ለታሊታ ኩም አመራሮች በፔሩ ዋና ከተማ ሊማ 5ኛ ዙር የአመራር ስልጠና ተሰጠ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከዚህን በፊት በታሊታ ኩም የተሰጡ አራት ዙር ሥልጠናዎች ላይ የተሳተፉትን ሰዎች ፈለግ በመከተል በ5ኛው የአመራር ስልጠና ላይ ከ27 ሀገራት የተውጣጡ 30 አባላት የተካፈሉ ሲሆን፥ ሥልጠናው የተካሄደው በፔሩ ዋና ከተማ ሊማ ከመጋቢት 14 እስከ 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ እንደሆነ ተነግሯል።
ሥልጠናው የተዘጋጀው የዓለም አቀፉ ታሊታ ኩም ናይሮቢ ከሚገኘው ታንጋዛ ዩኒቨርሲቲ እና ከትስስሩ ወቅታዊ ፍላጎት ጋር በማጣጣም ሥልጠናውን ከነደፈው ሮም ከሚገኘው የቅዱስ መስቀል ጳጳሳዊ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ጋር በመተባበር ሲሆን፥ የአካባቢው የታሊታ ኩም ትስስር የሆነው ‘ሬድ ካውሳይ ፔሩ’ ሥልጠናውን ማስተባበሩ ተገልጿል።
ታሊታ ኩም ለከፍተኛ አመራሮች በቂ የአመራር ስልጠና መስጠት በሚል ዓላማ በ 2010 ዓ.ም. ሰኔ ወር ላይ የመጀመሪያ ዙር ሥልጠናውን በሲስተር ገብርኤላ መሪነት በሮም የጀመረ ሲሆን፥ በወቅቱ የተደረገውን ስልጠና አስመልክተው ሲስተር ገብርኤላ እንደተናገሩት “የተገለሉ መሪዎችን ሳይሆን ትስስሩን ለመዘርጋት እና ለመምራት የሚችሉ መሪዎችን ማቋቋም እና መመስረት ያስፈልገን ነበር” ብለዋል።
በህይወት ዘመን አንዴ የሚገኝ
እህት አቢ አቬሊኖ በአሁኑ ወቅት ተነሳሽነቱን በሃላፊነት እየመሩ የሚገኙ ሲሆን፥ መጋቢት 14 እሑድ ምሽት ላይ በተከናወነው የመክፈቻ ሥነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር “ዛሬ አንድ ላይ ስንሰበሰብ ‘በህይወት ዘመን አንዴ ብቻ የሚገኝ ገጠመኝ’ የሚል አቻ ትርጉም ያለው ‘ኢቺ-ጎ ኢቺ-ኤ’ (ichi-go ichi-e’) የሚለውን ጥልቅ የጃፓናዊያን አባባል መጥቀስ እፈልጋለሁ” ካሉ በኋላ፥ በመቀጠልም ይህ ጥልቅ ትርጉም ያለው ሀረግ የእያንዳንዱ የምናሳልፈው ሰዓት ወይም ቅጽበት ልዩ መሆኑን እንደሚገልጽ እና ያጋጠመን እያንዳንዱ ገጠመኝ የማይተካ፣ በትክክል በተመሳሳይ መንገድ የማይደገም መሆኑን እንደሚገልጽ ያብራሩ ሲሆን፥ ተሳታፊዎቹ በሳምንቱ ውስጥ ለሚሰጣቸው የማይደገም ልምድ ክፍት እንዲሆኑ አበረታተዋል።
“በዚህ ቦታ እና ጊዜ ውስጥ የምናካፍለው ልምድ ልዩ ነገር ነው” ያሉት እህት አቢ፥ በስልጠናው ወቅት የሚለዋወጡት ጥበብ፣ ልምዶች እና ግንዛቤዎች በግለሰብ እና በቡድን አመለካከቶች የተቀረጹ እንደሆኑ እና ይህ ጊዜ ካለፈ በኋላ እንደገና በተመሳሳይ መልኩ እንደማይመጣ አስረድተዋል።
ለአመራር የሚያስፈልጉ ነገሮች
ሳምንት በሚቆየው ሥልጠና ውስጥ የአመራር ስልቶች፣ ሲኖዶሳዊነት፣ እራስን እና ሌሎችን ለመምራት አስፈላጊ የሆኑ ባህሪያት፣ የመግባቢያ ክህሎት፣ የተዋሃደ አመራር እና በፔሩ ለተጎጂዎች እንዴት ድምጽ መሆን እንደሚቻል እና ለፖሊሲ አወጣጥ ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም የራስን ሚና መጫወት፣ የቡድን ስራ፣ ችግር አፈታት እና በመንፈሳዊ ውይይቶች ላይ መሳተፍ፣ ለተሳታፊዎች በባህል እና ቋንቋዎች ላይ የሚደርሱ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚችሉበትን ዕድል መዘርጋት እና እንደ አንድ የትስስር መረብ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ዕድሎች ይፈጠራሉ ተብሏል።
ቡድኑ በሊማ ከተማ እምብርት የሚገኘውን በቅዱስ ቪንሴንት ዲ ፖል የበጎ አድራጎት ሴት ልጆች የሚተዳደረውን የ ‘ሶር ሮዛሊያ ሬንዱ’ የስደተኞች መጠለያ ማዕከልን የጎበኘ ሲሆን፥ በማዕከሉ ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ሰለባዎች የሚያቀርቧቸውን አገልግሎቶች ዝርዝር ማብራሪያ የሚሰጡት ገዳማዊያቱ ብቻ ሳይሆኑ የፔሩ የህዝብ ሚኒስቴር ተወካዮች እና ‘አዎር ሬስኪዩ’ የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ተወካይም በቦታው ተገኝተው በመጠለያው ውስጥ የሚሰጠውን አገልግሎት እንዴት እንደሚደግፉ እና እንደሚረዱ ብሎም ከገዳማዊያቱ እህቶች ጋር እንዴት እንደሚተባበሩ አብራርተዋል።
አንድ የፔሩ የህዝብ ሚኒስቴር ተወካይ ከቪንሴንሺያን እህቶች ጋር እንዴት በቅርበት እንደሚሰሩ ሲገልጹ ከገዳማዊያቱ ጋር የምንተባበረው የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች እና የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባዎችን በተመለከተ ምን ዓይነት ጣልቃ-ገብነት እንደሚያስፈልግ ስለምንረዳ ነው ብለዋል።
ከ ‘ሬድ ካውሳይ ፔሩ’ አባላት በተጨማሪ የፔሩ የከፍተኛ የበላይ ተቆጣጣሪዎች ጉባኤ ተወካዮች፣ ከሌሎች ማህበራዊ ድርጅቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የመንግስት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ ተወካዮች ቅዳሜ ምሽት ከተካሄደው የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ በአመራር ሥልጠናው ከተሳተፉት ጋር ተገኝተዋል። ይህም ተሳታፊዎች በሳምንቱ ውስጥ በግል የተማሩትን እና የመሪነት ሚናቸውን በተሻለ ሁኔታ ለመወጣት የሚረዱ ክህሎቶችን በይፋ እንዲገልጹ እድል ፈጥሮላቸዋል።
ከኮሎምቢያ የመጡት እህት ሉዝ ኤሌና ስልጠናውን አስመልክተው እንደተናገሩት፥ “መሪ መሆን በጥልቅ ለመረዳት እና በትህትና አብሮ ለመሆን ከልብ እንዴት ማዳመጥ እንደሚቻል ማወቅ እንደሆነ ተምሬያለው” ብለዋል።
ከኢትዮጵያ የተወከሉት ሲስተር ፅጌ ጴጥሮስ በበኩላቸው “ስልጠናው በሃሳቤ፣ በድርጊቴ እና በስሜቴ ራሴን በመቆጣጠር፣ ራሴን የመምራት ችሎታን እንድጠቀም አስችሎኛል” በማለት ተናግረዋል።
በሳምንቱ ውስጥ ታቅደው የሚከናወኑት በተለያዩ ባህሎች የበለጸጉት የመዝናኛ ምሽቶችን ጨምሮ የተደረጉት የባህር ዳርቻ እና የሊማ ከተማ ጉብኝቶች እያንዳንዱ ተሳታፊ ለታሊታ ኩም ትስስር እና ለሚያገለግላቸው ሰዎች የሚያቀርበውን ልዩ የአመራር ክህሎት ለማሳደግ ያለመ ነበር ተብሏል።
ወደ ፊት ምን ሊደረግ ይችላል
ምንም እንኳን የስልጠናው ቀን ቅዳሜ ያበቃ ቢሆንም፥ ነገር ግን ኮርሶቹ ቅዳሜ ምሽት ያላለቁ እንደሆነ፣ ተሳታፊዎች በሳምንቱ ውስጥ በተፈጠሩ የፕሮጀክት ቡድኖች ውስጥ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ እና በነዚህ ቡድኖች በኩል በሊማ ያገኙትን የተጠናከረ ስልጠና በጋራ መተግበሩን እንደሚቀጥሉ ተብራርቷል። ይህ ብቻም ሳይሆን አንድ ላይ ሆነው በራሳቸው ክልል ውስጥ ሊተገበር የሚችል የፀረ-ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ፕሮጀክት ያዘጋጃሉ ተብሏል።
ከቡድን ፕሮጀክት በተጨማሪ፣ እያንዳንዱ ተሳታፊ በሚቀጥለው ዓመት መስከረም ወር ላይ ባለ 15 ገጽ የጥናት ወይም የመመረቂያ ጽሁፍ የሚያቀርብ ሲሆን፥ ይህ ልምምድ በስልጠናው ሳምንት ውስጥ ያገኙትን የአመራር ልምድ እንዲያንፀባርቁ እና እንዲገልጹ እንዲሁም ይህንን ልምድ በንድፈ-ሀሳባዊ/ተግባራዊ አውድ ውስጥ እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል ተብሏል።
ታሊታ ኩም የመሪዎችን ምስረታ ለማስፋፋት በፅናት ለሚተጋው የዓለም አቀፍ የበላይ አለቆች ህብረት ድጋፍ ለማድረግ ያለመ ሲሆን፥ የሂልተን ፋውንዴሽን በበኩሉ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ተሳታፊዎችን በማሰባሰብ ከዚህ ስልጠና ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ግብአት በማዘጋጀት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል።