MAP

'አድሪያኖ' ተብሎ የሚታወቀው ሮቦት በሃድሪያን ቤተመቅደስ ጎብኝዎችን ሲቀበል 'አድሪያኖ' ተብሎ የሚታወቀው ሮቦት በሃድሪያን ቤተመቅደስ ጎብኝዎችን ሲቀበል  

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የወደፊት ሕይወታችንን ብሩህ ሊያደርጉልን ይገባል ተባለ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለሚያዚያ ወር የሚሆን የጸሎት ሃሳብ ባቀረቡበት ወቅት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ስንጠቀም የሰዎችን የእርስ በርስ ግንኙነት መተካት እንደሌለበት፣ የሰው ልጅን ክብር እንዲጠብቅ እና የዘመናችንን ቀውሶች መከላከል የሚያስችለን መሳሪያ እንዲሆን አበክረን መጸለይ ይገባል ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተጽዕኖ አስመልክተው በዩናይትድ ስቴትስ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የጸሎት ትስስር አባል የሆኑት የኢየሱሳዊያን ማህበር ካህን አባ ጆይ ላርሜ ባቀረቡት አጭር ጽሁፍ በልጅነታቸው መጪውን ጊዜ በመተንበይ የሚታወቀው ‘ጄትሰንስ’ የተሰኘውን ካርቱን ፊልም ማየት እንደሚወዱ እና በፊልሙ ውስጥ የነበሩት በቀለማት ያሸበረቁ ገጸ-ባህሪያት ሰማይ ላይ በሚበሩ መኪኖች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲፈተለኩ እገረም ነበር ብለዋል።

“እንዲሁም ታዋቂው አርኖልድ ሽዋርዜኔገር የተወነባቸው የ 'ተርሚኔተር' ፊልሞችን አስታውሳለሁ፥ በዚህም ፊልም ውስጥ ያኔ ያልነበሩ፣ በአሁኑ ወቅት ግን ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙ ጅምላ ገዳይ የሆኑ መሳሪያዎችን ተዋናዩ ሲጠቀም አስተውያለሁ” በማለት በወቅቱ በምናብ ደረጃ ብቻ የነበሩ ቴክኖሎጂዎች አሁን እውን እንደሆኑ ገልጸዋል።

ቅዱስ አባታችን ለሚያዝያ ወር የሚሆን የጸሎት ሃሳብ ባቀረቡበት ወቅት “ስለ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም” እንድንጸልይ ጠይቀውናል ያሉት ካህኑ፥ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች የሰው ልጅን የእርስ በርስ ግንኙነት መስተጋብር እንዳይተኩ፣ ይልቁንም የሰው ልጅን ክብር እንዲጠብቁ እና የዘመናችንን ቀውሶች መጋፈጥ የምንችልበት መሳሪያ ሆነው እንዲያገለግሉን ጸሎት ማድረግ እንደሚገባን ጥሪ አቅርበውልናል ብለዋል።

“አሁን ቴክኖሎጂን እየተጠቀምኩ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን የሚያዚያ ወር የጸሎት መነሻ ሃሳብ በአውታረ መረብ አየሁ” ያሉት ካህኑ፥ አክለውም “በኮምፒውተሬ ላይ ጥቂት ቃላትን ጻፍኩ፥ ይህንን የፃፍኩትን በ ‘አይ ፎን’ (iPhone) ስልኬ እየቀዳሁ ነው” በማለት ቴክኖሎጂ ከቀን ተቀን ህይወታችን ጋር ያለውን ትስስር አብራርተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በሌላ ከተማ ውስጥ ካሉ የእህቶቻቸው እና የወንድሞቻቸው ልጆች ጋር ለመነጋገር ‘ፌስ ታይም’ (FaceTime) የሚባለውን ዘመን አመጣሽ መተግበሪያን እንደሚጠቀሙ የጠቆሙት ካህኑ፥ እሁድ በመስዋእተ ቅዳሴ ወቅት በሚነበቡ ምንባቦች ላይ ለመጸለይ እና ከብጹአን ጳጳሳት እና ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪዎች የሚሰጡ አስተንትኖዎችን ለመከታተል ጭምር የካቶሊክ መተግበሪያዎችን እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።

እንደ ቀላል ነገር እንኳን የሚታየው እና በዘመኑ ቴክኖሎጂ የሚሰራው ዊልቼር አካል ጉዳተኞች ከተፈጥሮ ጋር በቀላሉ እንዲቀራረቡ እንደሚያስችላቸው ብሎም ከሰው ጋር ያላቸውን ወዳጅነት እንደሚያጠናክርላቸው ገልጸዋል።

“ቴክኖሎጂ ጉልበት ያለው እና ለበርካታ መልካም ነገሮች ልንገለገልበት የሚያስችለን መሳሪያ ሊሆን ይችላል” ያሉት ካህኑ፥ በዚሁም ልክ አደገኛ እና አደንዛዥ ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ፥ ለበርካታ ሰዓታት ጥቅም የሌላቸው ቪዲዮዎችን ስንመለከት፣ ከዚህም ባለፈ ግጭት ቀስቃሽ ወይም ጎጂ የሆኑ ይዘቶችን ስንከታተል ጊዜያችንን ሊበላው ይችላል በማለት አሳስበዋል።

“የወደፊቱ ጊዜ ምን ይመስላል? 'ጄትሰንስ' የሚባለው የካርቱን ፊልም ወይም የ 'ተርሚኔተር' ፊልም ካሳዩን ምስል የበለጠ ይችል ይሆን?” ብለው የጠየቁት ካህኑ፥ ፊልሞቹ ያኔ ያሳዩን ጎጂም ሆኑ ጠቃሚ ቴክኖሎጂዎች በአሁኑ ወቅት በሰዎች ዘንድ ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ ብለዋል።

አባ ጆይ ላርሜ በመጨረሻም “አእምሮአችንን፣ እንዲሁም የሳይንስ ሊቃውንት እና የባህል መሪዎችን አእምሮ በልቦናችን ሃሳብ እንዲመራ እግዚአብሔርን ልንጠይቀው እንችላለን” ካሉ በኋላ፥ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች የወደፊት ሕይወታችንን ብሩህ እንዲያደርጉ ሁላችንም ተግተን እንጸልይ በማለት አጠቃለዋል።
 

03 Apr 2025, 14:07