስለ እምነት፣ ዓላማ እና ተስፋ ግልጽ ውይይቶች መደረጋቸው ተነግሯል።
የበዓሉ መንፈስ
የወጣቶች ፌስቲቫሉ በ180 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እና በ60 ጎልማሶች ድጋፍ የተደረገለት ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር አዘጋጆቹ በዘላቂነት፣ መልሶ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ቁሳቁሶችን በመጠቀም እና ቆሻሻ አልባ አሠራሮችን በመተግበር ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠ በመግለጽ፥ በአስፈላጊ ጊዜ የሚደረግ እገዛ እና በቦታው ላይ የተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች ለአንዳንድ ተሳታፊዎች ተሞክሮ አስተዋፅዖ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ዝግጅቱን “ከአካባቢያዊ ክብረ በዓልም በላይ” እንደሆነ የገለጹት አዘጋጆቹ፥ “ከአንድ ዓመት በኋላ ለሚከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን ጭምር ታማኝ ቅድመ እይታ” ሆኖ አገልግሏል ብለዋል።
ጸሎትን፣ ባህልን እና የማህበረሰብ ተሳትፎን አንድ ላይ በማዋሃድ የቀረበው የ “ሄ ሄ ሄ” የወጣቶች ፌስቲቫል፥ አዘጋጆቹ እንዳሉት “በብርሃን የምትመላለስ፣ በተስፋ የምትኖር እና ደስታን የምታንጸባርቅ እና በወጣቶች የምትመራ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ለምታዘጋጀው ለ 2027 የዓለም ወጣቶች ቀን ጥሩ ራዕይን እንደፈጠረ ገልጸዋል።