MAP

በአሌፖ ገጠራማ አካባቢዎች በተፈፀመ ጥቃት በትንሹ 6 ሰዎች ተገድለዋል በአሌፖ ገጠራማ አካባቢዎች በተፈፀመ ጥቃት በትንሹ 6 ሰዎች ተገድለዋል   (ANSA)

በሶሪያ የነበሩት ጥቂት ተስፋዎች አሁን ላይ ጠፍተዋል ተባለ

በሶሪያ ጥቂት ወራትን ብቻ ካስቆጠረው ሰላም በኋላ በቅርቡ ለሳምንታት ተጠናክሮ የቀጠለውን ብጥብጥ ተከትሎ በሀገሪቱ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በአሌፖ የሚገኙት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ እና ካህን በጉዳዩ ዙሪያ ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የበሽር አል አሳድ አገዛዝ ታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ በሃገሪቷ ለወራት መረጋጋት ታይቶባት የነበረ ቢሆንም፥ ከሶስት ወራት ቆይታ በኋላ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ግድያ፣ አፈና፣ ስርቆት፣ ፆታዊ ትንኮሳ እና ዝርፍያ በሶሪያ እንደገና መቀስቀሳቸው ተነግሯል።

በሃገሪቷ ባህር ዳርቻ ክፍለ ግዛት ውስጥ የቀድሞ ፕሬዝደንት ታማኞች ከጸጥታ ኃይሎች ጋራ ባደረጉት አስከፊ ግጭት በተጀመረ ሁከት ሀገሪቱ ውስጥ በርካቶች ለሞት የተዳረጉ ሲሆን፥ ሲቪሎችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

እርግጠኛ መሆን ያልተቻለበት ጊዜ
የሶሪያ የሰብአዊ መብቶች ታዛቢ እንዳስታወቀው አሳድ ከስልጣን ከተባረረ በ 100 ቀናት ውስጥ 4,700 ንፁሀን ዜጎች መገደላቸውን ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ ከወራት ሰላማዊ ቆይታ በኋላ ባለፈው ሳምንት በበሽር አላሳድ ደጋፊዎችና በአዲሱ የሶሪያ መንግስት የጸጥታ ሀይሎች መካከል በተከፈተ ውግያ ከ 70 ሰዎች በላይ መገደላቸው ተገልጿል። አጸፋውን ለመመለስ የሱኒ እስላማዊ መንግስትን የሚደግፉ ታጣቂዎች የተለያዩ ጥቃቶችን ፈጽመዋል ተብለው ተከሰዋል።

በሶሪያ የላቲን ሥርዓት የምትከተል ቤተክርስቲያን ካህን የሆኑት አባ ባህጃት ካራካች እና የአሌፖ የላቲን ሥርዓት ተከታይ ሐዋሪያዊ አስተዳደር ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ሃና ጃሉፍ ከክርስቲያን ሚዲያ ሴንተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በአከባቢው ስለሚገኙ ክርስቲያኖች ሁኔታ እና በሶሪያ ሰላም እንዲሰፍን ያደረጉትን ሚና ገልፀዋል።

አባ ካራካች በአሌፖ እንዲሁም በአጠቃላይ በሶሪያ ያለው ድባብ በእርግጠኝነት የማይታወቅ መሆኑን በመግለጽ፥ “የአገዛዙ መውደቅ ማለት ወዲያውኑ ወደ መደበኛው ህይወት መመለስ ማለት አይደለም” በማለት አሁን ያለውን ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ ሲሉ ገልጸዋል። ሰዎች በፍርሃት ውስጥ እንደሚኖሩ እና ስለወደፊቱ ጊዜ እርግጠኛ እንዳልሆኑ ጠቁመው፥ “የነበሩት ጥቂት እርግጠኝነቶች አሁን ላይ ጠፍተዋል” በማለት አባ ካራካች ገልጸዋል።

ላለፉት 13 ዓመታት ሲካሄድ የነበረው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነቶች የአሳድ መንግስት ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ትንሽ ጋብ ያለ ቢመስልም አሁን የተነሳው ሁከት እና ብጥብጥ ግን እጅግ የከፋ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል።

በአሌፖ የሚገኙት የላቲን ሥርዓት ተከታይ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ አስተዳደር የሆኑት ብጹእ አቡነ ሃና ጃሉፍ ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩት በተለያዩ ቡድኖች መካከል የሚደረጉ ግጭቶች “አሳፋሪ ናቸው” ሲሉ አበክረው ከገለጹ በኋላ፥ ‘ወደ ቀደመው ሥርዓት መመለስ ለሚናፍቁ’ ላሏቸው ሰዎች ባስተላለፉት መልዕክት “ታሪክ ወደ ፊት መሄድ እንጂ ወደ ኋላ እንደማይመለስ ይረሳሉ” ብለዋል።

ክርስቲያኖች ሰላምን ለማምጣት ድርሻ አላቸው
ክርስቲያኖች ከእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ከአጠቃላይ የሶሪያ ህዝብ 2 በመቶ ያህል በመሆን በሀገሪቱ ውስጥ በቁጥር አናሳ ቢሆኑም፥ ብጹእ አቡነ ጃሉፍ እና አባ ካራካች እንደሚሉት የክርስቲያኖች መገኘት ለእርቅ ትልቅ ሚና እንዳለው አጥብቀው ይከራከራሉ።

አባ ካራካች ከዚህም በተጨማሪ የክርስቲያኑ ማህበረሰብ ግባቸውን ለማሳካት “ምንም ዓይነት ውጊያ ወይም ዓመፅ ተጠቅመው አያውቁም” በማለት ገለልተኛ እንደሆኑ የገለጹ ሲሆን፥ ይህም ባህሪያቸው “አሁን በሶሪያውያን ዘንድ ተአማኒነት እንዲኖራቸው” እንዳደረገ እና ይህ አድልዎ የሌለበት አካሄድ ክርስቲያኖች በተለያዩ ቡድኖች መካከል የውይይት ድልድይ መሆን እንዳስቻላቸው አብራርተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሶሪያ ውስጥ ግጭት ከ6 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ጨምሮ ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን አፈናቅሏል ብሏል።

አባ ካራካች ሶሪያ በአሁኑ ጊዜ ወደ 15 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የጤና አጠባበቅ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎችን በመያዝ ዓለም ላይ ካሉ አስከፊ ሰብዓዊ ቀውሶች ካሉባቸው ሃገራት መካከል አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፥ የክርስቲያኑ ማኅበረሰብ “በዙሪያው ላሉ ሰዎች አርአያ እንዲሆን” ካበረታቱ በኋላ፥ በመጨረሻም “የሀይማኖት ነፃነት ፈተና በገጠመው እና አክራሪነት እየተስፋፋ ባለበት ሀገር መካከል ብንሆንም፣ ይህ ተስፋ ሊያስቆርጠን አይገባም፥ የበለጠ አስተዋይ እንድንሆን ይገፋፋናል” በማለት አጠቃለዋል።
 

20 Mar 2025, 12:48