MAP

በታህሳስ 2014 ዓ.ም. በተመረቀው ባህሬን የሚገኘው የአረቢያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ካቴድራል ምዕመናን ለቅዳሴ ሲመጡ በታህሳስ 2014 ዓ.ም. በተመረቀው ባህሬን የሚገኘው የአረቢያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ካቴድራል ምዕመናን ለቅዳሴ ሲመጡ 

በባህሬን የህጻናትን ስቃይ ለመቅረፍ ያለመ ጳጳሳዊ ማህበር ማዕከል መከፈቱ ተነገረ

በሰሜን አረቢያ ሐዋርያዊ ሃገረ ስብከት ሥር ጳጳሳዊ የልጅነት ማኅበር ማዕከል ሥራ የጀመረበትን ቀን በማስመልከት በባህሬን በሚገኘው የአረቢያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ካቴድራል ውስጥ ሥርዓተ ቅዳሴ ተካሂዷል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ጳጳሳዊ የቅዱስ ልጅነት ማኅበር መጋቢት 19 ቀን 2017 ዓ.ም. በባህሬን በሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል አዲስ ማዕከል አስመርቆ የከፈተ ሲሆን፥ ይህም በአካባቢው ለሚገኘው የካቶሊክ ማኅበረሰብ ጠቃሚ እንደሆነ ተነግሯል።

በዓለም ዙሪያ ከ130 በላይ አገሮች ውስጥ የሚገኘው ማኅበሩ፥ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሕፃናትን ስቃይ ለማቃለል እና ለመቅረፍ ቤተክርስቲያን ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል።

የቅድስት ልጅነት ማኅበር በድህነት፣ በግጭት እና በችግር ላይ ባሉ ክልሎች ውስጥ ለሚኖሩ ሕጻናት እርዳታ የሚሰጥ ዓለም አቀፋዊ ተነሳሽነት ሲሆን፥ ለረጅም ዓመታት የተቸገሩ ሕፃናትን በመደገፍ እውቅና ያገኘ ተቋም ነው።

የድርጅቱ ተልዕኮ መሰረታዊ የትምህርት፣ የጤና አጠባበቅ እና አጠቃላይ ደህንነትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ህጻናት እንዲያገኙ በማድረግ አብሮነትን፣ ጸሎትን፣ በጎ አድራጎትን እና የጋራ መደጋገፍን ማጎልበት ነው።

ጸሎት ሕይወትን ይለውጣል
ማኅበሩ በሰሜን አረቢያ ሐዋርያዊት ሃገረ ስብከት ውስጥ መቋቋሙን አስመልክቶ የተደረገው መስዋዕተ ቅዳሴ የተመራው በብጹእ አቡነ አልዶ ቤራርዲ ሲሆን፥ የማህበሩ ሥልጣንም አራት አገሮችን ማለትም ባህሬን፣ ኩዌት፣ ኳታር እና ሳዑዲ አረቢያን ያጠቃልላል ተብሏል። ብጹእነታቸው በሥርዓተ ቅዳሴው ወቅት ባሰሙት ቃለ ምዕዳን ተግባራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጥሪ በማቅረብ፥ በመርሃ ግብሩ ላይ ለተገኙ ሰዎች ባስተላለፉት መልዕክት ለጳጳሳዊ ማኅበሩ ክፍት እንዲሆኑ እና ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ብጹእ አቡነ አልዶ በህፃናት ሕይወት ውስጥ የጸሎትን አስፈላጊነት አፅንዖት በመስጠት፥ “ስለ ህፃናት መጸለይ አለብን፥ ነገር ግን እርስ ለራሳቸው እንዲጸልዩ ማስተማርም አለብን” ብለው ካሳሰቡ በኋላ፥ በማከልም ጸሎት እና የጋራ ድርጊቶች በጣም የተጋለጡ ሰዎችን ሕይወት ሊለውጥ እንደሚችል ጠቅሰዋል።

ጳጳሳዊ የቅዱስ ልጅነት ማኅበር ለህፃናት ቁሳዊ ነገሮችን መስጠት ብቻ ሳይሆን፥ ይልቁንም ከዚያ በላይ የሚዘልቅ እና በህፃናት መካከል ሁለንተናዊ የኃላፊነት እና የአብሮነት ስሜት መፍጠር ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።

የመክፈቻው መስዋዕተ ቅዳሴ ማብቂያ ላይ ወደ 46 የሚጠጉ ህጻናት ለማኅበሩ ያላቸውን ቁርጠኝነት በመግለጽ ለማህበሩ ለመጸለይ፣ ለመካፈል እና ለመርዳት ቃል ገብተዋል።

የማኅበሩ ታሪክ
እ.አ.አ. በ 1880ዎቹ አጋማሽ ላይ ፈረንሣዊ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ቻርለስ ደ ፎርቢን-ጃንሰን በቻይና የሚገኙ ሕፃናት ሚስጥረ ጥምቀትን ሳያገኙ ይሞታሉ የሚለውን ዜና በመስማታቸው፥ የጳጳሳዊ ተልእኮዎች ማኅበር አካል የሆነውን የጳጳሳዊ የእምነት ማኅበር መስራችን እርዳታ በመጠየቅ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተገልጿል።

ብጹእ አቡነ ደ ፎርቢን-ጃንሰን የፈረንሳይ ህፃናትን በጸሎት እና በተጨባጭ ተግባር ለመርዳት ህፃናትን ለማሳተፍ ሀሳብ ነበራቸው። ይህ በመሆኑም እያንዳንዱ ልጅ ቁርጠኝነቱን ለማሳየት በወር አንዴ ‘ጸጋ የሞላሽ ማርያም ሰላም ላንቺ ይሁን” የሚለውን ጸሎት ለመጸለይ እና አንድ ብር ለመስጠት ቃል ገብቶ ነበር። በዚህም መሰረት ማህበሩ እ.አ.አ. ግንቦት 19 ቀን 1843 ዓ.ም. “ህፃናት ህፃናትን መርዳት ይችላሉ” በሚል መሪ ቃል ተመሰረተ።
 

02 Apr 2025, 15:09