ብፁዕ ካርዲናል ግራስያስ በህንድ እና በፓኪስታን መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ አቀረቡ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በካሽሚር ክልል ለተፈጠረው ግጭት በህንድ እና በፓኪስታን መካከል ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥረቱ ቀጥሎ ባለበት በአሁኑ ወቅት የቀድሞው የቦምቤይ ሊቀ ጳጳስ ሁለቱም ወገኖች ሙሉ እና በአስቸኳይ ተፈፃሚ የሚሆን ስምምነት እንዲፈልጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ታጣቂዎች ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም. በካሽሚር የሽብር ጥቃት አድርሰው 26 ንፁሀን ዜጎችን ከገደሉ በኋላ ውጥረቱ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፥ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እስከተደረገበት ቀን ድረስ ሁለቱ ሃገራት እርስ በእርስ ለአራት ተከታታይ ቀናት የአፀፋ ጥቃት ሲፈጽሙ እንደነበር ይታወቃል።
ፓኪስታን የ26 ሂንዱዎችን ሕይወት በቀጠፈው ጥቃት ላይ እጄ የለበትም ብላ ብታስተባብልም ሕንድ ግን በመንግሥት በሚደገፉ አማፂያን የተፈጸመ ነው ስትል ትሞግታለች።
ለአራት ቀን ከቆየው ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት በኋላ ፓኪስታን እና ሕንድ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ሙሉ እና ወድያውኑ ተፈጻሚ የሚሆን የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማምተዋል።
ሁለቱ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት በፈጸሙበት ማግሥት፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሕንድ እና በፓኪስታን መካከል የተደረገውን የተኩስ አቁም ስምምነት በደስታ መቀበላቸውን በመግለጽ፥ “በቅርቡም ዘላቂ የሆነ ስምምነት ላይ ሊደረስ ይችላል” በማለት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
የቀድሞው የቦምቤይ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ኦስዋልድ ግራሲያስ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱን ጥሪ በማስተጋባት “የሰላም ጊዜው አሁን ነው” ሲሉ ድምፃቸውን አሰምተዋል።
ብጹእ ካርዲናሉ ፊደስ ለተባለው የቫቲካን ዜና ወኪል እንደተናገሩት “የጥንት ቂሞችን የምናቆምበት ጊዜው አሁን ነው” ያሉ ሲሆን፥ “እኛ እንደ ቤተክርስቲያን በካሽሚር ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ከልብ የመነጨ ጥሪ እናደርጋለን” ካሉ በኋላ፥ “ሙሉ እና ወድያውኑ ተፈፃሚ የሚሆን ስምምነት እንደሚደረግ ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ፥ “ይህ መሆኑ ለህንድ እና ፓኪስታን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሰላም እጅግ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።
‘ፓኪስታን እና ህንድ የጋራ ቅርስ አላቸው’ ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ግራሲያስ፥ “እኛ አንድ አይነት ባህል፣ ወግ፣ አስተሳሰብ እና ስሜት ያለን ወንድማማቾች ነን፥ ይህም በመሆኑ ፊት ለፊት ተቀምጠን ከነፃነት ጊዜ ጀምሮ ስቃይ የፈጠረብንን የካሽሚር ክልል ቋጠሮ ተነጋግረን ለመፍታት ጊዜው አሁን ነው” በማለት አሳስበዋል።
ሕንዳዊው ካርዲናል አክለውም በካሽሚር እየተስተዋለ ያለው ውዝግብ ጦርነትን፣ ሀዘንን እና መከራን ያስከተለ ጥንታዊ የግዛት ውዝግብ መሆኑን በመጥቀስ፥ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ የታጠቁት ሁለቱ ሀገራት ቀጣይነት ያለው ግጭት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ በማስጠንቀቅ፥ እንዲህ ያለው ጦርነት በዓለማችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ብለዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ግራሲያስ በመጨረሻም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከሁለቱም ወገኖች ገለልተኛ በሆነ ሁኔታ ሃገራቱን እንዲያሸማግል እና አስቸኳይ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲያደርግ በመጋበዝ፥ “ዛሬ ላይ የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ሃይማኖታዊ አመለካከትን ወደጎን በመተው፥ ሰላምን ተጨባጭ በሆነ ሁኔታ የማስፈን ግዴታ አለባቸው፤ ይህ እንደሚሆንም ተስፋ እናደርጋለን” በማለት አጠቃለዋል።