MAP

የመጋቢት 21/2017 ዓ.ም  ዘገብርኄር ዕለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የመጋቢት 21/2017 ዓ.ም ዘገብርኄር ዕለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የመጋቢት 21/2017 ዓ.ም ዘገብርኄር ዕለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ  ንባባት

1.    2ጢሞ 2:1-15 

2.    1ጴጥ 5:1-11

3.    ሐዋ 1:6-8 

4.    ማቴ 25:14-30

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የመክሊቶቹ ምሳሌ

“የእግዚአብሔር መንግሥት አገልጋዮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት በዐደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሊሄድ የተነሣ አንድ ሰውን ትመስላለች፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በመደልደል ለአንዱ አምስት መክሊት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ መክሊት ሰጥቶ ጕዞውን ቀጠለ። አምስት መክሊት የተቀበለው ሰውየ፣ ወዲያው በገንዘቡ ንግድ ጀምሮ አምስት መክሊት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት መክሊት የተቀበለው ሁለት አተረፈ፤ አንድ መክሊት የተቀበለው ግን መሬት ቈፍሮ የጌታውን ገንዘብ ደበቀ።

“የአገልጋዮቹም ጌታ ከብዙ ጊዜ በኋላ ከሄደበት ተመልሶ የሰጣቸውን ገንዘብ ተሳሰበ። አምስት መክሊት የተቀበለውም፣ ሌላ አምስት ተጨማሪ መክሊት ይዞ በመቅረብ፣ ‘ጌታ ሆይ! አምስት መክሊት ዐደራ ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸውልህ አምስት ተጨማሪ መክሊት አትርፌአለሁ’ አለው።

“ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። “እንዲሁም ሁለት መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሁለት ተጨማሪ መክሊት አትርፌአለሁ’ አለው።

“ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። “አንድ መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ ፈራሁህ፤ ሄጄም መሬት ቈፍሬ መክሊትህን ጕድጓድ ውስጥ ደበቅሁት፤ ገንዘብህ ይኸውልህ’ አለው።

“ጌታውም መልሶ፣ ‘አንተ ክፉ፣ ሰነፍ አገልጋይ፤ ካልዘራሁበት የማጭድ፣ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ መሆኔን ታውቅ ኖሯል? ታዲያ፣ በምመለስበት ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እንዳገኘው ለለዋጮች መስጠት ይገባህ ነበር።

“ ‘በሉ እንግዲህ መክሊቱን ወስዳችሁ ዐሥር መክሊት ላለው ስጡ፤ ላለው ይጨመርለታል፤ የተትረፈረፈም ይኖረዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ይህን የማይረባ አገልጋይ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት’ አለ።

የእለቱ ቃለ እግዚአብሔር አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ! ዛሬ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት አምልኮ አቆጣጠር ዘገብርኄር የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን። ይህ ስደተኛው የዓብይ ፆም ሰንበት ዘግብርኄር ተብሎ የሚጠራበት ምክንያት በዚሁ ሰንበት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ከዋዜማው ጀምሮ “ገብርኄር ወገብር ምእመን ገብር ዘአሥመሮ ለእግዚኡ፣ ገብርኄር ወገብር ምእመን ዘበውሁድ ምእመን ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሰይመከ...” (ጌታውን ያስደሰተ አገልጋይ ታማኝ እና ቸር አገልጋይ ነው፣  በጥቂቱ የታመንክ ቸር አገልጋይ ሆይ በብዙ እሾምሃለሁ፣ ጌታው የሚያገኘውና በገንዘቡ ሁሉ ላይ የሚሾመው ቸርና የታመነ አገልጋይ ማነው?) እየተባለ የሚዜምበት ሰንበት በመሆኑ የተነሳ ነው። በተጨማሪም እንደ እንደ ቸር አገልጋዮች እና በሰማይ ባለው መንግሥተ እግዚአብሔር እስከሚገቡ ድረስ ጌታቸውን ደጅ እንደሚጠኑ እንደ ክርስቶስ አገልጋዮች ሁኑ። ጹሙ፣ ጸልዩ እንደ በጎ አገልጋዮች ለእግዚአብሔር ተገዙ፣ እያለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የካህናትንና የምእመናንን የጽድቅ ሥራ በመልካም አገልጋይ ሥራ፣ የኃጥያንን የበደል ሥራ በክፉ አገልጋይ ሥራ እያመሳሰለ በወንጌል ያስተማረውን ትምህርት በአጠቃላይ ስለጻድቃንና አጥያን በምሳሌ የተናግረውን ቃለ ወንጌል እየጠቃቀሰና እያነሣሣ ስለሚዘመር ሰንበቱ "ገብርሄር" ተብሎ ተጠርቷል። ይህ ሰንበት የጻድቃን መታሰቢያ ሰንበት ነው።

በዛሬው እለት የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል የመክሊቶችን ምሳሌ ይሰጠናል (ማቴ. 25፡14-30)። አንድ ሰው ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ለአገልጋዮቹ መክሊት ሰጠ፤ በዚያን ጊዜ ዋጋ ያለው ሳንቲም ነበረ፤ ለእያንዳንዱ እንደ አቅሙ አምስት መክሊት ለአንዱ አገልጋይ፣ ለአንዱ ሁለት፣ ለአንዱ ደግሞ አንድ መክሊት ሰጠ።  አምስት መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ሂዶ ነገደበት እና ሌላ አምስት አተረፈ። ሁለት የተቀበለው አገልጋይም እንዲሁ አደረገና ሌላ ሁለት አተረፈ። ሆኖም አንድ የተቀበለው አገልጋይ ጉድጓዱን ቆፍሮ የጌታውን ሳንቲም ደበቀ፣ ቀበረ።

ጌታው በተመለሰ ጊዜ፣ ይህ አገልጋይ የድርጊቱን ምክንያት ሲያስረዳ፡- “መምህር ሆይ፣ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንክበት የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንክ አውቃለሁ፣ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት” (ማቴ 25፡24-25) አለው። ይህ አገልጋይ ከጌታው ጋር የሚታመን ዝምድና አልነበረውም፣ ነገር ግን ፈራው እናም ፍርሃቱ እንቅፋት ሆነበት። ፍርሃት ሁል ጊዜ የማይንቀሳቀስ እና ብዙ ጊዜ ወደ መጥፎ ምርጫዎች ይመራል። ፍርሃት ተነሳሽነትን እንዳንወስድ ያደርገናል፤ አስተማማኝ እና የተረጋገጡ መፍትሄዎች ላይ ብቻ እንድንጠለጠል ያነሳሳናል፣ እናም ምንም ጥሩ ነገር እንዳናሳካ ያደርገናል። ወደ ፊት ለመራመድ እና በህይወት ጉዞ ላይ ለማደግ ፍርሃት ሊኖረን አይገባም፣ እምነት ሊኖረን ግን ይገባል።

ይህ ምሳሌ የእግዚአብሔር እውነተኛ ጽንሰ-ሐሳብ እንዲኖረን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል። እኛን ለመቅጣት የሚፈልግ ጨካኝ፣ ምሕረት የለሽ እና አስፈሪ ጌታ ነው ብለን ማሰብ የለብንም። ይህ የተሳሳተ የእግዚአብሔር መልክ በውስጣችን ካለ ህይወታችን ፍሬያማ ሊሆን አይችልም፣ ምክንያቱም በፍርሃት ውስጥ እንኖራለን እና ይህ ወደ ምንም ገንቢ ነገር አይመራንም። በተቃራኒው ፍርሃት ሽባ ያደርገናል፣ የእኛን መጥፋት ያስከትላል። ስለ እግዚአብሔር ያለን አመለካከት ምን እንደሆነ ለማወቅ እንድናስብ ተጠርተናል። ቀድሞውንም በብሉይ ኪዳን ራሱን “መሐሪና ይቅር ባይ፣ ከቍጣ የራቀ ምሕረቱና ታማኝነቱ የበዛ” (ዘፀ 34፡6) በማለት ገልጿል። ኢየሱስም እግዚአብሔር ጨካኝ ወይም ትግሥት የለሽ ጌታ ሳይሆን ፍቅር፣ ርኅራኄ፣ በጎነት የተሞላ አባት መሆኑን ሁልጊዜ አሳይቶናል። ስለዚህ በእርሱ ላይ ትልቅ እምነት ሊኖረን ይችላል፤ ደግሞም ሊኖረን ይገባል።

ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ልግስና እና እንክብካቤ በብዙ መንገዶች ያሳየናል፡ በቃሉ፣ በተአምራቱ፣ ለሁሉም ሰው፣ በተለይም ለኃጢአተኞች፣ ለታናናሾች እና ለድሆች አቀባበል የምያደርግ አባት አድርጎ ያቀርብልናል። ነገር ግን ሕይወታችንን በከንቱ እንዳናባክን ፍላጎቱን በሚያሳየው ምክርም እንዲሁ ያደርጋል። በእርግጥም እግዚአብሔር ለእኛ ታላቅ ክብር እንዳለው የሚያሳይ ምልክት ነው፡ ይህ ግንዛቤ በድርጊታችን ሁሉ ኃላፊነት የሚሰማን ሰዎች እንድንሆን ይረዳናል። ስለዚህ የምክሊቱ ምሳሌ “መክሊቱን ሳንቀብር”፣ ማለትም እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታዎች እና ለዚህም ተጠያቂ እንድንሆን የሚጠራንን፣ አዳዲስ መንገዶች ላይ መራመድ የሚያስችል የግል ኃላፊነት እና ታማኝነትን ያስታውሰናል።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ያ ጌታ አምስት መክሊት ለመጀመሪያው አገልጋይ፣ ሁለት ለሁለተኛው እና አንድ ለሦስተኛው አደራ እንደ ሰጠ በድጋሚ ልናስታውስ ይገባል። እነዚህ ሦስቱ አገልጋዮች ትርፍ ማግኘት አለባቸው። የመጀመሪያው እና ሁለተኛው አገልጋዮች እያንዳንዳቸው የካፒታላቸውን የመጀመሪያ እሴት በእጥፍ ያሳድጋሉ። ሦስተኛው ግን ሁሉንም እንዳያጣ በመፍራት የተቀበለውን መክሊት ጉድጓድ ውስጥ ቀበረው። ጌታው ሲመለስ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ምስጋና እና ሽልማቶችን ይቀበላሉ፤ ሦስተኛው ግን የተቀበለውን ሳንቲም ብቻ በመመለሱ ተነቅፏል እናም ይቀጣል።

የዚህ ትርጉም ግልጽ ነው። በምሳሌው ላይ ያለው ሰው ኢየሱስን ይወክላል፣ እኛ አገልጋዮች ነን፣ መክሊቱም ጌታ የሰጠን ርስት ነው። ርስቱ ምንድን ነው? ቃሉ፣ ቅዱስ ቁርባን፣ በሰማዩ አባት ላይ ያለው እምነት፣ ይቅርታው...፣ በሌላ አነጋገር፣ በጣም ብዙ ነገሮች፣ በጣም ውድ ሀብቶቹ። ይህ ርስት የተሰጠን ደብቀን እንድንጠብቀው ብቻ ሳይሆን ፍሬያማ ለማድረግ ነው! በተለምዶ አገላለጽ “መክሊት” የሚለው ቃል የግለሰባዊ ጥራትን የሚያመለክት ቢሆንም በምሳሌው ውስጥ፣ መክሊት የጌታን ሀብት የሚወክለው ፍሬ እንዲያፈራ አደራ ሰጥቶናል። “ክፉ እና ሰነፍ አገልጋይ” (ማቴ 25፡ 26) በአፈር ውስጥ የተቆፈረው ጉድጓድ ፈጠራን እና የፍቅርን ፍሬያማነትን የሚከለክለውን የአደጋ ፍራቻ ያመለክታል፣ ምክንያቱም የፍቅር አደጋዎችን መፍራት፣ ከተግባራችን እንድንቆም ያደርገናል። ኢየሱስ ጸጋውን ደብቀን እንድናከማች አይጠይቀንም! ኢየሱስ ይህንን አይጠይቀንም፣ ነገር ግን ሌሎችን ለመጥቀም እንድንጠቀምበት ይፈልጋል። የተቀበልነውን ጸጋ ሁሉ ለሌሎች ማካፈል ይኖርብናል፣ ይህንን ስናደርግ ደግሞ ጸጋዎቻችን እየጨመሩ ይሄዳሉ፡- “እነሆ ምሕረቴ፣ ርኅራኄዬ፣ ይቅርታዬ፣ ውሰዷቸውና አብዝታችሁ ተጠቀሙባቸው" ይለናል። በእምነታችን 'የማረክናቸው" ሰዎች ስንት ናቸው? በተስፋችን ስንት ሰው አበረታተናል? ከጎረቤታችን ጋር ምን ያህል ፍቅር ተካፍለናል? ብለን እራሳችንን ብንጠይቅ የሚጠቅሙን ጥያቄዎች ናቸው። የትኛውም አካባቢ፣ በጣም ሩቅ እና ተግባራዊ ያልሆነው፣ የእኛ ተሰጦ ፍሬ የሚያፈራበት ቦታ ሊሆን ይችላል። ከክርስቲያን መገኘት እና ምስክርነት የተከለከሉ ሁኔታዎች ወይም ቦታዎች የሉም። ኢየሱስ ከእኛ የሚጠይቀው ምስክርነት የተዘጋ አይደለም፣ ነገር ግን ክፍት ነው፣ በእጃችን ነው።

ይህ ምሳሌ እምነታችንን እና የክርስቶስ መሆናችንን እንዳንደብቅ፣ የወንጌልን ቃል እንድንቀብር ሳይሆን በሕይወታችን፣ በግንኙነታችን፣ በተጨባጭ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲሰራጭ፣ የሚያበረታታ፣ የሚያጠራ፣ የሚያድስ ጥንካሬ እንዲሆን ያሳስበናል። በተመሳሳይም ጌታ በተለይ በምስጢረ ንስሐ በኩል የሚሰጠን ይቅርታ በውስጣችን ቆልፈን እንድንይዘው ሳይሆን ኃይሉን እንዲያወጣ እንፍቀድለት፣ ይህም ኃይላችን በራስ ወዳድነት መንፈስ የተገነባውን የጥል ግድግዳ የምያፈርስ፣ ይህም በችግር ውስጥ ያለ ግንኙነት ውስጥ የመጀመሪያውን እርምጃ እንድንወስድ ያስችለናል፣ መግባባት በሌለበት ውይይ እንዲቀጥል፣ ሰላም በሌለበት ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ... እና የመሳሰሉት። እነዚህን መክሊቶች፣ እነዚህ ስጦታዎች፣ እነዚህም ጌታ የሰጠን፣ እንድናድግ፣ ለሌሎች ፍሬ እንድናፈራ ሊያደርገን ይገባል።

እያንዳንዳችን ዛሬ በቤታችን ውስጥ ያለውን መጽሐፍ ቅዱስ አንስተን በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ምዕራፍ 25 ከቁጥር 14 እስከ 30 በድጋሚ አንብበን ትንሽ ብናሰላስል፡- “እግዚአብሔር የሰጠኝን መክሊት፣ ሀብት፣ የሰጠኝን ሁሉ መንፈሳዊ በረከት፣ ፀጋ፣ ቸርነቱን ሁሉ እንደ ሰነፉ አገግልጋይ ደብቄ አከማቻለሁ ወይስ ፍሬ እንዲያፈራ አውጥቼ እጠቀማለሁ? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል።

ከዚህም በላይ ጌታ ለሁሉም ሰዎች ተመሳሳይ ነገሮችን በተመሳሳይ መንገድ አይሰጥም፣ እርሱ እኛን በግል ያውቀናል እና ለእኛ ትክክል የሆነውን አደራ ሰጥቶናል፣ ግን በሁሉም ውስጥ እኩል የሆነ ነገር አለ ፣ አንድ ዓይነት ፣ ትልቅ እምነት። እግዚአብሔር እኛን ያምናል፣ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ተስፋ ያደርጋል! እናም ይሄ ለሁሉም ሰው ተመሳሳይ ነው። አናሳዝነው! በፍርሃት እንዳንታለል፣ ነገር ግን እምነትን በመተማመን እንመልስ! ድንግል ማርያም ይህንን አመለካከት በፍፁም እና በሚያምር መልኩ አሳይታለች። እጅግ የላቀውን ስጦታ ኢየሱስን ተቀበለችው እናም በምላሹም ለሰው ልጆች በልግስና ሰጠችው። "በጌታችን ደስታ" ለመሳተፍ "ጥሩ እና ታማኝ አገልጋዮች" እንድንሆን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ ትርዳን። አሜን!

የእዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅታቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ

 

 

29 Mar 2025, 13:39