MAP

የመጋቢት 28/2017 ዓ.ም ዘኒቆዲሞስ እለተ ሰንበት ቃለ እግዚአብሔር አስተንትኖ የመጋቢት 28/2017 ዓ.ም ዘኒቆዲሞስ እለተ ሰንበት ቃለ እግዚአብሔር አስተንትኖ 

የመጋቢት 28/2017 ዓ.ም ዘኒቆዲሞስ እለተ ሰንበት ቃለ እግዚአብሔር አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.     ሮሜ 7፡1-18

2.     1 ዮሐ 4፡ 18-21

3.     ሐዋ ሥራ 5፡ 34-42

4.     ዮሐ 3፡1-11

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ ኒቆዲሞስን አስተማረ

ከፈሪሳውያን ወገን፣ ከአይሁድ አለቆች አንዱ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ ሰው ነበረ፤ በሌሊትም ወደ ኢየሱስ መጥቶ፣ “ረቢ፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ ሰው በቀር አንተ የምታደርጋቸውን ታምራዊ ምልክቶች ማንም ሊያደርግ ስለማይችል፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣህ መምህር እንደሆንህ እናውቃለን” አለው።

ኢየሱስም መልሶ፣ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” አለው። ኒቆዲሞስም፣ “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ እንዲወለድ ተመልሶ ወደ እናቱ ማሕፀንስ ሊገባ ይችላልን?” አለው።

ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፤ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደም መንፈስ ነው። ‘ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ’ ስላልሁህ አትገረም፤ ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደ መጣ፣ ወዴት እንደሚሄድም አታውቅም፤ ከመንፈስም የተወለደ ሁሉ እንደዚሁ ነው።” ኒቆዲሞስም፣ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ሲል ጠየቀው።ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ሳለ እነዚህን ነገሮች አታውቅምን? እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ እናንተ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉም።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ዛሬ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘኒቆዲሞስ የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን ። ይህ ሰባተኛ የዐብይ ጽሞ ሳምንት ኒቆዲሞስ የተባለበት ምክንያት በዚሁ ሰንበት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ከዋዜማው ጀምሮ “ወሀሎ አሐዱ ብእሲ እምፈሪሳዊያን ዘስሙ ኒቆዲሞስ መልአኮሙ ለአይሁድ ዞሖረ ኃቤሁ ቀዲሙ ሌሊት ወይቤሎ ለኢየሱስ ዕጓለ አንበሳ ሰከብከ ወኖምክ አንሥአኒ በትንሣኤክ” (ስሙ ኒቆዲሞስ የሚባል የአይሁድ አለቃ የሆነ ከፈሪሳዊያን ወገን አንድ ሰው ነበረ። እርሱ አስቀድሞ ሌሊት ሂዶ ኢየሱስን በመቃብር አንቀላፋህ በትንሣኤህ አንሳኝ) ያለው ነው። ኒቆዲሞስ ሰገደ መንፈቀ ሌሊት ለዘቀደሳ ለሰንበት፣ ሰንበትን ላከበራት ጌታ ኒቆዲሞስ ኢየሱስን ረቢ መምህር ሆነህ ከአብ ዘንድ እንደመጣህ እናምንብሃለን አለው እያለ ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ ኢየሱስ ይሄድ እንደነበረና ምስጢረ ጥምቀትን ከእርሱ እንደተማረ እየጠቃቀሰ እያነሣሣ ስለሚዘመር ይህ ሰንበት ለዚሁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ከጌታ ለመማሩ መታሰቢያ ሆኖ ስለተሰጠ ነው፣ የዚህ ሰንበት ታሪክ ሁኔታ በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ ማለትም በዮሀንስ 3፡1-21 ላይ ተጠቅሶ እናገኘዋለን።

ይህ ኒቆዲሞስ ኒቆዲሞስ በመባል የሚታወቀው ሰው የአይሁድ አለቃ ነበር፣ ባለሥልጣን የነበረ ሰው ጭምር ነው፣ ወደ ኢየሱስ የመሄድ አስፈላጊነት በተሰማው ጊዜ በሌሊት ወደ እርሱ ሄዶ ነበር፣ ምክንያቱም እሱ በተወሰነ ሚዛን እርምጃ መውሰድ ነበረበት፣ ምክንያቱም ኢየሱስን ለማነጋገር የሚሄዱ ሰዎች በደንብ መታየት አይፈልጉም ነበር፣ (ዮሐንስ 3፡2)። እርሱ ጻድቅ የነበረ ፈሪሳዊ ሰው ነበር፣ ምክንያቱም ፈሪሳውያን ሁሉ ክፉዎች አይደሉም። ጻድቃን ፈሪሳውያንም ነበሩ። ይህ ጻድቅ ፈሪሳዊ ነው። ነብያትን ያነበበ እና ኢየሱስ የሚያደርገው ነገር በነቢያት የተነገረ መሆኑን ስለሚያውቅ እረፍት አጥቶ ነበር። ዕረፍት ስለሌለው ኢየሱስን ሊያናግረው ሄደ፡- “ረቢ፣ አንተ መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን” (ዮሐንስ 3፡2) በማለት ስለኢየሱስ ማንነት ተናገረ። "እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ካልሆነ በስተቀር አንተ የምታደርጋቸውን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል ማንም ሰው የለም" በማለት ይናገራል። ኢየሱስም ኒቆዲሞስ ባልተበቀው መልኩ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” በማለት ይመልስለታል።  እናም  ኒቆዲሞስ ግራ የመጋባት መንፈስ ተሰምቶታል፣ አልተረዳውም ሆኖም የኢየሱስን መልስ ተቀበል፣ “ነገር ግን ሰው ትልቅ ከሆነ በኋላ እንዴት በድጋሚ ሊወለድ ይችላል?” በማለት ይጠይቃል፣ ከላይ የተወለደ በመንፈስ የተወለደ ነው። የኒቆዲሞስ እንዴት መልሶ መጠየቅ እንደሚገባ ግራ ተጋባ።  ምክንያቱም መንፈስ የማይታወቅ እና ሊታይ የሚችል ነገር ስላልነበረ ነው። እዚህ ላይ ኢየሱስ የሰጠው የመንፈስ ትርጉም ትኩረት የሚስብ ነው። “ነፋስ ወደ ፈለገበት ይነፍሳል ድምፁንም ትሰማለህ ነገር ግን ከየት እንደ መጣ ወዴትም እንሄደ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው” (ዮሐንስ 3፡8) ብሎ ይናገራል። ራሱን በዚህና በዚያ በመንፈስ ቅዱስ እንዲመራ የፈቀደ ሰው፡ ይህ የመንፈስ ነፃነት ነው። እናም ይህን የሚያደርግ ሁሉ ታዛዥ ሰው ነው እና እዚህ የምንናገረው ስለ መንፈስ ቅዱስ ባህሪይ ነው።

ክርስቲያን መሆን ማለት ትእዛዛቱን መፈጸም ብቻ አይደለም፣ ትእዛዛቱ መፈጸም አለባቸው፣ ይህ እውነት ነው ነገር ግን እዚያ ላይ ካቆምክ ጥሩ ክርስቲያን አይደለህም። ክርስቲያን መሆን ማለት መንፈሱ ወደ ውስጣችሁ እንዲገባ እና ወደ ፈለገበት ቦት እንዲወስዳችሁ መፍቀድ ማለት ነው፣ ወደ ፈለገበት እንዲወስዳችሁ ራሳችሁን ለመንፈስ ቅዱስ አስገዙ። በክርስትና ህይወታችን ብዙ ጊዜ እንደ ኒቆዲሞስ እናቆማለን ከ"ስለዚህ" በፊት የምንወስደውን እርምጃ አናውቅም እንዴት ማድረግ እንዳለብን አናውቅም ወይም ይህን እርምጃ እንዲወስድ በእግዚአብሔር እምነት የለንም መንፈስም በውስጣችን እንዲገባ አንፈቅድም። ዳግመኛ መወለድ መንፈስ ወደ እኛ እንዲገባ መፍቀድ እና መንፈሱ እንዲመራኝ መፍቀድ ማለት ነው፣ ነፃ በሆነው በዚህ የመንፈስ ነጻነት የት እንደምትደርስ አታውቀውም።

ከኢየሱስ ሞት በኋላ በፍርሃት ተውጠው የነበሩት ሐዋርያት ፈርተው በላይኛው ክፍል ውስጥ ተደብቀው በነበሩበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ካይ በወረደበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ በድፍረት ለመስበክ እንዲወጡ እንዳነሳሳቸው እናውቃለን (የሐዋርያት ሥራ 2፣1-13 ተመልከት) ... ይህ እንደሚሆን ግን እነርሱ አላወቁም ነበር፣ መንፈስም ስለመራቸው አደረጉት። ክርስቲያኑ ትእዛዛቱን በመፈጸም ላይ ብቻ ማቆም የለበትም፡ ትእዛዛቱ መፈጸም አለባቸው፣ ነገር ግን ወደዚህ አዲስ ልደት ማለትም በመንፈስ መወለድ የመንፈስን ነፃነት ወደ ሚሰጠን መንፈስ ቅዱስ መሄድ ይኖርብናል።

በዚህ በዛሬው የዮሐንስ ወንጌል 3፡1-11 ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ከሚባል የአይሁድ ሃይማኖታዊ ሸንጎ አባልና የአይሁድ አለቃ ጋር ስላደረገው ውይይት እንመለከታለን። ኒቆዲሞስ የአይሁድን ሥርዓት ጠንቅቆ የሚያውቅና የተማረ ሰው ነበረ። ነገር ግን በአይሁድ ሸንጎ ዘንድ እንደ ነብይ ከማይቆጠረውና  እንደ ነውጠኛ ከሚታየው ከእየሱስ ዘንድ በማታ በመሄድ እየሱስን ያነጋግረው ነበረ። ይህ ኒቆዲሞስ ውስጠ ቀናና በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ነቢይነት ያምን የነበረ በዚህም ምክንያት ማታ ማታ ወደ እርሱ በመሄድ ከእየሱስ ጋር ይወያይ የነበረ መልካም ሰው ነው።

አይሁዳውያኑ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ላይ ሲነሱ ሲቃወሙ ኒቆዲሞስ ግን እየሱስን በተቻለው አቅም ይከላከልለት ነበር ለዚህም ማስረጃ የሚሆነን  “ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስ ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምን እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን አላቸው? እንርሱም መለሱና አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንደማይነሳ መርምረህ እይ አሉት” (ዮሐ. 7፡50-52) ይነበባል።።

ይህ መልካም ሰው ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የነበረው አመለካከት በዚህ አልተቋጨም የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የቅርብ ሰዎች የነበሩት ሐዋርያት ከእርሱ ጋር አብረው የበሉት ከእርሱ ጋር አብረው የጠጡት ከእርሱ ጋር አብረው ከቦታ ቦታ የተዘዋወሩት ብዙ ተዓምር ሲያደርግ በዓይናቸው የተመልከቱት በዛ በጭንቅ ሰዓት ሲሸሹት ይህ ኒቆዲሞስ ግን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከሞተ በኃላ  ከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ በመምጣት እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከገነዙት ከሽቶ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከከፈኑት በቅርቡ በነበረም የአትክልት ሥፍራ  አዲስ መቃብር ውስጥ ካኖሩት መልካም ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው (ዮሐንስ  19፡39)።

ይህ ሰው በዚህ ድርጊቱ ከሐዋርያቱ የበለጠ ለጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ያለውን ታማኝነት አስመስክሯል። ይህ እንግዲህ ለእያንዳዳችን የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንም እንኳን ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር ሕብረት ቢኖረንም ለእርሱ ያለንን ታማኝነት በይፋና ጉልህ በሆነ መልኩ ማንንም ሳንፈራ ማስቀመጥ ይገባናል።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከኒቆዲሞስ ጋር በነበረው ውይይት ያስተማረው አንድ ጠልቅና መሠረታዊ  ነገር አለ ይኸውም “እውነት እውነት እልሃለው ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ሊገባ አይችልም ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው” (ዮሐ 7፡5-6)።

እውነት ነው ሰው ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ሊገባ የሚችለው ሕግን በመጠበቅ ብቻ ሳይሆን በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሲታደስ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አምኖ በዕምነቱም አዲስ ሕይወት መላበስ ሲችል ብቻ ነው። “ነገር ግን ሰው በእየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አወቅን ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ እየሱስ አምነናል” (ገላ. 2፡16) ይላል። እንግዲህ ዛሬም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እያንዳዳችን በአዲስ መልክ ከውኃና ከመንፈስ እንድንወለድ ይፈልጋል ይኸውም ኃጢአታችንን በምስጢረ ንስሃ አማካኝነት አንድናጥብና ለኃጢአት እንድንሞት ብሎም በእግዚአብሄር መንፈስ እንድንሞላ ይህንንም አድርገን የዘለዓለማዊ  ሕይወት ተቋዳሾች አንድንሆን ይፈልጋል።

ሰው በጥምቀትና በምስጢረ ንስሃ አማካኝነት ኃጢአቱን ካጠበ መላ እሱነቱ በመንፈስ እንደሚሞላ ግልጽ ነው ይህ መንፈስ ነው ታዲያ እንደ እግዚአብሄር ቃል እንዲመላለስ የሚያደርገን የስይጣንን ዕቅድ በሙላት እንድንዋጋ ብርታት የሚሆነን ዘወትር ከሚስጢራት ጋር የሚያቆራኘን። ስለዚህ ሰው ሁል ጊዜ በመንፈስና በሥጋ መታደስ ይገባዋል ይህንን ካደረገ ብቻ ምድራዊ ሕይወቱ የተስተካከለና የታረመ እንዲሁም የተቀደሰ ይሆናል የመንግሥተ ሰማይም እጩ ይሆናል።

እንግዲህ እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋ ውስጥ እየተመላለስን መኖር እንድንችልና የእርሱ እውነተኛ ደቀማዛሙርት ለመሆን እንድንችል የዘውትር ጠባቂያችንና አማላጃችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሄር ፊት ትቁምልን በሥጋና በመንፈስ ለመታደስ እንድንችል በረከቱን ከልጇ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ታሰጠን።

 

05 Apr 2025, 10:23