የመለኮታዊ መገለጥ መነገር
የመለኮት መገለጥ የሚነገረው ለምንና እንዴት ነው?
እግዚአብሔር “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ ይፈልጋል” (1ኛ ጢሞ. 2፡4)። እርሱም ኢየስስ ክርስቶስ ነው። ስለዚህ፣ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ” (ማቴ. 28፡19) በሚለው በራሱ ትእዛዝ መሠረት ክርስቶስ ሊሰበክ ይገባል። ይህም የሚፈጸመው በሐዋርያዊ ትውፊት ነው።
ሐዋርያዊ ትውፊት ምንድነው?
ሐዋርያዊ ትውፊት ከክርስትና እምነት መጀመሪያ አንሥቶ በስብከት፣ በምስክርነት፣ በተቋማት፣ በአምልኮ እና በመንፈሳዊ ጽሑፎች አማካይነት የክርስቶስን መልእክት ማስተላለፍ ነው። ሐዋርያት ከክርስቶስ የተቀበሉትንና ከመንፈስ ቅዱስ የተማሩትን ሁሉ ለተከታዮቻቸው፣ ለጳጳሳት፣ በእነርሱም በኩል ለትውልዶች በሙሉ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ አስተላለፉ።
ሐዋርያዊ ትውፊት የሚገኘው በምን ዐይነት መንገድ ነው?
ሐዋርያዊ ትውፊት የሚገኘው በሁለት መንገዶች ነው፤ እነርሱመ ቃለ እግዚአብሔርን ሕያው በሆነ መንገድ (በአጭሩ በትውፊት) ማስተላለፍና በጽሑፍ መልክ ድኀነትን መስበክ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ አማካይነት ነው።
በትውፊትና በመጽሐፍ ቅዱስ መካከለ ያለው ግንኙነት ምንድነው?
ትውፊትና መጽሐፍ ቅዱስ በቅርብ የተሳሰሩና እርስ በርስ የሚገናኙ ናቸው። እያንዳንዳቸውም በቤተክርስትያን ውስጥ የክርስቶስን ምስጢር ሕያውና ፍሬያማ የሚያደርጉ ናቸው። ከአንድ መለኮታዊ ምንጭ የሚነሡና ቤተክርስያን ስለራእይ እርግጠኛነትዋን የምታገኝበት የእምነት የተቀደሰ ሀብት መሠረት ናቸው።
የእምነት መዝገብ አደራ የተሰጠው ማን ነው?
ሐዋርያት የእምነትን መዝገብ ለመላዋ ቤተክርስቲያን አደራ ሰጥተዋል። ሕዝበ እግዚአብሔር በሙሉ ለእምነት ካለው የላቀ ስሜት የተነሣ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታና በቤተክርስቲያን የበላይ አመራር መሪነት መለኮታዊ የመገለጥ ስጦታን ከመቀበል፣ ወደ ሥራ ጠልቆ ከመግባትና በሙላት ከመኖር አያቋርጥም።
የእምነት ቅርስ በሐቅ የመተርጐም ሥራ የተሰጠው ለማን ነው?
የእምነትን ቅርስ በሐቅ የመተርጎም ሥራ የተሰጠው ለቤተክርስቲያን ሕያው የማስተማር ሥልጣን ላላቸው ማለትም የጴጥሮስ ተከታይ ለሆኑት ለሮም ጳጳስ እና ከእርሳቸውም ጋር ለጳጳሳት ነው። በመለኮት መገለጥ ውስጥ የሚገኙ እውነቶችና ድንጋጌዎች የሆኑትን ቀኖናዎች የማስረዳት ሥራም የዚህ በቃለ እግዚአብሔር አገልጋይነቱ የተወሰነ የእውነት ጸጋ የተሰጠው የቤተክርስቲያን የበላይ አመራር ነው። ይህ የቤተክርስቲያን የበላይ አመራር ሥልጣን ከራእይ ጋር የተገናኙ እውነቶችንም ያካትታል።
በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በትውፊትና በቤተክርስቲያን የበላይ አመራር መካከል ያለው ግንኙነት ምንድነው?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ትውፊትና የቤተክርስቲያን የበላይ አመራር እርስ በርሳቸው በቅርብ የተሣሠሩ ከመሆናቸው የተነሣ አንዱ ያለ ሌላው ሊቆም አይችልም። በአንዱ በመንፈስ ቅዱስ ሥር ሆነው እያንዳንዳቸው በራሳቸው መንገድ በጋራ በመሥራት ለነፍሳት ደኀንነት ሁሉም ውጤታማ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ
መጽሐፍ ቅዱስ እውነትን የሚያስተምረው ለምንድነው?
እግዚአብሔር ራሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ ስለሆነ ነው። ስለዚህ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ የተቀሰቀሰና ለደኀንነታችን አስፈላጊ የሆኑ እውነቶችን ያለ ስሕተት የሚያስተምር መሆን አለበት። እርሱ ሊያስተምረን የፈለገውን ነገር የጻፉትን ሰብአዊ ደራሲያንን የቀሰቀሰው መንፈስ ቅዱስ ነው። ይሁን እንጂ፣ ክርስቲያናዊ እምነት “የመጽሐፍ እምነት” ሳይሆን የቃለ እግዚአብሔር ይኸውም “የተጻፈ ወይም ድምፅ አልባ ቃል ሳይሆን ሥጋ የለበሰና ሕያው ቃል” እምነት ነው (ቅዱስ በርናርዶስ ዘክለይርቮ)።
መጽሐፍ ቅዱስ የሚነበበው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ መነበብና መተርጎም የሚገባው በመንፈስ ቅዱስ እርዳታና በቤተክርስቲያን የበላይ አመራር መሪነት በሚከተሉት ሦስት መመዘኛዎች መሠረት ነው።
1. መጽሐፍ ቅዱስ ሲነበብ ለመላው መጽሐፍ ቅዱስ ይዘትና አንድነት ትኩረት በመስጠት መሆን አለበት
2. በቤተክርስቲያን ሕያው ትውፊት ውስጥ ሆኖ መነበብ አለበት።
3. ለእምነት መመሳሰል ማለትም በራሳቸው በእምነት እውነቶች መካከል ላለው ውስጣዊ ህብር ትኩረት በመስጠት መነበብ አለበት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና ምንድነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና ቤተክርስያን በሐዋርያዊ ትውፊት አማካይነት የተቀበለቻቸው የቅዱሳት መጻሕፍት ሙሉ ዝርዝር ነው። ቀኖናው 46 የብሉይ ኪዳንና 27 የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ያካተተ ነው።
ብሉይ ኪዳን ለክርስቲያኖች ያለው ጠቀሜታ ምንድነው?
ክርስቲያኖች ብሉይ ኪዳንን እንደ እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል ያከብሩታል። የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ በመለኮት የተቀሰቀሱና ዘላቂ ዋጋ ያላቸው ናቸው። እነዚህ መጻሕፍት የእግዚአብሐርን አዳኝ ፍቅርና መለኮታዊ ትምህርት የሚመሰክሩ ናቸው። የተጻፉትም፣ ከሁሉም በላይ የመድኃኔ ዓለም ክርስቶስን መምጣት ለማዘጋጀት ነው።
አዲስ ኪዳን ለክርስቲያኖች የሚሰጠው ጠቀሜታ ምንድነው?
ዋና ዓላማው ኢየሱስ ክርስቶስ የሆነው አዲስ ኪዳን የመለኮታዊ ራእይና የመጨረሻ እውነት ያሳውቀናል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙት አራቱ የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስ ወንጌሎች የኢየሱስ ሕይወትና ትምህርት ዋና ምስክሮች በመሆናቸው የቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ እምብርት ናቸው። በመሆኑም በቤተክርስቲያን ውስጥ ልዩ ቦታ አላቸው።
በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል ያለው አንድነት ምንድነው?
የእግዚአብሔር ቃል አንድ እስከሆነ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስም አንድ ነው። የእግዚአብሔር የማዳን ዕቅድ አንድ ነው፣ የሁለቱመ ኪዳናት መለኮታዊ ቅስቀሳ አንድ ነው። ብሉይ ኪዳን ለአዲስ ኪዳን ማዘጋጃ ሲሆን፣ አዲስ ኪዳን ደግሞ የብሉይ ኪዳን ፍጻሜ ነው፤ ስለዚህ አንዱ የሌላው ማብራሪያ ነው።
በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ሚና ምንድነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተክርስቲያን ሕይወት ድጋፍና ኃይል ይሰጠዋል። ለእግዚአብጀሔር ልጆች የእምነት ብርታት፣ የነፍስ ምግብ የመንፈሳዊ ሕይወት ምንጭ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የነገረ መለኮትና የሐዋርያዊ ስብከት እስትንፋስ ነው። መዝሙረኛው ዳዊት “ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው” (መዝ. 119፡105) ይለዋል። ስለዚህ፣ ቤተክርስቲያን ሁሉም ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር እንዲያነብ ታበረትታለች፣ ምክንያቱም “መጽሐፍ ቅዱስን አለማወቅ ክርስቶስን አለማወቅ ነውና” (ቅዱስ ጀሮም)።
NJͭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዩሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ካጸደቁት፣ በአጭሩ ከተጻፈው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ከዋናው ከላቲን ቅጂ ከተተረጎመው መጽሐፍ ከአንቀጽ 78-141 ላይ የተወሰደ።