የመጋቢት 28/2017 ዓ.ም የ5ኛው ዐብይ ጾም ሣምንት ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የእለቱ ንባባት
1. ኢዝቄል 37፡12-14
2. መዝሙር 129
3. ሮም 8፡8-11
4. ዩሐንስ 11፡1-45
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
የአልዓዛር መሞት
አንድ ሰው ታሞ ነበር፤ እርሱም እንደ ማርያምና እንደ እኅትዋ ማርታ ከቢታንያ የነበረው አልዓዛር ነው። ማርያም ጌታን ሽቱ የቀባችው፥ እግሩንም በጠጉርዋ ያበሰችው ስትሆን፤ የታመመውም አልዓዛር ወንድምዋ ነበር። ስለዚህም እኅቶቹ “ጌታ ሆይ! እነሆ የምትወደው ታሞአል፤” ብለው ወደ እርሱ ላኩበት። ኢየሱስም ሰምቶ “ይህ ሕመም ለሞት አይሰጥም፤ ይልቁንም ለእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ነው፤ የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ነው” አለ።
ኢየሱስም ማርታንና እኅትዋን እንዲሁም አልዓዛርን ይወድ ነበር። እንደ ታመመም በሰማ ጊዜ ያንጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ዋለ፤ ከዚህም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ “ወደ ይሁዳ እንደገና እንሂድ፤” አላቸው። ደቀመዛሙርቱ “መምህር ሆይ! አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፤ በድጋሚ ወደዚያ ትሄዳለህን?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ “በቀን ውስጥ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ይገኙ የለምን? በቀን የሚመላለስ የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤ በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለ ሌለ ይሰናከላል፤” አላቸው። ይህንንም ከተናገረ በኋላ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ፤” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “ጌታ ሆይ! ተኝቶ እንደ ሆነስ ይድናል፤” አሉት። ኢየሱስ ግን ስለ ሞቱ ነበር የተናገረው፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ የተናገረ መሰላቸው። እንግዲህ ያንጊዜ ኢየሱስ በግልጥ “አልዓዛር ሞተ፤ እናንተ እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ፤” አላቸው። ዲዲሞስ የሚሉትም ቶማስ ለሌሎቹ ደቀ መዛሙርት “ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛም እንሂድ፤” አለ።
ኢየሱስ ትንሣኤና ሕይወት እንደሆነ
ኢየሱስም በመጣ ጊዜ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት ነበር። ቢታንያም ዐሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች። ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር። ማርታም ኢየሱስ እንደመጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ አውቃለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ወንድምሽ ይነሣል፤” አላት። ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሣ አውቃለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ 26ሕያው የሆነና በእኔ የሚያምን ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽኝ?” አላት። እርሷም “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው።
ይህንም ብላ ሄደች፤ እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ “መምህር መጥቷል፤ እየጠራሽም ነው፤” አለቻት። እርሷም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች፥ ወደ እርሱም መጣች፤ 30ኢየሱስም ማርታ እርሱን በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። ከእርሷ ጋር በቤት ሲያጽናኑአት የነበሩ አይሁድም፥ ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር፤” አለችው። ኢየሱስም እርሷ ስታለቅስ ከእርሷም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ “ወዴት አኖራችሁት?” ዓለም። እነርሱም “ጌታ ሆይ! መጥተህ እይ፤” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህም አይሁድ “እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ፤” አሉ። ከእነርሱ ግን አንዳንዶቹ “የዐይነ ሥውሩን ዐይኖች እንደ ከፈተ ይህም ሰው እንዳይሞት ማድረግ አይችልም ነበርን?” አሉ።
ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት እንዳስነሣው
ኢየሱስም በድጋሚ በጥልቅ ኀዘን ተውጦ ወደ መቃብሩ መጣ፤ መቃብሩም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር። ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሡ፤” አለ። የሞተውም ሰው እኅት ማርታ “ጌታ ሆይ! ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል፤” አለችው። ኢየሱስ “ካመንሽ የእግዚአብሔርን ክብር እንደምታዪ አልነገርሁሽምን?” አላት። ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዐይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ እንዲህ አለ፥ “አባት ሆይ! ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ፤” ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ “አልዓዛር ሆይ! ና፥ ወደ ውጭ ውጣ፤” ብሎ ጮኸ። ሞቶ የነበረውም ሰው እጆቹና እግሮቹ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበረ። ኢየሱስም “ፍቱትና ይሂድ፤ ተዉት፤” አላቸው። ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፥ ኢየሱስም ያደረገውን ካዩት ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!
በዛሬው በአምስተኛው የዐብይ ጾም ሳምንት ሰንበት እለተ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል (ዮሐንስ 11፡1-45) የአልዓዛር ከሞት መነሳት ይገልጻል። አልዓዛር የኢየሱስ ወዳጆች የነበሩት የማርታ እና የማሪያ ወንድም ነው። ኢየሱስ ወደ ቢታንያ ሲደርስ አልዓዛር ከሞተ አራት ቀናት ያህል ሞልቶት ነበር፣ ማርታ ጌታን ለመገናኘት ሮጣ በመሄድ “እዚህ ብትኖር ኖሮ ወንድሜ አይሞትም ነበር” (ዮሐንስ 11፡ 21) አለችው። ኢየሱስም “ወንድምሽ ይነሳል” (ዩሐንስ 11፡23) በማለት መለሰላት። “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል” (ዩሐንስ 11፡25) በማለት አክሎ ይናገራል። ለሙታን እንኳን ሕይወት የመስጠት ችሎታ ያለው መሆኑን እና ኢየሱስ ራሱን የሕይወት ጌታ መሆኑ ይገልጻል። ከዚያም በኋላ ማርያም እና እርሷን ተከትለዋት የመጡት አይሁድም ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ ቅዱስ ወንጌል እንደ ሚነግረን “ኢየሱስ መንፈሱ በኀዘን ታወከ፣ ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ” (ዮሐንስ 11፡ 33. 35)። ይህንን የሁከት ስሜት በልቡ ውስጥ ይዞ ወደ መቃብሩ ስፍራ ይሄዳል፣ ሁል ጊዜም ቢሆን ጸሎቱን የሚሰማውን አባቱን እያመሰገነ መቃብሩን አስከፍቶ “አልዓዛር ፣ ና ውጣ!” ብሎ በታላቅ ድምጽ ተጣራ (ዮሐንስ 11፡43)። አልዓዛርም “እጅና እግሩ በቀጭን ስስ ጨርቅ እንደ ተጠቀለለ፣ ፊቱም በሻሽ እንደ ተጠመጠመ ወጣ” (ዮሐንስ 11፡44)።
እዚህ ላይ እግዚአብሄር ሕይወት መሆኑን እና ሕይወት ሰጪ መሆኑን ተጨባጭ በሆነ መልኩ እንመለከታለን። ኢየሱስ ወዳጁ የነበረውን የአልዓዛር ሞት አስቀድሞ ማስቅረት ይችል የነበረ ሲሆን ነገር ግን የምንወዳቸው ሰዎች ከእኛ በሞት በሚለዩበት ወቅት የሚሰማንን ከፍተኛ ሐዘን ኢየሱስ የራሱ ሐዘን አድርጎ በመቁጠር እና ከሁሉም በላይ ደግሞ እግዚአብሔር በሞት ላይ ያለውን ስልጣን ለማሳየት ይፈልጋል። በዚህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ውስጥ የሰዎች እምነት እና የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር የሚፈልጉ ሁሉ በመጨረሻም እንደሚያገኙት እናያለን። ማርታ እና ማርያም እንዲሁም ሁላችንም “አንተ አዚህ ብትኖር ኖሮ . . . ” ብለን የምናሰማውን ጩኸት እናያለን። የእግዚአብሔር መልስ ግን ወሬ አልነበረም፣በፍጹ እንዲህ አልነበረም! ሞት ላስከተለው ችግር የእግዚአብሔር መልስ ኢየሱስ ነው-“ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ… በእኔ እምነት ይኑራችሁ! ለቅሶ ሲያጋጥማችሁ በእኔ ማመናችሁን ቀጥሉ፣ ሞት አሸናፊ ሆኖ የሚወጣ ቢምስላችሁ እንኳን በእኔ ማመናችሁን ቀጥሉ። ድንጋዩን ከልባችሁ ላይ አስወግዱት! ሞት ወዳለበት ስፍራ እግዚአብሔር ቃል ገብቶ መልስ ይሰጥ ዘንድ ፍቀዱለት”።
ዛሬም ቢሆን ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሱ” በማለት ይናገራል። እግዚአብሔር ለመቃብር አልፈጠረንም፣ እርሱ የፈጠረን ለሕይወ፣ ለውብት እና ለደስታ ነው የፈጠረን። ነገር ግን መጽሐፈ ጥበብ እንደ ሚናገረው “ሞት ወደ ዓለም የገባው በዲያብሎስ ቅናት ነው” (መ. ጥበብ 2፡24) ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከእዚህ ስይፍ ሊያድነን መጣ።
ስለሆነም የሞት ጣዕም ያላቸውን ድንጋዮች ሁሉ እንድናስወገድ ተጠርተናል፣ ለምሳሌ በእምነታችን ውስጥ ያለው ግብዝነት በራሱ ሞት ነው፣ ሌሎችን የሚጎዳ ትችት በራሱ ሞት ነው፣ በደል መፈጸም፣ ስም ማጥፋት ሞት ነው፣ ድሆችን ማግለል ሞት ነው። ጌታ እነዚህን ድንጋዮች ከልባችን እንድናስወግድ ይጠይቀናል፣ ይህንን በምናደርግበት ወቅት ሁሉ ሕይወት አሁንም በዙሪያችን ያብባል። ክርስቶስ ህያው ነው ፣ እሱን የተቀበለ እና እሱን የሚከተል ሁሉ ከሕይወት ጋር ይገናኛል። ያለ ክርስቶስ ወይም ከክርስቶስ ውጭ በሕይወት የመኖር ያለመኖር ጉዳይ ብቻ አይደለም፣ አንድ ሰው ወደ ሞት የሚወስደውን መንገድ ይከተላል ማለት ነው።
የአልዓዛር ከሞት መነሳት ደግሞ አማኙ በምስጢረ ጥምቀት አማካይነት በክርስቶስ የፋሲካ ምስጢር ውስጥ መግባቱን የሚያመለክት የእድሳት ምልክት ነው። በመንፈስ ቅዱስ ተግባር እና ኃይል ክርስቲያን እንደ አዲስ ፍጥረት በመሆን በሕይወቱ የሚራመድ ሰው ነው - ለሕይወት የተፈጠረ እና ወደ ሕይወት የሚሄድ ሰው ነው።
ሐዘናችንን ሐዘኑ በማድረግ ርህራሄውን የሰጠንን ልጇን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየንን ተምሳሌት በመከተል ርህሩህ እንድንሆን ድንግል ማርያም እንድትረዳን ልንማጸናት ይገባል። በፈተና እና በመከራ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች እያንዳንዳችን ቅርብ እንድሆን ዘንድ፣ ለእነሱ ሞትን የሚያሸንፍ እና ሕይወትን የሚሰጥ የእግዚአብሔር ፍቅር እና ርህራሄ ነፀብራቅ መሆን እንችል ዘንድ እርሷ እንድትረዳን አማላጅነቷን መማጸን ይኖርብናል።
አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን