MAP

ዓርባ ጾም ዓርባ ጾም 

ዓርባ ጾም

እግዚአብሔር በተወሰነ ጊዜና አደራረግ ከአንዳንድ ምግቦች እንድንከለከል ማለትም እንድንጾም ይፈልጋል። "ጾምን ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ ሽምግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ ጌታ ቤት ሰብስቡ፥ ወደ ጌታም ጩኹ" (ት. ኢዩኤል 1፡14) ይለናል። ጾም እግዚአብሔርን የሚያስደስት ለነፍሳችን ደግሞ አስፈላጊ መንፈሳዊ ተግባር ነው። ለሥጋችን መግቻ ልጓም ተጋድሎም ነው። በጾም ሥጋችንን እንቀጣዋለን እናደክመዋለን። የኃጢአታችንን ምሕረት ደግሞ እንለምናለን።

ኢየሱስ ጾም አስፈላጊ እንደሆነ ሊያስረዳን አርባ ቀን ጾመ። ቤተክርስቲያን ደግሞ ፈለጉን በመከተል ልጆቹ ሁሉም እንዲጾሙ አዘዘቻቸው። ፍውንም አይታ በአመት ብዙ ጊዜ እንዲጾሙ ፈለገች ። ከብዙዎቹ የሕዝበ ክርስቲያን ጾሞች አንዱ ሕዝቡ በአክብሮት የሚያየውና በተስፋ የሚጠብቀው የአርባ ጾም ነው። ይህ የጾም ጊዜ የኢየሱስን ጾም ያስታውሰናል። በተለይም ደግሞ የደኀንነታችን መጨረሻ የሆነውን የትንሣኤ በዓል ማስተናገጃ በመሆኑ ቤተክርስቲያን በጥሩ ሁኔታ ጾአን እንድናሳልፈው ትመክረናለች።

በአርባ ጾም መግቢያ ላይ ቤተክርስቲያን "እነሆ የተመረጠው ሰዓት አሁን ነው፤ የደኀንነት ቀን አሁን ነው። አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ በምንም ነገር፤ ለማንም መሰናከያ አንሆንም። ይልቅስ መከራን ችግርን ጭንቀትንም እየታገስን የእግዚአብሔርን አገልጋዮች መሆናችንን በሁሉም በኩል እንገልጣለን" (2ኛ ቆሮ 6፣2) የሚውለን የቅዱስ ጳውሎስን ቃል እየጠቀሰች አርባ ጾም ምን እንደሆነ እንዴት አድርገን ማሳለፍ እንደሚገባን ታስተምረናለች።

ዓርባ ጾም ቅዱስ ወቅት የጸጋና የደኀንነታችን ጊዜ ነው። እንደዚህ ከሆነ በቅድስና ልናሰልፈው፣ጸጋውንም ልንጠቀምበት ይገባል። ይህንንም እንድናደርግ ከላይ የጠቀስነውን የቅዱስ ጳውሎስን ቃል እንከተል። እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ሐሳብ አርባ ጾምን በሚገባ እንድናከብረው በመጀመሪያ ኃጢአትን መተው ቀጥለን ደግሞ መልካም ሥራ ማዘውተር አለብን።

ሶ/ ኃጢአትን መተው፣«በምንም ነገር ለማንም መሰናከያ አንሆንም» ይለናል እግዚአብሔርና ባልንጀራችንን የሚያሳዝ ሃይማኖታችንን የሚያስነቅፍ ሥራ ማድረግ የለብንም። በአነጋገራችን ወይም በሥራችን አምላክንና ሰውን እንዳንበድል መፍራት አለብን። ስለዚህ ከመጥፎ ንግግር (ውሸት፣ስድብ፣ሐሜት፣እረግማን) ከመጥፎ ሥራ (ቂም መያዝ፣ ዓመጽ፣ ጥል፣ ሌብነት፣ አመንዝራነት፣ ባልንጀራን በሆነ መንገድ መጉዳት …) መጠንቀቅ አለብን። ይህም የመልካም ሥራ መሠረት ነው።

ለ/ መልካም ማድረግ፣ «መከራንና ችግርን ጭንቀትንም እየታገስን የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆናችንን በሁሉ በኩል እንገልጣለን» እያለ ያሳስበናል። ኃጢአትን ስንተው መልካም ሥራን ደግሞ ማድረግ አለብን። ቆሻሻ ልብስ አውልቀን ንጹሑን እንደምንለብስ እንደዚሁም ደግሞ የኃጢአት ልብስን አውልቀን የጽድቅ ልብስ መልበስ አለብን። በእውነት የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሚያደርገን እርሱን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ስንፈጽም ነው። ይህም ደግሞ ፍቅር፣ ጸሎት፣ ተጋድሎ፣ ጾም፣ትሕትና፣ትዕግስት፣ምሕረት ነው። ከአምላክ ቀጥለን በአምሳሉ የፈጠረውን ባልንጀራችንን ልናከብረውና ልናስደስተው ይገባናል። በመሆኑም ከማንኛውም ሰው ጋር የመቃረን፣የጥላቻ፣የአምባጓሮ ምልክት እንዳይኖረን ብቻ ሳይሆን ፍቅርም እንዲኖረን ያስፈልጋል። በዚህ ዓይነት መንፈስ ነው አርባ ጾም በጥሩ ሁኔታ ሲያልፍ አምላክን ሊያስደስት እኛንም ሊጠቅመን የሚችለው ።

ብዙ ግዜ በሂደት ዋናው ነገር ይረሳና ሌላ ተጨማሪ ነገር እናደርጋለን። የሚበዛው ጾም ቢሆንም ዋናው ነገር (መጥፎ ነገርን መተው መልካም ነገርን ማድረግ) ቸል በማለት ለውጫዊው ነገር እንጨነቃለን። አንዳንዶቹ ክርስቲያኖች ይሰከራሉ፣ ይጨፍራሉ፣ ይሰርቃሉ፣ ያመነዝራሉ፣ ያምጻሉ፣ ባልንጀራቸውን ይጠላሉ። ለትልቅ ኃጢአት አይጨነቁም ለጾም ግን ይጨነቃሉ። እንዳያፈርሱ ብለው እስከ ሞት ይደርሳሉ። ነፍሳቸውን ግን በትልቅ ኃጢአት እንዳትበላሽ የሚያደርጉትን ነገር የለም። እንደዚህ ዓይነቱን እግዚአብሔር «እኔ የምፈልገው ጾም የዚህ ዓይነት ጾም ነውን? ይህንን ደግሞ ጾም ትሉታላችሁን? የዚህ ዓይነት ጾም ጸሎታችሁ እንዳይሰማ ያደርገዋል» (ኢሳ. 58፣3) እያለ ይናገራቸዋል። ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ጽድቅ እንዴት ከኃጢአት ጋር ልትሆን ትችላለች? እንዴትስ ብርሃን ከጨለማ ጋር ሊተባበር ይችላል?» (2ኛ ቆሮ. 6፣10) እያለ ይናገራል። «ስንጾም ሕይወታችን ከቅድስና መንፈስ ጋር የማይስማማ ከሆነ አረማውያን ይንቁናል መጥፎ ልማዳቸውም የእምነታችን ተቃራኒ ሆኖ ይገኛል። ዋናው ቁም ነገር ምግብን መተው ሳይሆን ኃጢአትን በመተው ላይ ነው» ይላል ቅዱስ ጎርጎርዮስ ትልቁ ውጫዊ ጾማችን ከውስጣዊ ጾማችን (ከኃጢአት መከላከል) ጋር ካልተባበረ ፍሬ የለውም ጐደሎ ነው። በመጀመሪያ ከምግብ ከመከልከላችን በፊት ከኃጢአት መከላከል እንዳለብን አንዘነጋ። ኃጢአት በተፈጥሮ ክፋ በመሆኑ ክልክል ነው። ጾም ያለው ምግብ ግን በተፈጥሮ መጥፎ ባይሆንም ኃጢአት የሚሆነው ስለ ተከለከለ ነው። የሚከለከልበት ጊዜ ደግሞ የተወሰነ ነው። ሁል ጊዜ አይደለም። እምነት ያለ ሥራ የሞተች ናት። መልካም ሥራ ደግሞ ያለ እግዚአብሔር ጸጋ ፍሬ የለውም። እንደዚሁም ጾም ያለ ንጽሕና ፍሬ የለውም። ጥሩ ምግብን በቆሻሻ ዕቃ እንደማቅረብ ነው።

ዓርባ ጾማችን ጥቅም ያለው እንዲሆን ከፈለግን የቅዱስ ጳውሎስን ምክር እንከተል። ጾማችን ውጫዊ እንዲሆን እናድርገው። በሥጋችንና በመንፈሳችን እንጹም። ከኃጢአትና ከጥፋት እየተከላከልን መልካም ተግባር እያደረግን ለፋሲካ እንሰናዳ።

 

07 Mar 2025, 13:28