MAP

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ ልማት ኮሚሽን 25ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ ልማት ኮሚሽን 25ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ 

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ ልማት ኮሚሽን 25ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ማሕበራዊ ልማት ኮሚሽን (ካቶሊክ ካሪታስ ኢትዮጵያ) 25ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ውስጥ በሚገኘው የሰላም አዳራሽ ውስጥ አካሂዷል።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ማሕበራዊ ልማት ኮሚሽን ባካሄደው 25ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንት፣ ብጹአን ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ጽህፈት ቤቱ ዋና ጸሃፊ፣ የቦርድ አባላት፣ የሃገረ ስብከቶች ማህበራዊ ልማት ኮሚሽን ተወካዮች፣ የጠቅላይ ጽህፈት ቤቱ የሥራ ሃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

25ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ብጹእ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ በጸሎት እና በመግቢያ ሃሳብ ያስጀመሩ ሲሆን፥ ብጹእነታቸው በያዝነው ዓመት ላይ አዲስ የተቀቡትን ብጹአን ጳጳሳት በማስተዋወቅ ጉባኤው ቤተክርስቲያኒቷ በምትታወቅበት የልማት ሥራዎች ይበልጥ ጠንክራ እንድትሰራ፣ አዳዲስ እቅዶችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ በማሳሰብ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አደራ ብለዋል።

በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የ 2024 ዓ.ም. የሥራ አፈፃፀም እና የ 2025 ዓ.ም. ደግሞ የ 11.6 ቢሊየን ብር በጀት ቀርቦ የፀደቀ ሲሆን፥ በዚህም ከ5.9 (5,926,777) ሚሊዮን ሰዎች በላይ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ እና ከተጠቃሚዎች ፆታዊ ስብጥርም አንፃር የሴት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከባለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነፃጸር ብልጫ ማሳየቱም ተመላክቷል።

ከዚህም ባሻገር የማህበራዊ ልማት ጽ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ሞገስ የልማት ኮሚሽኑን የተሻሻለውን መመሪያ ደንብ ለጉባኤው ያቀረቡ ሲሆን፥ ይህ መመሪያ ደንብ በተለይም ቤተክርስቲያን ለቀጣይ አሥር ዓመታት ለመተግበር ያቀደችውን የ10 ዓመት ዕቅድ መሰረት በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው ለጉባኤው አባላት የተሻሻለውን ደንብ በማቅረብ፥ የጉባኤው አባላት በተሻሻለው ደንብ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ደንቡን አጽድቀዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ማሕበራዊ ልማት ኮሚሽን ወይም በአሁኑ ወቅት ‘ካቶሊክ ካሪታስ ኢትዮጵያ’ በሚል ስሙን ለመቀየር ሂደት ላይ ያለው ተቋም በ 1957 ዓ.ም. እንደተመሰረተ እና፥ በ 1992 ዓ.ም. ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት እውቅና አግኝቶ መመዝገቡ የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያሳያል። የመጀመሪያ ተልዕኮውንም ያደረገው በኢትዮጵያ የዓለም አቀፏን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የማህበራዊ እና ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ሥራ ማስተዋወቅ እና ማስተባበር እንደሆነ እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ከ150 ዓመታት በፊት ጀምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ተበታትነው ሲሠሩ የነበሩትን የልማት ሥራዎች አንድ ላይ በማቀናጀት፥ የ13 ቱንም ሃገረ ስብከቶች እንዲሁም 67 የሚሆኑ ማህበረ ምዕመናን ከብሄራዊ ጽህፈት ቤቱ ጋር አንድ ላይ ሆኖ በተዋቀረ ሁኔታ በሁሉም ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች እንዲሠራ ተደርጓል።

ቤተክርስቲያኒቷ ለሁለንተናዊ የሰው ልጅ እድገት ላይ በርካታ ሥራዎችን እየሰራች እንደመሆኑ መጠን በየሃገረ ስብከቶቹ ከምታከናውናቸው ሃዋሪያዊ ሥራዎች ጎን ለጎን፥ በስፋት ስትሰራቸው የነበሩትን  የማህበራዊ ልማት ኮሚሽን መርሃ ግብሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት፣ በሂደት በገጠርና በከተማ በህዝቡ ህይወት ላይ ዘላቂ ለውጥ በማምጣት ረገድ የሚታይ ስኬት እያስመዘገቡ እንደሚገኙ፥ ብሎም ቤተክርስቲያኒቷ በማህበራዊ ኮሚሽኑ በኩል ጥራት ያለው ትምህርት፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ እና የምግብ ዋስትና፣ የማህበራዊ መልሶ ማቋቋም፣ የውሃ ሥራዎች፣ የአካባቢ ጽዳትና ንፅህና፣ የጤና እና የኤች አይ ቪ/ኤድስ ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን፣ ከስደት እና ከስደተኞች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች፣ በሴቶች እና ቤተሰብ ጉዳዮች እንዲሁም አቅምን በማጎልበት በማህበረሰብ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ እየሰራች ትገኛለች። ይህ ብቻም ሳይሆን፥ የልማት ፕሮግራሞችን በማበልፀግ እና የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት ዘመቻዎችን በሴቶች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ በኩል የማጎልበት ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል።

ካሪታስ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሃገራት የካሪታስ አባላት ማለትም፥ ከሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ኢሲያ እና አውስትራሊያ ካሉ፥ እንዲሁም እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ጽ/ቤት ያላቸዉም ሆነ የሌላቸው አጋር አካላት ከሆኑ፥ ለአብነትም ሲ አር ኤስ የተባለው የአሜሪካ የጳጳሳት ጉባኤ አካል የሆነው የሰብአዊ ዕርዳታ ድርጅት ከዋነኞቹ አጋር ድርጅቶቻችን አንዱ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፥ ከእነዚህም የእርዳታ ድርጅቶች የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፎችን ያገኛል ተብሏል። በዚህ ዓመት ብቻ ከ 5.6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አግኝታ በተለያዩ የሃገሪቷ ክፍሎች ላይ በርካታ ሥራዎችን ለመስራት እንዳቀደች ተገልጿል።

በጉባኤው ማጠቃለያ ላይም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አዲሱ የአሜሪካ መንግስት ‘ዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ’ ን (US AID) በማስመልከት ያወጣው የሥራ ማስፈጸሚያ ትዕዛዝ በቤተክርስቲያን የልማት ሥራዎች ላይ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ጫና ለመቀነስ የሚረዱ ስልታዊ አቅጫዎች ለጉባኤው ቀርቧል። በዚህም መሰረት ቤተክርስቲያን የሀገር በቀል የገቢ ማሰባሰቢያ አማራጮችን፣ ሁሉንም የቤተክርስቲያን አካላት እና ምዕመናንን ያሳተፉ የማህበራዊ ልማት ሥራዎች ላይ ማተኮር እና ዘላቂ የሆኑ የማህበራዊ ልማት እና የሰብዓዊ ተግባራትን የሚደግፉ አማራጮችን ለመጠቀም አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።

የማሕበራዊ ልማት ኮሚሽኑ ዋና ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ ሲሆን፥ 13 የሀገረ ስብከት አስተባባሪ ጽህፈት ቤቶች እና ንኡስ ጽህፈት ቤቶች በመላ አገሪቱ ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜም ከ3000 በላይ ሰዎች በ ‘ካቶሊክ ካሪታስ ኢትዮጵያ’ ተቀጥረው እየሰሩ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

28 Mar 2025, 10:08