ፍቅር በቤተሰ ውስጥ፥ “ሕጻናትን በተሻለ ሁኔታ ስለ ማስተማር”
በደግም ሆነ በክፉ፣ ወላጆች ምንጊዜም በልጆቻቸው ግብረ ገባዊ ዕድገት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ስለሆነም፣ ይህን መሠረታዊ ሚናቸውን ተገንዝበው በማስተዋል፣ በጽኑ መንፈስ፣ በትክክልና በተገቢ አኳኋን መወጣት ይኖርባቸዋል። የቤተሰቦች የማስተማር ሚና እጅግ አስፈላጊና ይበልጥ ውስብስብ በመሆኑ በዝርዝር ለመወያየት እፈልጋለሁ።
ልጆቻችን የት ናቸው?
ቤተሰቦች ስልታቸውን እንደ ገና ማጤንና አዳዲስ ዘዴዎችን መፈለግ ቢኖርባቸውም፣ የድጋፍ፣ የምሪትና የምክር ሥፍራዎች ከመሆን በቀር ሌላ ምርጫ የላቸውም። ወላጆች ልጆቻቸው ለምን ዐይነት ነገር መጋለጥ እንዳለባቸው ማሰላሰል ይኖርባቸዋል፤ ይህም አዝናኛቸው ማን እንደ ሆነ፣ በቴሌቭዥንና በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አማካይነት ወደ ክፍሎቻቸው የሚገባ ማን እንደ ሆነና ትርፍ ጊዜያቸውን ከማን ጋር እንደሚያሳልፉ ማወቅን፣ ማሰብንና መጨነቅን ሊያካትት ይችላል። ለልጆቻችን ጊዜ ብንሰጣቸው፣ ስለ ዋና ዋና ነገሮች በየዋህነትና በተቆርkሪነት ስሜት ብንነግራቸውና ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበትን ጤናማ መንገድ ብናገኝላቸው ከጉዳት ልንታደጋቸው እንችላለን። ንቃት ምንጊዜም አስፈላጊ ነው፣ ችላ ባይነት ከቶ አይጠቅምም። ወላጆች ለምሳሌ ጥቃትን፣ በደልን ወይም የአደንዛዥ ዕጽ ሱሰኝነትን እንዲዋጉ ጨቅላ ሕጻናትና ዐዋቂ ልጆቻቸውን መርዳት አለባቸው።
በሐሳብ መጠመድ ግን ትምህርት አይደለም። አንድ ሕጻን የሚያጋጥመውን ነገር ሁሉ መቆጣጠር አንችልም። እዚህም ላይ ቢሆን ‹‹ ጊዜ ከቦታ ይበልጣል›› የሚለው ብሂል እውነትነት አለው። በሌላ አነጋገር፣ ሂደቶችን መጀመር ቦታዎችን ከመቆጣጠር የበለጠ ዋጋ አለው። ወላጆች ሁልጊዜ ልጆቻቸው የት እንዳሉ በማወቅ ጉጉት ከተጠመዱና እንቅስቃሴያቸውን ሁሉ ከተቆጣጠሩ፣ የእነርሱ ፍላጎት ቦታን መቆጣጠር ብቻ ይሆናል። ይህ ግን ፈተናን እንዲጋፈጡ ልጆችን የማስተማሪያ፣ የማጠናከሪያና የማዘጋጃ መንገድ አይደለም። ዋናው ነገር፣ በነጻነት፣ በማስተዋል፣ በአጠቃላይ ሥነ ሥርዓትና በእውነተኛ ራስን የመቻል መንፈስ እንዲያድጉ በፍቅር ለመርዳት መቻል ነው። ሕጻናት ራሳቸውን ለመከላከልና ችግሮች ሲገጥሙአቸው በማስተዋልና በጥበብ ለማለፍ የሚያስፈልጋቸውን ችሎታ የሚያዳብሩት በዚህ መንገድ ብቻ ነው። ስለዚህ፣ ትክክለኛው ጥያቄ፣ ልጆቻችን በአካል ያሉበት ሥፍራ ወይም በተወሰነ ጊዜ ከማን ጋር እንደ ሆኑ ማወቅ ሳይሆን፣ አሁን ያሉበት ተጨባጭ ሁኔታና፣ በእምነታቸው፣ በግባቸው፣ በምኞታቸውና በሕልሞቻቸው ረገድ ያላቸው አkም ነው። እኔም ለወላጆች የማቀርብላቸው ጥያቄዎች ፡- ‹‹ለመሆኑ ልጆቻችን በጉዞአቸው ላይ ያሉበትን ትክክለኛ ሁኔታ ለመረዳት እንሻለን? ነፍሳቸውስ የት እንዳለች በእርግጥ እናውቃለን? ከሁሉ በላይ፣ ለማወቅስ እንፈልጋለን ?›› የሚሉ ናቸው።
የአእምሮ ብስለት በዘረ መላችን ቀመር ውስጥ ያለ ነገር እድገት ነው ከተባለ ምንም ማድረግ አይቻል ይሆናል። ነገር ግን፣ ማስተዋል፣ መልካም አስተሳሰብና የተፈጥሮ እውቀት የሚወሰኑት በመጠን እድገት ሳይሆን፣ በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ በይበልጥም በነጻነታችን ውስጥ ተሰባስበው በሚገኙ በርካታ ነገሮች ነው። እያንዳንዱ ልጅ የራሳችንን ሐሳብ ዳግመኛ እንድናጤን የሚፈታተኑንን ከዚያ ነጻነት የሚመነጩ ሐሳቦችና ዕቅዶችን ይዞልን መምጣቱ አይቀርም። ይህ ጥሩ ነገር ነው። ትምህርት ነገሮችን በጥሩ ስሜትና በማስተዋል መጋፈጥንና ነጻነትን በኃላፊነት መንፈስ መጠቀምን ያበረታታል። ትምህርት የራሳቸው ሕይወትና የማኅበረሰቡ ሕይወት በእነርሱ እጅ እንደ ሆነና ነጻነት በራሱ ትልቅ ስጦታ እንደ ሆነ በትክክል የሚረዱ ሰዎችን መቅረጽንም ያካትታል።
የልጆች ሥነ ምግባር ሕንጸት
ወላጆች ለልጆቻቸው መሠረታዊ ትምህርት መሰጠቱን ለማረጋገጥ በትምህርት ቤቶች ላይ ቢመረኮዙም፣ የልጆቻቸውን ግብረ ገባዊ ሕንጸት ግን ለሌሎች ሙሉ በሙሉ ከቶ አሳልፈው አይሰጡም። የሰው ስሜታዊና ስነ ምግባራዊ ዕድገት በዋናነት የተመሠረተው ወላጆች የታመኑ ናቸው በሚለው ልዩ ተሞክሮ ላይ ነው። ይህም ማለት ወላጆች፣ በአስተማሪነታቸው፣ በፍቅራቸውና በምሳሌነታቸው በልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ እምነትንና ፍቅራዊ አክብሮትን የማስረጽ ኃላፊነት አለባቸው። ልጆች ቢሳሳቱ እንኳ፣ ለወላጆቻቸው አስፈላጊ ስለ መሆናቸው ወይም ወላጆቻቸው ለእነርሱ ከልብ እንደሚያስቡላቸው ሊሰማቸው ካልቻለ፣ ይህ ሁኔታ ወደ አዋቂነት ዕድሜ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ጉዳት ሊያመጣባቸውና ብዙ ችግሮችን ሊፈጥርባቸው ይችላል። ይህ አካላዊ ወይም ስሜታዊ ግንኙነት አለመኖር አንድ ልጅ አንድን ጥፋት በመፈጸሙ ከሚደርስበት ተግሳጽ የበለጠ ሊጎዳው ይችላል።
ወላጆች የልጆቻቸውን ፍላጎት የመቅረጽ፣ መልካም ባሕርያትንና የበጎነት የተፈጥሮ ዝንባሌን የማዳበር ኃላፊነትም አለባቸው። ይህም አንዳንድ የአስተሳሰብና የአሠራር ስልቶች ተስማሚና ተፈላጊ እንደሆኑና የአሚ እድገት ሂደት አካል መሆናቸውን ማሳየትን ይጨምራል። ከኅብረተሰብ ጋር የመቀላቀል ምኞት፣ ወይም ለተሻለና ይበልጥ ሥርዓት ላለው ለጋራ ሕይወት ሲባል ጊዜያዊ ደስታን የመተው ልማድ በራሱ ለትልቅ እሴቶች ግልጽ መሆንን የሚያበረታታ እሴት ነው። ግብረ ገባዊ ሕንጸት ሁሌም መካሄድ ያለበት ስሜትን የሚኮረኩርና ልጆች የሚገባቸውን kንk በመጠቀም ትምህርት በሚሰጥ ገቢራዊ ዘዴና በውይይት ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ ግብረ ገባዊ ሕንጸት በእውነት ላይ ተመሥርቶ መካሄድ ይኖርበታል። ይህም መደረግ ያለበት ልጆች የአንዳንድ እሴቶችን፣ መርሆችንና መመዘኛዎችን አስፈላጊነት በራሳቸው መንገድ እንዲማሩ በመርዳት እንጂ እነዚህን ነገሮች እንደ ፍጹምና የመጨረሻ እውነቶች አድርጎ በእነርሱ ላይ በግዴታ በመጫን አይደለም።
ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ፣ ከአስፈላጊነቱ አኳያ “ከሁሉ የተሻለ የሚመስለውን ከመገመት” ወይም መደረግ ያለበትን በግልጽ ከማወቅ ይበልጣል። ምንም ያህል ጽኑ ቢሆኑ፣ ብዙውን ጊዜ የራሳችን እምነቶች ራሳቸው ወጥነት የላቸውም። ኅሊናችን ግልጽ የሆነውን ግብረ ገባዊ ውሳኔ ቢነግረንም፣ ሌሎች ምክንያቶች አንዳንዴ ይበልጥ ማራኪና ኃይለኛ ይሆናሉ። አእምሮ ትክክል ነው ብሎ የተረዳው መልካም ነገር እንደ ፍጹም ስሜታዊ ዝንባሌና ከሌሎች ማራኪ ነገሮች ሁሉ እንደሚበልጥ የመልካም ነገር ጥማት ሆኖ በውስጣችን ሥር ወደሚሰድበትና እኛ መልካም ነው ብለን ያሰብነው ነገር ‹‹ለእኛ›› አሁንም እዚህም መልካም መሆኑን እንድንገነዘብ ወደሚያስችለን ደረጃ መድረስ አለብን። ጥሩ የግብረ ገብ ትምህርት አንድ ሰው ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ጥቅሙ ለራሱ መሆኑን ማሳየትን ያካትታል። ዛሬ፣ የሚያስከትለውን ጥቅም በግልጽ ሳያመለክቱ ጥረትና መሥዋዕትነትን የሚጠይቅ ነገር መጠየቅ ውጤታማነቱ እየቀነሰ መጥቶአል።
መልካም ልምዶች መዳበር ያስፈልጋቸዋል። የልጅነት ልማዶች እንኳ ዋና ዋና ውስጣዊ እሴቶችን ወደ ምቹና ዘላቂ የአሠራር ዘዴዎች ለመለወጥ ይረዳሉ። አንድ ሰው ተግባቢና ለሌሎች ሰዎች ግልጽ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን፣ ለረጅም ጊዜያት ታላላቆቹ “እባክህ”፣ “አመሰግናለሁ” እና “አዝናለሁ” ማለትን ካላስተማሩት ውስጣዊ መልካም አkሙ በቀላሉ ጎልቶ ሊታይ አይችልም። ቁርጠኝነትን ማጠናከርና የተወሰኑ ተግባራትን መደጋገም የግብረ ገባዊ ምግባር መገንቢያ መሠረቶች ናቸው፤ አንዳንድ መልካም ባሕርያት ሆን ተብለው፣ በነጻነትና ዋጋ ባለው ሁኔታ ካልተደጋገሙ የግብረ ገብ ትምህርት ሊካሄድ አይችልም። በሚገባ የተቀሰቀሱ ተግባራት በሌሉበት ሁኔታ ምኞት ወይም በአንድ እሴት መማረክ ብቻ ጥሩነትን ለማስረጽ በቂ አይሆንም።
ነጻነት ድንቅ ነገር ቢሆንም፣ ሊባክንና ሊጠፋ ይችላል። የግብረ ገብ ትምህርት በሐሳብ፣ በማበረታቻ፣ በተግባራዊ ልምድ፣ በቅስቀሳ፣ በሽልማት፣ በምሳሌ፣ በአምሳያ፣ በምልክት፣ በማሰላሰል፣ በምክር፣ በውይይትና ነገሮችን የምናከናውንባቸውን መንገዶች ያለመታከት በማጤን ነጻነትን ከማዳበር ጋር የተያያዘ ነው። እነዚህ ሁሉ በቀጥታ መልካም ነገርን ወደ ማድረግ የሚመሩንን የተረጋጉ ውስጣዊ መርሆች ለማዳበር የሚረዱ ናቸው። ጥሩነት ጽኑ ውስጣዊ የአሠራር መርሆና እምነት ነው። ስለዚህ፣ ጥሩ ሕይወት ነጻነትን ይገነባል፣ ያጠናክራል፣ ይቀርጻል፤ ሰብአዊ ክብርን የሚያዋርድ የጸረ ኅብረተሰብ ዝንባሌ ባሮች እንዳንሆን ያደርገናል። ምክንያቱም ሰብአዊ ክብር ራሱ እያንዳንዳችን ‹‹ከውስጥ በመነጨና በተቀሰቀሰ ግላዊ መንገድ በማስተዋልና በነጻ ምርጫ እንድንመላለስ›› ይጠይቀናል።
ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርዕሥ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 259-268 ላይ የተወሰደ።
አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በርግኔ